መልእኽቲ ኣይተ ረዳኢ ሓለፎም ሓላፊ ቢሮ ርክብ ህዝብን መንግስትን ክልል

907

ትግራይ።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።05-01-2011ዓ.ም
የተከበራችሁ የኦነግ ኣመራሮች፣
የተከበራችሁ የኦነግ ሰራዊት አባላት፣
የተከበራችሁ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣
የተከበራችሁ የመቐለ ከተማ አመራሮች፣
የተከብራችሁ የጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን አመራሮችና አባላት፣
የተከብራችሁ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች፣
ክቡራትና ክቡራን፣
ከሁሉም አስቀድሜ የኦነግ ኣመራሮችና የሰራዊት አባላት የትጥቅ ትግል አማራጭን በመዝጋት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስናችሁ ወደሀገራችሁ ስለገባችሁ እንኳን በሰላም መጣችሁ ለማለት እፈልጋለሁ።
የኢፌዴሪ መንግስት ያቀረበላችሁን የሰላም ጥሪን በመቀበል በሀገሪቱ ፖለቲክ ውስጥ በሕጋዊና ሰላማዊ አኳኋን ለመታገል መወሰን የሰለጠነና ከሁሉም በፊትደግሞ የህዝብን ጥቅም ማስቀደም በመሆኑ የኦነግ አመራሮችና የሰራዊት አባላት ለወሰዳችሁት ሰላማዊ አማራጭ ሊትመሰገኑ ይገባል።

ኦነግ በሕግዊና በሰላማዊ መንገድ መታገል የሚያስችል ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ባላት ሀገር ውስጥ የትጥቅ ትግል ማካሄድ የሀገር የዕድገትና የለውጥ ጉዞ የሚያደናቅፍ መሆኑ በማመን ሰላማዊ የትግል ስልት መምረጡ ትክክለኝ ውሳኔ በመሆኑ ምስጋናና እውቅና ሊቸረው የሚገባ የተቀደሰ ተግባር ነው።
ስለሆነም ኦነግ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት በማክበርና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ አወንታዊ ሚና ለመጫወት በሚያደርገው ጥረት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ድጋፍ እንደማይለየው ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ማክበርና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ጉዳይ በጋራ ርብርብ እንጂ በተናጠል እውን የሚሆን ጉዳይ አይደለምና።

ክቡራትና ክቡራን፣
እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ ሀገር እና እንደ ህዝብ ህልውናችን የሚረጋገጠው በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት፣ መከባበር መተሳሰብና ፍቅር ላይ የተመሰረት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ዘላቂነት እስካለው ድረስ ነው። በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል እኩልነት ሳይሆን መበላለጥን፣ መከባበር ሳይሆን መናናቅን፣ መተሳሰብ ሳይሆን መናቆርን፣ ፍቅር ሳይሆን ጥላቻን የበላይነት የሚያገኙ ከሆነ እና ችግሮቹ ሲፈጠሩም በአፋጣኝ የማይታረሙ ከሆነ ግን የሀገራችን እጣ ፈንታ እጅግ አስቸጋሪና የተወሳሰበ መሆኑ አይቀርም። የኦነግ አመራር እና የሰራዊት አባላትም በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስር እንዲሰድ በሚደረገው አጠቃላይ ጥረት ገንቢ ሚና መጫወት ይችላሉ የሚል ሙሉ እምነት አለን።

የተከበራችሁ የኦነግ ኣመራሮች፣
የተከበራችሁ የኦነግ ሰራዊት አባላት፣
ክቡራትና ክቡራን፣
ከባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እየተፈፀሙ ያሉ ማንነትን ማእከል ያደረጉ ጥቃቶችና በደሎች የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ በጥብቅ የሚኮንኗቸው ናቸው። እነዚ ድርጊቶች የዜጎች የመዘዋወር፣ የመኖር እና ሃብት የማፍራት ሕገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚፃረሩ ተቀባይነት የሌላቸው አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ስለሆኑ ሁላችን ልናወግዛቸውና ሊንታገላቸው ይገባል።

የተከበራችሁ የኦነግ ኣመራሮች፣
የተከበራችሁ የኦነግ ሰራዊት አባላት፣
ክቡራትና ክቡራን፣
የትግራይ ህዝብ ለዘመናት ያካሄደው መራራ ትግልና የከፈለው ክቡር መስዋእት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የሃይማኖቶችን የእምነት፣ የቋንቋ እንዲሁም የፃፆታ እኩልነት ለማረጋገጥና ማንኛም የአድልዎ ዓይነት ለማስወገድ ነው። የትግራይ ህዝብ አሁንም በተመሳሳይ እነዚህ እኩልነቶች አደጋ ውስጥ የሚከቱ አስተሳሰቦችና ተግባራት አይቀበልም። በዚህ ረገድ የኦነግ አመራሮችና የሰራዊት አባላትም ተመሳሳይ ዓላማ ይዘው ሰላማዊ ትግላቸውን እንደሚያካሂዱ ጥርጥር የለንም።

በመጨረሻም ኦነግ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመታገልና የሀገራችን ህዳሴ እውን ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደማይለየው ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።
መንገዳችሁ ሁሉ ሰላም ይሁን!!
አመሰግናለሁ!

Comments are closed.