Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰሞኑን በጐንደር ከተማ የተከሰተውን ሁከት አስመልክቶ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

0 1,117

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰሞኑን በጐንደር ከተማ የተከሰተውን ሁከት አስመልክቶ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሕዝብ ለዘመናት ከነበረበት ድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ባደረጉት ዙሪያ መለስ ርብርብ እነሆ ሁለንተናዊ ለውጥ የጀመረና ብሩህ ተስፋ የታየበት ክልል መፍጠር ችለዋል፡፡ የክልላችን ሕዝቦች አስከፊውን ስርዓት ለማስወገድ በከፈሉት መስዋዕትነት፣ ለልማት የተመቸና ማንም በሰላም ወጥቶ መግባት የሚችልበት፤ እንዲሁም ዜጐች ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት በመመስረት ላይ ይገኛሉ፡፡
በክልላችንም ይሁን በአገራችን እየተፈጠረ ያለው ይህ የሚያጓጓ እና ብሩህ ተስፋ የታየበት ሁኔታ ያልተመቻቸው እና የምንገነባው ስርዓት ጠላቶች በየጊዜው በክልላችን ልማትና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ለመሆን ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉም በአስተዋዩና ሠላም ወዳዱ የክልላችን ሕዝብ ጥረት አልተሳካላቸውም፡፡ ይህም በመሆኑ ክልላችን በመለወጥ ላይ ሲሆን በሀገራችን ለሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ሁነኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት አሁንም ማንኛውም አጋጥሚ በመጠቀም ክልላችንን ብሎም ሀገራችንን የብጥብጥና የሽብር ዓውድማ ለማድረግ ሌት ከቀን በመስራት ላይ ናቸው፡፡
ሰሞኑን በጐንደር ከተማ የብሔራዊ ፀረ-ሽብር ግብረ-ኃይል በወንጀል የጠረጠራቸውን አካላት በቁጥጥር ስር ለማዋል በተሰማራበት ወቅት በተፈጠረው ግጭት በሀገራችንና በክልላችን ፖሊስ አባላት እንዲሁም በንፁሃን ዜጐች ላይ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ በንፁሃን ዜጐች እና በመንግስት ንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡ በሂደትም በሰላም እና በተረጋጋ ሁኔታ በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጐች ላይ አለመረጋጋት ተከስቷል፡፡
ይህ የተፈጠረው ሁኔታ የክልሉን መንግስትና ሕዝብ በእጀጉ አሳዝኗል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የክልሉ መንግስት በተፈጠረው ሁኔታ እጅግ ያዘነ መሆኑን ሲገልፅ ለተጐጂ ወገኖች መፅናናትንና መረጋጋትን ይመኛል፡፡
በመሠረቱ በሀገራችን እየተገነባ ያለው ስርዓት የሕግ-የበላይነት ያለበት እንጂ ማንም ሰው በምንም ምክንያት ከሕግ በላይ የሚሆንበት ስርዓት አይደለም፡፡ በሕጉ መሠረት ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው አካል በወንጀል የጠረጠረውንና በቂ መረጃና ማስረጃ ሊያቀርብበት የሚችለውን አካል ሕጉንና አሠራሩን ጠብቆ በቁጥጥር ስር ማዋሉ የሚጠበቅና ለሕዝብና ለሀገር ደህንነት ሲባል የግድ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የክልላችንም መንግስትና ሕዝብ በሕግ የበላይነት ላይ መቼም ቢሆን የማያወላዳ አቋም ያላቸው ሲሆን ለሕግ የበላይነት አበክረው እንደሚሰሩ ማንም ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በመሆኑ ሕግን ለማስከበር የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለአፍታም ቢሆን ቸል የማንል ሲሆን በማንኛውም ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሕግና ስርዓትን ለማስከበር በትብብር የምንሰራ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ በመሆኑም ሻብዕያ እና መሰሎቹ በጐንደር እና አካባቢው የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምመላ ክልሉን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ መራወጣቸውን አቁመው አደብ እዲገዙ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ እንገደዳለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ በጐንደር እና አካባቢው የተፈጠረውን ሁኔታ ወደ መላ የክልላችን አካባቢዎች ለማስፋፋት ሕና ግጭቱም መልኩን ቀይሮ የዘር ቅርፅ እንዲይዝ ጥረት የሚያደርጉ ወገኖች ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጡ እናሳስባለን፡፡
የእስከ አሁኑም እኩይ እንቅስቃሴያቸው የተገታው በጐንደርና አካባቢው አርቆ አሳቢ እና አስተዋይ ሕዝብ ጥረት ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ለጐንደርና አካባቢው ሕዝብ በዚህ አጋጣሚ እስከአሁን ላሳየው ጨዋነት እና ታላቅ ኃላፊነት የተሞበላት እንቅስቃሴ የላቀ አክብሮትና ምስጋና ያለው መሆኑን እየገለፅን አሁንም እያንዳንዱን ነገር በአስተዋይነት፣ በአርቆ አሳቢነት እና በሕግ የበላይነት መነፅር እየተመለከተ ማንኛውንም ወንጀል እንዲከላከል ጥሪውን እያስተላለፈ በማንኛውንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ላይ ምህረት የሌለው እርምጃ እንደሚወስድ እንገልፃለን፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ሐምሌ 11 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም
ባህር ዳር

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy