POLITICS

ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው፣ ነግ እልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነው

By Admin

July 04, 2016

የብዝሃነት አገር ሆና ነገር ግን ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ አቅቷት የጥንታዊ ስልጣኔ ቦታዋን ለቅቃና በማሽቆልቆል ጉዞ ተጉዛ ከብተና አፋፍ ደርሳ የነበረችው አገራችን ኢትዮጵያ፣ ህዝቦቿ በእልህ አስጨራሽ የዘመናት ትግል በከፈሉት መስዋእትነት እነሆ ዛሬ በህዳሴ ጉዞ ወደ ነበረችበት የስልጣኔ ማማ ለመውጣት የከፍታ ጉዞ ጀምራለች፡፡

በዚህ የትግልና የድል ጉዞ ዛሬ በማክበር ላይ የምንገኘው የብአዴን የ35 አመታት የፅናት፣ የትግልና የድል ጉዞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለውና ደማቅ ታሪክ የተፃፈበት ሆኖ ይገኛል፡፡ የአገራችን ህዝቦች የረጅም ጊዜ የጸረ ጭቆና ትግል የየካቲት 1966ን መሬት አንቀጥቅጥ አብዮት አስከትሎ የፊውዳል ስርዓቱን ማስወገድ የተቻለ ቢሆንም፣ ደርግ ትግሉን የሚመራ መሪ ድርጅት አለመኖሩን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ የህዝቡን አብዮታዊ ትግል አኮላሽቶ በኃይልና በጉልበት ስልጣን ላይ በመውጣት የአፈና ስርአቱን በህዝቦች ላይ በመጫን ታሪክ የማይረሳው ወንጀል መፈፀሙ አይዘነጋም ፡፡

ይህንኑ ተከትሎም መቼውንም ቢሆን ጭቆናን አሜን ብለው የማይቀበሉት የአገራችን ህዝቦች፣ ትግላቸውን አጠናክረው በመቀጠል በአምባገነናዊ ስርአት መቃብር ላይ የዴሞክራሲዊ ስርአት መሰረት ለመጣል ያስቻላቸውን ተጋድሎ አካሄዱ፡፡ የመሪ ድርጅት አስፈላጊነት ጐልቶ በወጣበት በዚያ የትግል ዘመን ደርግን ለመታገል ቆርጠው ከተነሱት ውስጥ አንዱ ኢህአፓ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ፓርቲው ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ አግኝቶና ትግሉም በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀጣጥሎ አምባገነኖች የሚይዙት የሚጨብጡት አስኪያጡ ድንጋጤ ውስጥ አስገብቷቸው የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

ቆራጥ የህዝብ ልጆች ከፍተኛ ጀብዱ በመፈጸም ትግሉን በጋለ ወኔና ስሜት ይዘው መጓዝ ቢችሉም የኢህአፓ አመራር ህዝባዊ ትግሉ በአጭር ጊዜ የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ ብቻ በማየት በስሜትና በተሳሳተ ግምገማ ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ ቋምጦ በተከተለው የተዛባ መስመርና የተሳሳተ የትግል ስልት ምክኒያት ራሱን በራሱ አዳክሞ የት ይደርሳል የተባለውን ህዝባዊ ትግል አደጋ ላይ ጥሎታል። አምባገነኖችም ሁኔታውን ተጠቅመው የበርካታ ንጹሃን ዜጎችን ህይወት በመቅጠፍና ለአሰቃቂ እስራትና ግርፋት በመዳረግ ትግሉ ውጤት ሳያስከትል በአገራችን ህዝቦች የጸረ ጭቆና ትግል ላይ ትልቅ ጠባሳ ትቶ አልፏል፡፡ ህዝባዊ ትግሉ ተስፋ ቆራጭነትና ጨለምተኝነት በተላበሰበት በዚያን ወቅት ነው ከኢህአፓ የወጡ ጥቂት ቆራጥና ፅኑ የህዝብ ልጆች “ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው፣ ነግ እልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነው” ብለው የጭቁን ብሄሮችና ብሄረሰቦች አታጋይ ድርጅት የሆነውን ኢህዴን የመሰረቱት፡፡