Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ትግል በማጎልበት ጠባብነትና ትምክህተኝነትን እንመክት

0 1,030

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

1. ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ትግል በማጎልበት ጠባብነትና ትምክህተኝነትን እንመክት 1.1.ታዳጊ ዴሞክራሲያችን የሚጎለብተው በምክንያታዊነት የሚያምን ሕብረተሰብ በመፍጠር ነው በሓጎስ ገ/ክርስቶስ ክፍል 1 የኢትዮጵያ ህዝቦች አሁን የተገኘውን የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ለመሆን ያካሄዱት መራራ ተጋድሎና የከፈሉት መስዋእትነት እጅግ ውድ መሆኑን ግልጽ ነው ፡፡ የዜጎችና የቡድን መብቶች እንዲከበሩ ፣ዘላቂና አስተማማኝ ዋስትና ያለው ሰላም እንዲሰፍን መራራ ተጋድሎ አካሂደዋል ፡፡ ክቡር ህይወታቸውና አካላቸውም ገብረዋል ፡፡ በዚህም ሰው በላ የደርግ ስርዓት ግብአተ-መሬት እንዲገባ በማድረግ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የስልጣን ባለቤት የሆኑበት ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ተገንብቷል ፡በቀጣይነት እተገነባም ይገኛል ፡፡ እየተገነባ ያለው ስርዓት ሁሉም ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተጠቃሚ ያደረገ ስርዓት ነው ፡፡ እየተገነባ ያለ ስርዓት በብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መልካም ፈቃድ የተመሰረተ ፤ የቀደምት ስርዓቶች ኋላ ቀርና አድሃሪ አመለካከትን በመሰረታዊ መልኩ አሽቀንጥሮ የጣለ ስርዓት ነው ፡፡ የተጀመረው ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያውያን ላይ ተበይኖ ነበረውን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ልጓም የፈታ ፣ኢትዮጵያ የጥቂቶች ሳትሆን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ያደረገ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው ፡፡ አሁን እየተገነባ የሚገኘው ታዳጊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የቀድሞ ስርዓት እንደ ሃጥያት ሲመለከቱት የነበረውን የብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦች ፣የሃይማኖት እኩልነት እና ነጻነትን ያረጋገጠ ስርዓት ነው ፡፡ እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የግዛት አንድነት አስተሳሰብን በመናድ በምትኩ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተችውን የህዝቦች አንድነት የተቀበለና እየተገበረ ያለ ስርዓት ነው ፡፡ ለብተና ለመዳረግ አፋፍ ላይ የነበረችውን ሃገራችን ከብተና እና እልቂት ያተረፈ ስርዓት ነው ፡፡ የህዝቦችና የዜጎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እስርቤቶችን በማፈራረስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሆነች ሃገር የገነባና በመገንባት ላይ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው ፡፡ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፣በቋንቋቸው እንዲማሩ እና እንዲዳኙ ፣በባህላቸውና ማንነታቸውን እንደኮሩና እንዲያሳድጉ በጋራ ጉዳያቸው ደግሞ ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው በሚዛናዊ ውክልና በጋራ እንዲወስኑ ያስቻለ ስርዓት ነው ፡፡ ሲጠቃለል ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ ስርዓታችን ባለፉት 25 ዓመታት በፖለቲካ፣በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች ሃገራችን ከነበረችበት የቁልቁለት ዕድገት አውጥቶ ሽቅብ እንድትወጣ ያደረገ ስርዓት ነው ፡፡ የድህነት ተምሳሌት በመሆን በድህነትና ኋላ ቀርነት ማዕበል ስትናወጥ የነበረችውን ሃገራችን አረጌውን ታሪክ በመቀየር በፈጣን የዕድገት ባቡር እንድትጓዝ ያስቻለ ስርዓት ነው ፡፡ የድህነት ውቅያኖስን በዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መስመር እየቀዘፈ በዕድገት ገናና ሃገር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ያለ ስርዓት ነው ፡፡ በሃገራችን እየታየ ያለ ስኬትም ትክክለኛ የሆነ መስመር ፣ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ስለ ተረጋገጠና የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ስለተረጋገጠ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምክንያታዊ ካለመሆን የተነሳ በሃገሪቱ ያለውን ተጨባጭ እውነታ የማጣጣል ፣ የመጡ ለውጦችን እና ፈተናዎችን ሚዛናዊ ሆኖ በምክንያታዊነት ያለመረዳት ፣ለመረዳት ያለመፈለግ ፣ ጨለምተኛ አስተሳሰብ የመያዝ እንዲሁም ለውጡን የመካድ አዝማምያ ይታያል ፡፡ እዛም እዚህም የሚታዩ አለመግባባቶችን ከስርዓቱ የመነጩ ናቸው የሚል የተሳሳተ አመለካከት የመያዝ ፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ትሩፋቶችን የማንኳሰስ አባዜ ይታያል ፡፡ በየአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮች በውስጣችንና በውጪ ባሉ ጥገኛ ሃይሎች መፈጠራቸው ባይካድም ረጋ ብሎ ሁኔታዎችን መተንተን ፣ ትርፉና ኪሳራውን በብቃት ያለማስላት ፣ ወገንና ጠላትን በበስለት ያለመለየት ፣የጥገኞች ጉዳይ የህዝብ ጉዳይ እንዳልሆነ ፣ጥገኞች በየትኛው አካባቢ በብሄር ስም ለመነገድ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጪ ከያዙት አለማ አንጻር የሚወክሉት ብሄርም ህዝብም እንደሌለ አንድ ምክንያታዊ ሆነ ዜጋ ማሰብ ይኖርበታል ፡፡ ይገባልም ፡፡እናም በአንድ አካባቢ ችግር ሲከሰት ከችግሩ በስተጀርባ ያለው ማነው ? ለምንድነው እንደዚህ አይነት ፍላጎትና አድራጎት ሊኖረውና ሊፈጽም የቻለው ? በሚል መንፈስ መድረኩ በሚጠይቀው የዴሞክራሲያዊ የትግል አስተሳሰብ በመጠቀም እንዴት መመከት ይቻላል ብሎ ማሰብ ፣መተንተን ፣ጠላትን ከወዳጅ ፣ ህዝብና ጥገኞች ፣ድርጅትና በውስጡ የሚገኙ ጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎችን በህግጋተ-ምክንያታዊነት መለየት ፣መታገል እና የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ማጎልበት ይኖርበታል ፡፡ በተለይ የህዳሴው ወጣት በእንዲዚህ አይነት ሁኔታና አጋጣሚ ንፋስ ሽው ወዳለበት በአንድ ሴኮንድ ሽው ሳይል እውነተኛውና የጥፋት ፕሮፖጋንዳዎችን መለየት ፣እንደየ አመጣጣቸው ህጋዊ ፣ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ የትግል አግባብ በሃሳባዊ ትግል መመከት ይሮርበታል ፡፡ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች እየታየ ያለው አደገኛ አዝማምያም ምክንያታዊ ሆኖ የመቅረብ ጉድለት ይታያል ፡፡ መንግስት የዜጎች ደህንነት መጠበቅ አለበት ፣ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መስራት አለበት ፣ ወንጀል ፈፃሚዎችን በህግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብሎ ማንሳት ተገቢ ነው ፡፡ ነውር የለውም ፣የነበረ ፣ያለ እና መኖርም ያለበት ነው ፡፡ መንግስት እያደረገው ያለውም ይሄው ነው ፡፡ በአንፃሩ በሩዋንዳ የተከሰተውን የሁቱሲና ተቱሲ ዓይነት እልቂት እንዲፈጸም የሚቀሰቅሱ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችና ብሎጎሮች ግን የጥፋት ሰባኪዎች ናቸው ፡፡ አንዱን ብሄር በሌላው እንዲያምጽ ፋኖ ተሰማራ ፣ክተት ብለው የክተት ጥሩንባ የሚነፉት ሃይሎች እየገናባነው ባለው የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፈንጅ እያጠመዱበት መሆናቸውን መውሰድ ይኖርባቸዋል ፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ወጣት አለም በግሎባላይዜሽን ህግጋት አንድ መንደር ለመሆን እየተገደደችበት ባለበት ሁኔታና በሃገራችን ደግሞ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ በሄርን ከብሄር ፣ህዝብን ከህዝብ ለያፋጅ የሚችል ስሜታዊ ቅስቀሳ መቀስቀስ ጠቃሚም ተገቢም አስተማሪም አይደለም ፡፡ የወጣቱ ስራ ጥገኞች የፈፀሙትን ስህተት በስህተት ማረም ሳይሆን ምክንያታዊ በሆነና ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ትግልን በመከተል መታገል ፣ማጋለጥ ፣ ወንጀል አድራጊዎችንና እና ተባባሪዎቻቸው የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ጠባቂ መላእክት በሆነው የተጠያቂነት መርህ እንዲጠየቁ ማድረግ መሆን አለበት ፡፡ ጠባብነትንና ትምክህትን የምንዋጋው በሌላኛው መልክ የጠባብነትና የትምክህተኝነት መንገድ ሳይሆን በአብዮታዊ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ትግል ነው ፡፡ ጠባብነትና ትምክህት የምንዋጋው አፈ-ሙዝ አንስተን ፋኖ ተሰማራ ብለን ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው ፡፡ ጠባብነትና ትምክህተኝነት ለመዋጋት በህገ-ወጥ መንገድ መታገል ማለት የሚፈልገውን የፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ለም መሬት ሆንለት ማለት ነው ፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ስሜታዊ ከመሆን ፣በስሜት ከመደግፍና ከመቃወም ወጥቶ በምክንያታዊነት ማመን ፣ የምክንያታዊነትን ህግጋት ማክበርና ማስከበር በዚህም የስርዓቱ ነቀርሳ ሆኑትን የጠባብነትና ትምክህተኝነት አመለካከትን በብስለት መታገል ይኖርበታል ፡፡ ክፍል 2 ይቀጥላል ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy