Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመረጠች

0 468

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመረጠች

ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመረጠች

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመረጠች።

ዛሬ በኒውዮርክ በተካሄደው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ በብቸኝነት ተወዳድራለች።

ድምፃቸውን ከሰጡ 190 አገራት መካከል የ185 የድርጅቱ አባል አገራትን ድምፅ በማግኘትም ነው የአፍሪካን ቦታ በመወከል ለሁለት ዓመት ያገለገለችውን አንጎላን የተካችው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2017 እስከ 2018 ለሁለት ዓመት የምታገለግል ይሆናል።

ከፈረንጆቹ ጥር ወር 2017 ጀምሮም በይፋ በምክር ቤቱ አባልነት ስራዋን ትጀምራለች።

ከምርጫው ቀደም ብሎ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ኒውዮርክ ላይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት አባልነት ቆይታዋ የአፍሪካውያንና የታዳጊ አገራትን ጥቅም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት ትሰራለች።

አገሪቷ የዓለም ደህንነትና ሠላምን ለማረጋገጥ፣ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለማስወገድ ግልጽ አቋም እንዳላት ገልጸው፥ ይህን አቋሟን ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ጥቅሞቻቸውን በማስጠበቅ በኩል ያከናወነቻቸው ተግባራት ግምት ውስጥ በማስገባት ድምፃቸውን አስቀድመው ሰጥተዋታል።

የዓለም የመንግሥታት ማኅበር ፈርሶ የተባበሩት መንግሥታት ሲመሰረት ነፃነታቸውን ጠብቀው በመስራችነት የተገኙ አገራት ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ናቸው።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1950 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ አገራት እንዲረጋጉ፣ የህዝቦች ደህንነትና ሠላም እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ አበርክታለች።
ኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ላይቤሪያ ደግሞ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የሠላም ማስጠበቅ ተልዕኮ የተወጣችባቸው አገራት ናቸው።

አሁንም ከተባበሩት መንግሥታት የሠላም አስከባሪ ኃይል ጋር በመሆን በሱዳን አብዬና ዳርፉር ግዛቶችና በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ አፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ (አሚሶም) ሥር በሶማሊያ ተልዕኳዋን በመወጣት ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ቁጥሩ የበዛ ሠላም አስከባሪ ኃይል በማሳለፍ በዓለም በሁለተኛነት ስትቀመጥ በሴት የሠላም አስከባሪ አባላት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ናት።

አገሪቷ ለሁሉም አገሮች ስደተኞች በሯን ክፍት በማድረግ ከተለያዩ አገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ደረጃም ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆን ችላለች።

ዶክተር ቴድሮስ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ ለዓለም ሠላምና ደህንነት በቁርጠኝነት በመስራቷ የአፍሪካውያንን ሙሉ ድምጽ አግኝታለች።

ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1967 እስከ 1968 እንዲሁም ከ1989 እስከ 1990 ለሁለት ያህል ጊዜ አገልግላለች።

Dr_Tedros_voting.jpg

የፀጥታው ምክር ቤት አባልነት ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል።

ከእነዚህም ውስጥ ሀገሪቱ በዓለም ሀገራት ላይ ያላት ተደማጭነት እንዲጨምር ያደርጋል።

በየትኛውም ዓለም በሚኖር ግጭት ሀገሪቱ የራሷን አቋም እንድትይዝ፣ በአፍሪካ ላይ ያላት የመሪነት ሚናም እንዲጨምር እና ብሄራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጠቀሜታዎችም አሉት።

በአዲስ አባበ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ደመቀ አጢሶ፥ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባልነት ቀጥታ እና ቀጥታ ባልሆነ መንገድ የሚገኙ ጠቀሜታዎች አሉት ይላሉ።

ቀጥተኛ ጥቅሞቹም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ስፍራ እና ከበሬታ ከፍ እንዲል ማድረግ እና ከአደጉ ሀገራት ጋር አብሮ የመስራት እድልን መፍጠር ነው ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ከአገራቱ የምታገኘው ድጋፍ ከፍ እንዲል ያደርጋል ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር ደመቀ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ቀጥተኛ ባልሆነ ጠቀሜታ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ከፍ እንዲል እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የምክር ቤቱ አባል ሆና አገልግላለች። የአሁኑ አባልነቷ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፥ ይህም ከዚህ በፊቶቹ በበርካታ መልኩ እንደሚለይ ረዳት ፕሮፌሰር ደመቀ ይናገራሉ።

ይህም ሀገሪቱ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እያበረከተችው ያለው አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ በሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ፥ የሀገሪቱ የውጭ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስተባባሪ አቶ ፀጋ ክበበው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ጊዜ የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆኗ ሀገሪቱ ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የምታደርገውን ጉዞ ያግዛል ብለዋል።

አባል አገራት የመረጡትን አጀንዳ ለውይይት ወደ ምክር ቤቱ ይዘው መሄድ ይችላሉ?

የትኛውም የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገር የመረጠውን አጀንዳ ማቅረብ የሚችል ሲሆን፥ ውይይት የሚደረግበት ግን ከ15 የምክር ቤቱ አባል አገራት መካከል የዘጠኙን ድጋፍ ሲያገኝ ነው። የምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ ሆኖ ለመፅደቅ የአምስቱ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ያላቸው አገራትን ጨምሮ የዘጠኝ አባል አገራትን ድምፅ ማግኘት ይገባዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy