የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የሚሰጡ መግለጫዎች ወቅታዊ ሊሆኑ ይገባል :-ም/ቤቱ
ሰኔ 08፣2008
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት በፅሕፈት ቤቱ የሚሰጡ መግለጫዎች ወቅታቸውን የጠበቁ መሆን እንደሚገባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል ቱሪዝምና መገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሀን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግስት ኮሚንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።
ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን ያቀረቡት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ጽሕፈት ቤቱ በአገሪቱ በሚከሰቱ ሁነቶች የጋራ አጀንዳ ከመቅረጽ አንፃርና በየጊዜው በሚከናወኑ ጉዳዮች ዙሪያ በሚሰጡ መግለጫዎች ተመስርቶ በህዝብ ዘንድ የጋራ አመለካከት መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው እባላትም በቀረበው ሪፖርት መሰረት ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን በጽሕፈት ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው ግብረ መልስ ጽሕፈት ቤቱ የኮሚኒኬሽንና የሚዲያ ስራዎችን በተደራጀ የለውጥ ሰራዊት ለመምራት ያከናወናቸው ስራዎች፣ በጽሕፈት ቤቱ ማሻሻያ ሰነዶች፣ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ በመንግስት ኃላፊዎች በተሰጡ መግለጫዎችና የህዝብ አስተያየት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን የዳሰሰ ጥናት በማድረግ ከጥናቱ በተገኙ ውጤቶችና በመፍትሔ ሀሳቦች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት መምከሩን በጠንካራ አፈጻጸም ገምግሟል።
ጽሕፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ከመመደብና ከማዘዋወር ረገድ ተቋማት የሚመደብላቸው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አለመቀበልና ተቋማት ድጋፍ አግኝተው የመረጃ ምንጭነት ሚናቸው በአግባቡ አለመወጣታቸው በጉድለት የሚታይ መሆኑን ገልጿል።
በጽሕፈት ቤቱ የሚሰጡ መግለጫዎች ወቅታቸውን ጠብቀው መውጣት እንደሚገባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
ሪፖርተር፥ ተስፉ ወልደገብርኤል