Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢ.ፌ.ድ.ሪ የመከላከያ አዛዥነትና እስታፍ ኮሌጅ በተለያዩ ሙያ ያሰለጠናቸውን መኮንኖችን በዛሬው እለት አስመርቋል። በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ያደረጉት ንግግር ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

0 2,068

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 ውድ የኢ.ፌ.ድ.ሪ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች የኢ.ፌ.ድ.ሪ የመከላከያ አዛዥነትና እስታፍ ኮሌጅ ተመራቂ መኮንኖችና ቤተሰቦች የተከበራችሁ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ክብራት ክቡራን ! ከሁሉ አስቀድሜ የረዥም ጊዜ ጥረታችሁን ውጤት በምታከብሩበትና በምታወድሱበት የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ በመካከላችሁ ተገኝቼ የደስታችሁ ተካፋይ ለመሆን በመታደሌ የተሰማኝን ልባዊ ደስታና ኩራት እየገለፅኩ ውድ የመከላከያ አዛዥነትና እስታፍ ኮሌጅ ተመራቂዎችና ቤተሰቦቻችሁ እንኳን ለዚህች ቀን አደረሳችሁ፣ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ፡፡
q1
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን የቆመለትን ሕዝባዊ ዓላማ ታላቅነት በአግባቡ በመረዳት፤ በሕዝብና በመንገስት የተጣለበትን የከበረና ከባድ አደራ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፈፀም በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ይህ የምርቃት ሥነ-ስርዓትም ሰራዊታችን በብቃት እየተወጣቸው ያሉትን ታሪካዊ ግዳጆችን እንዲሁም መላ የአገራችን ህዝቦችን በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ ያለው ቀጣይነት ያለው ልማታችንና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደታችን ጽኑ መሠረት የሆነውን ሰላም እና ዋስትና ያላው ዴሞክራሲ በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ያለበትን ሃላፊነትና የማይተካ ሚና በወጉ ለመገንዘብ ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥርልን ቀንም ጭምር ነው፡፡ ሀገራችን ከምትገኝበት ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ የተነሳ በዓለማችን በየጊዜው ከሚከሰቱ በርካታ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ተዋናዮች የሚመነጩ የተለያዩ ስጋቶች በሀገራችንና በህዝቦቿ ሰላም፣ልማትና ደህንነት ላይ የሚደቀኑ ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን በመከላከልና አደጋውን በመቀነስ ጀግናው ሠራዊታችን ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች እና ከህዝቡ ጋር በመሆን ያከናወናቸውን ግዳጆችና ወደፊትም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን ለመመከት ያለውን አቅም ብቃትና የዝግጁነት ደረጃ እያሰብን የምንፅናናበትና የምንኮራበት ዕለት ነው፡፡ ውድ ተመራቂዎች ክቡራትና ክቡራን ! በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን፣በአገራችንና በአከባቢያችን ያለው የፀጥታና የሠላም ምህዳር እጅግ ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ ለመተንበይ እንኳን በጣም አስቸጋሪ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የተወሰኑ የአፍሪካ ክፍሎች ፣ ጎረቤት አገራት እንዲሁም መካከለኛው ምስራቅ በማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የገቡበትና ማብቂያው ወደ ማይታወቅበት ግጭቶችና ሁከቶች ውስጥ በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ ፡፡
በዚህም ለከፋ ሰብአዊና ማህበራዊ ቀውስ በመዳረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተያያዘም አክራሪነትና አሸባሪነት ህገ ወጥ የሠዎች፣የገንዘብ የአደንዛዥ ዕፆች ዝውውርና ድንበር ዘለል የተደራጁ ወንጀሎችና ጥቃቶች ዘመኑ ያፈራቸውን የጦር መሳሪያዎችና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ውስብስብ በሆነ መልኩ የሠውን ልጅ ፀጥታና ደህንነትን እየተፈታተኑ በሚገኙበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ከፀጥታ ስጋትም አልፎ የዓለም የፖለቲካ ሁኔታም አዳዲስ ክስተቶች የሚታዩበትና ያልተተነበዩና ያልተገመቱ ሁኔታዎች በየቀኑ የሚታዩበት ታሪካዊ ሂደቶች ውስጥ እንገኛለን፡፡
ምናልባትም የዓለምን ሀገሮች የሀይል ሚዛን የሚገለባበጡ ከዚህ በፊት መተከሰቱ ሁኔታዎች ያልተናነሱ ኩነቶችን እየተመለከትንም እነገኛለን፡፡ ስለሆነም መከላከያ ሠራዊታችንን በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስና የላቀ ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ በመላበስ በየወቅቱ ከሚለዋወጡ ዓለማዊ፣ አህጉራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች አንፃር በቀጣይነት ራሱን እያበቃ ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቃትና ዝግጁነት እያረጋገጠ በመምጣት የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ለውጥና ለህዳሴያችን መረጋገጥ ዘብ መቆም ብቻ ሳይሆን፣እንደተቋም በውስጡም የለውጥና የዕድገት ፋና ወጊና ለምናካሂደው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የቴክኖሎጂ አቅም በመፍጠርና በማከማቸት ጭምር ዋነኛ ተዋናይ እንዲሆን ትምህርትና ስልጠና እዲሁም ምርመራ የማይተካ ሚና እንደሚኖራቸው ታውቆ በታቀደና የታወቀ ግብን መሰረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በየጊዜውም እየተከለሱና እየታደሱ እንዲሄዱ ማድረግ ግን ይገባናል፡፡ በመሆኑም የመከላከያ ሀይላችን ለተሰጠውና ለሚሰጠው ተልዕኮ በብቃት የተዘጋጀ እንዲሆን የሚሰራቸው ቀጣይነት ያላቸው የአቅም ግንባታ ስራዎች በአስተማማኝ ሁኔታ የተዘጋጀ እንዲሆን እያደረጉት ናቸው ፡፡
a0
ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ሠራዊታችን አሸናፊና ምንጊዜም ድል እንዲቀዳጅ ተደርጎ የተገነባ ሠራዊት ነው ፡፡ አስተማማኝና ሁሌም ዝግጁ የሆነ ህዝባዊ ኃይልም ነው፡፡ አሁን ያለው የሠራዊታችን ቁመና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የሚያድግ ተተኪ የሆኑ ጀግና ወታደሮችንና ሙያተኞችን በየደረጃው የአዛዥነት ብቃታቸው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል በወታደራዊ ሳይንስና ጥበቡ እንዲሁም በሠራዊታችን እሴቶች በራሱ አቅምና አደረጃጀት በመገንባት በየአውደ ውጊያው ሁሌም አሸናፊነት መለያቸው የሆኑ ለለውጥ የሚተጉና የሚጓጉ አመራሮችና ወታደሮች የያዘ የመከላከያ ተቋም ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በአስተማማኝ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ ከዚህ በበለጠና በተጠናከረ መንገድ የጀመርናቸው የለውጥ ስራዎች ተቋማዊ ባህል እንዲሆኑና ጥልቀትና ስፋት እንዲኖራቸው ጠንክረን መስራት ይገባናል፡፡ በተለይም የሠራዊታችን ነባር እሴቶችና የጀግንነት ታሪኮች በአዲሱ ትውልድ የሠራዎቲ አመራሮችና አባላት ዘንድ እንዲታወቁና እንዲሠርፁ እንዲሁም የዕለት ተዕለት መመሪያ እንዲሆኑ ለማድረግ ተጨማሪ ጠንካራ ሥራ መሥራት ይገባናል፡፡ ውድ የመከላከያ ሠራዊታችንን ከፍተኛ አመራሮች የተወደዳችሁ የመከላከያ የአዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ተመራቂ መኮንኖች፣ ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ክቡራትና ክቡራን ሠራዊታችን የጀመራቸውን የለውጥና የዕድገት ስራዎች የበለጠ በማጎልበት ውጤት ተኮር የሆነ በየትኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ለመዋጋትና ለማሸነፍ የተዘጋጀ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰራ እና ህጎችንና መመሪያዎችን ያለ አንዳች መዛነፍ የሚያከብርና የሚያስከብር እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ፍሬ እያፈራ ይገኛል፡፡
ይህንኑ ያለማንም ጎትጓች የተቋማዊ ባህል ሆኖ ስር እንከሚሰድና ለሌሎች መሰል ተቋሞችም የተሞክሮ ምንጭ ማድረግ እንከምንችል ያልተቆራረጠና ያልተገደበ ሥራ መሥራት እንችላለን፣ ይገባናልም፡፡ ይህን በማድረግም ሠራዊታችን የደርግ መንግስትን ለመገርሰስ በተደረገው የትጥቅ ትግሉ ወቅትም ሆነ ባለፉት ሁለት አስርተ-ዓመታት ለፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስትና ለሀገራችን ሉዓላዊነት እንዲሁም በአህጉራችን በተለያዩ አገራት የህዝቦችን ሠላም በማስጠበቅና ውጤታማ በመሆን የተጎናፀፍናቸውን እጅግ መልካም ገፅታዎች፣ እውቅናና ዝና ያገኙበት ህዝባዊ ባህሪው ተጠብቆና ጎልብቶ እንዲቀጥልና ይህም ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ተግተን መስራት መጠቀም ይገባናል፡፡ በመሆኑም የሠራዊታችን ግንባታና የለውጥ ጉዞ ከሀገራችን ህዳሴ ጎዞ ተነጥሎ የሚታይ ባለመሆኑ የኢኮኖሚያችን እና የዴሞክራሲያችን ዕድገትና የሠራዊታችን አቅም ተያይዘው ማደግ እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ባለፉት ተከታታይ አስራ ሁለት ዓመታት ኢኮኖሚያችን በእጥፍ አድጓል፡፡ የሠራዊታችን አቅምና ችሎታም እንደዚሁ ጎልብቷል፡፡ ይህ ቀጣይነት ያለው መስተጋብር ሳይዛነፍ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ ሠራዊታችንን በአቅማችን ልክ በዘመናዊ መሳሪያዎች የማስታጠቅና ደረጃ በደረጃም የመከላከያ እንዱስትሪያችን አቅም በተመሳሳይ መንገድ ለማሳደግ የጀመርነው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ሀገራችን አሁንም ታዳጊ ሀገር ናት፡፡ስለሆነም እስካሁን ስናደርግ እንደነበርነው ሁሉ ሠራዊታችን እያንዳንዷን የተመደበችውን ሳንቲም በቁጠባና በአግባቡ የመጠቀም ሙስና፣ ብልሹ አሰራሮችንና ብክነትን ለማስወገድ ተቋሙ የዘረጋቸውን የአሰራር ግልፅነትና የአደረጃጀት ለውጦችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ይህንን በማድረጉ ምክንያት በህዝቦቻችንና በመንግስት የተቸረውን አድናቆትና ክብር ጠብቆ እንዲሄድ የማያቋርጥ ትግልና ህግንና መመሪያን በጥብቅ ተግባራዊ በማድረግ የህግ የበላይነት የማስከበር ሥራ አጠናክሮ በቀጠል ይገባዋል፡፡ የሥርዓታችን ዋነኛ አደጋ እንደሆኑ የለየናቸው ኪራይ ሰብሳቢነትና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ የሆኑ ብልሹ አሰራሮች ሁሌም የሚደቅኑብን ፈተናዎች ያሉ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የማያቋርጥ ትግልና ግንባታ እንደጀመርነው ሁሉ ሳንዘናጋ ማስቀጠል አማራጭ የማይገኝለት የአመራሩ የዕለት ተዕለት ሥራ ነው፡፡ ህዝባችን በተለያዩ መንገዶች መከላከያ ሠራዊታችን የሚያከናውናቸውን ተግባራት በጥልቀት እንዲገነዘብና ለተልዕኮው መሳካትም የማይነጠፍ ድጋፉን እንዲሰጥ ተመልሶም መከላከያ ሠራዊታችን በየአካባቢው በሚካሄደው የልማትና የዕድገት ስራዎች በመሳተፍ እንዲሁም በሰው ሀይሉ ምልመላ ላይ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ አሟጦ እንዲሰጥ ለማድረግ ተከታታይ የህዝብ ግንኙነት ስራ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲሰራ ማድረግ ይገባናል፡፡ ውድ የመከላከያ ኮማንድና እስታፍ ኮሌጅ ምሩቃን መኮንኖች የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ክቡራትና ክቡራን! በዛሬው ዕለት ከሁለት ዓመታት ስልጠና በኃላ ለመመረቅ የበቃችሁበት መስክ የሀገር ፍቅርና የህዝብ አገልጋይነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተማራችሁበት ሳይሆን የዚህችን ታላቅ አገር እና ታላቅ ህዝብ የወደፊት ህዳሴ ለማረጋገጥ የሚያስችል ተጨማሪ ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም የአመራር ጥበብ ያጎናፀፋችሁ እንደሆነ ሁሉም ሰው ይገነዘበዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ የመከላከያ ሠራዊታችን ጥንካሬ፣የአመራሩ ብቃትና ቀጣይነት እንዲሁም በየቀኑ የሚታደስ ግዳጅን የመወጣት ብቃት የእናንተ ብቃት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የሀገራዊ ህልውናችን ቀጣይነት መሠረት መሆኑን አውቃችሁ ከእስካሁኑ ባልተናነሰ ምናልባትም እጅግ በተሻለ ሁኔታ ልትንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ ሁሌም ለመማር፣ ሁሌም ዓለማዊና አህጉራዊ እንዲሁም ሀገራዊ ሁኔታ ለመገንዘብና ለመተንተን የሚያስችላችሁን መነሻና መንደርደሪያ ያገኛችሁ በመሆኑ በዚሁ ላይ በመንተራስ የራሳችሁን ትጋትና ጥረት በማከል ራሳችሁንና የሠራዊታችሁን ተቋሞች ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የበኩላችሁን ድርሻ የተለመደው ፅላታችሁና ሕዝባዊነታችሁ እየገፋችሁ ማከናወን ይገባችኋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስፋ ከሠላምና ከልማት ብቻ እንደሆነ መንግስታችን አበክሮ ያምናል፡፡ ከጦርነትም እንዳልሆነና ጦርነት እጅግ አውዳሚና ወደኋሊት ጎታች እደሆነም አበክሮ ይገነዘባል፡፡ ይሁንና ሠላማችንንና ዕድገታችንን የማይፈልጉ ሀይሎች ሠላማችንን ለማናጋት እና አገራችንም የጀመረችውን በተስፋ የተሞላ የህዳሴ ጉዞ ለማደናቀፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም!ተኝተውም አያድሩም፡፡ ስለሆነም እነዚህን ሀይሎች በትኩረት በመከታተል ያሰቡትና የወጠኑት እዳይሳካ ለአጭር ጊዜ እንኳ ቢሆን ተስፋ እንዳይኖራቸው የሁሌ ዝግጁነት ማረጋገጥ ያለባችሁ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በተሰጣችሁና ወደፊትም የሚሰጣችሁን ተልዕኮና ግዳጅ እንደምትወጡ ያለኝን እምነት እየገለፅኩ የህዝቦቻችን ሠላም ዕድገትና ብልፅግና ለማናጋት ሌት ተቀን ለሚተጉ ኃይሎችም በዚህ አጋጣሚ እጆቻቸውን እንዲሰበስቡና የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር ከመፈፀማቸው በፊት ደግመው ደጋግመው እንዲያስቡበት ለማድረግ የሚያስችል ጀግና መከላከያ ሠራዊት እዳለን እንዲያውቁት እና የዚሁ ምንጭም ለልማትና ለዴሞክራሲ እንዲሁም ለሠላም ቆርጦ የተነሳ ጀግና ህዝብ እንዳለን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ በዘንድሮ ዓመት ብቻ የተጎናፀፍናቸውን አንፀባራቂ ድሎችና አስደናቂ ክንዋኔዎችን የአገራችንን ሠላምና ዕድገት ሁሌም ከማደናቀፍ ለአፍታም የማይቦዝኑት የሻዕቢያ መንግስት፣አልሸባብ እና ሌሎች ፀረ- ሠላም ኃይሎች ለሚያደርጉት ትንኮሳና የጥፋት ድርጊት መከላከያ ኃይላችን በጣም አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰዱ በቂ ምስክር ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች መሠል ፀረ- ሠላም ኃይሎች በየጊዜው ከሚያካሂዱት ትንኮሳና እኩይ ተግባራቸው ካልተቆጠቡ መከላከያ ኃይላችን የሚወስደው የተመጣጣኝ እርምጃ እስትራቴጂ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ በዚሁ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ዛሬም እንደወትሮው የኢ.ፌ.ድ.ሪ መንግስት ተልዕኳችሁን በብቃትና በህዝባዊ ወገንተኝነት እንዲሁም በእውቀትና ዘመናዊነት ለመወጣት በምታደርጉት ጥረት የማይነጥፍ ድጋፉን የሚሰጥ መሆኑን የምረቃችሁን በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የጀግናው መከላከያ ሠራዊት አመራሮች፣ አባላትና ቤተሰቦች እንዲሁም ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ በድጋሚ ተመራቂዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ ለዚህ ቀን ላበቋችሁ ለኮሌጁ ማህበረሰብና በስልጠናችሁ ወቅት አስፈላጊውን ድጋፍና የሞራል ስንቅ የሰጧችሁን ቤተሰቦቻችሁንና የስራ ጓዶቻችሁን በኢ.ፌ.ድ.ሪ መንግስትና በእራሴ ስም የከበረ ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ!
Chat conversation end

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy