ኢትዮጵያና ካናዳ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የካናዳ ዓለም አቀፍ የትብብር ልማት ሚኒስቴርና የፓርላማ ጸሃፊ ካሪና ጎልድን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያና ካናዳ ከልማት ትብብራቸው በተጨማሪ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል።
ካናዳዊያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነባ ያለው የኢንዱስትሪ መንደር ባለሃብቱን በቀላሉ ወደ ስራ እንዲገባ የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአገሪቱ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ማበረታቻም ባለሃብቱን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የካናዳ መንግስትም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ተናግረዋል።
ካናዳ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ለገጠማት ችግር ላደረገችው ድጋፍና እርዳታም ዶክተር ቴድሮስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው የኢኮኖሚ እድገት የሁለቱን አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በር ይከፍታል ያሉት ደግሞ ሚስስ ካሪና ናቸው።
ወደ አገራቸው ሲመለሱ በኢትዮጵያ ያለውን የተመቻቸ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንደሚያስረዱም ቃል ገብተዋል።
በመጪው ህዳር ወር በሚካሄደው አፍሪካ ካናዳ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና ተሞክሮ እንደሚዳሰስም ተናግረዋል።።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት የካናዳ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያም በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና መመረጧ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ካናዳም በዚሁ ዙሪያ አብራ ትሰራለች ብለዋል።
ካናዳ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ እርዳታ ከምታደርግላቸው አገራት መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ነች።
የኢትዮጵያና የካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው ከዛሬ 50 ዓመት በፊት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የካናዳ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የፖታሽየም ምርት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ምንጭ፦ ኢዜአ