ባለፈው ወር ከፈረንሳይ ወደ ካይሮ እየተጓዘ እያለ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ የተከሰከሰው የግብፅ አየር መንገድ አውሮፕላን ስብርባሪ አካል መገኘቱ ቢቢሲን ጠቅሶ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡
ግብፃውያን መርማሪዎች ናቸው የአውሮፕላኑ ክፍል የሆነ ስብርባሪ መገኘቱን ያስታወቁት።
ስብርባሪ አካሉ የሚገኝበት አቅጣጫም ተለይቷል።
ጥልቅ የባህር ውስጥ ፍለጋ ጀልባም የስብርባሪ አካሉን ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ ልካለች ተብሏል።
የበረራ ቁጥሩ ኤም ኤስ 804 የሆነው የግብፅ አየር መንገድ አውሮፕላን በፈረንጆቹ ግንቦተ 19 ነበር 66 መንገደኞችን አሳፍሮ ከፓሪስ ወደ ካይሮ እየተጓዘ እያለ በሜዲትራኒያን ባህር የተከሰከሰው።
ኤርባስ ኤ320 አውሮፕላኑ ምንም መልዕክት ሳይጠቁም ከግሪክ እና ግብፅ የራዳር እይታዎች ውጪ መሆኑ ይታወሳል።
በመከስከስ አደጋው 66ቱም መንገደኞች ህይወታቸው አልፏል።