Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተያዙ ወጣቶች ወደየመጡበት እንዲመለሱ ተደረገ

0 714

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተያዙ ወጣቶች ወደየመጡበት እንዲመለሱ ተደረገ

በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው በሐረር ከተማ በኩል ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ ሲሞክሩ የተያዙ ወጣቶች ወደየመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የሐረሪ ክልል አመራሮች በአካባቢው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ላይ በፌዴራል ደረጃ ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው ባለፉት አራት ወራት ሀረር ከተማን አቋርጠው በኢትዮጵያ ሶማሌ በኩል ወደ አረብ አገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ ከስድስት ሺህ በላይ ወጣቶች ተይዘዋል፡፡

ለወጣቶቹ ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ ወደ የመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሰልሃዲን አሊ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳሉት ወጣቶቹን ወደ የመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ የተደረገው የስደትን አስከፊነት በመረዳት በሀገር ወስጥ ጠንክሮ መስራት ከተቻለ መለወጥ እንደሚችሉ ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ ነው፡፡

የተመለሱት ወጣቶች ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ እንደነበረም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

ወጣቶችን በህገ ወጥ መንገድ እያታለሉ ለእንግልት፣ለዘረፋ፣ለሞትና ስቃይ እንዲዳረጉ በማድረግ ተሳታፊ የነበሩ 12 ደላሎች ተይዘው እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸውን አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ጉዳዮዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው በክልሉ የሚታየውን ህገ ወጥ ዝውውርን ለመከላከል ከህብረተሰቡ፣ ከአጋር አካላትና ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመተባበር ጥረት ቢደረግም አሁንም አሳሳቢ ሆኖ እንደቀጠለ ገልጸዋል፡፡

ችግሩ ሊወገድ ያልቻለው ህገ ወጥ ደላሎቹ ወጣቶቹ ከሚነሱበት ስፍራ እስከ ሚደርሱበት ቦሳሶ ወደብ ድረስ ያለው የቅብብል ስራ የረቀቀ በመሆኑ ነው፡፡

ወጣቶቹ በሚያዙበት ወቅት ለፖሊስ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ያለመፈለግ ሁኔታም ይስተዋላል፡፡

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ከምንጩ ለማድረቅ የሁሉም ክልሎች ፖሊስ ተቋማት ተቀናጅተው በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በወጣቶቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ የሀገር ገጽታ የሚያበላሽ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሐናን ዱሪ ናቸው፡፡

በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር የተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ እንደገለጹት ደግሞ መንግስት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል አዋጅ ከማውጣቱም በላይ ስትራቴጂክ ፕላን ቀርጾና ግብረ ሃይል አቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው።

የውይይቱም ዓላማም በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው ከሀገር በህገወጥ መንገድ የሚወጡ ዜጎችን ከመነሻቸው ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ለይቶ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሐረር ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ በክልሉና በፌዴራል ደረጃ ከሚገኙና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የተወከሉ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ኢዜአ፣ ሀረር 9/2008

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy