ሰኔ 08፣2008
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ መንግስት ለአምስት ፕሮጀክቶች ማስፋፊያና ማስፈጸሚያ የሚውል የ18 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጠ።
ብድሩ ለከፍተኛ ትምህርትና ለኤሌክትሪክ መሥመሮች ማስፋፊያ፣ ለዘመናዊ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ለስደተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ይውላል።
ስምምነቱን የተፈራትረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካሮሊን ቱርክ ናቸው።
ሚንስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በብድር ከተገኘው 6 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብሩ በከተሞች ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስፋፋት ይውላል።
እንዲሁም 4 ነጥብ 34 ቢሊዮን ብር ለጥቃቅንና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ማጠናከሪያ እንደሚውልም ተናግረዋል።
የተገኘው ገንዘብ አገሪቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥታ የምትሰራባቸውን ዘርፎች በላቀ ሁኔታ ለማስቀጠል እንደሚረዳም አቶ አብዱልአዚዝ ተናግረዋል።
ባንኩ ብድሩ አገሪቱ የነደፈችውን ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሚያሳልጥና እድገቱን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ምንጭ፡- ኢዜአ