Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከኢህአዴግ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

0 1,200

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከኢህአዴግ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

ከኢህአዴግ ጉባኤ ቀጥሎ ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆነው የኢህአዴግ ምክር ቤት ከነሃሴ 18 – 22/2008 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የቀረበውን የ15 አመት የአገራዊ ህዳሴ ጉዞ ግምገማ መነሻ በማድረግ በጥልቀት የገመገመ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በምንገኝበት ወቅት የሚታዩ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ዝንባሌዎችንም የሚመለከት ግምገማ አካሂዷል፡፡

ምክር ቤቱ አገራችን ለ15 አመታት የተጓዘችበትን ሂደት በዝርዝር በመገምገም ሂደቱ መላ የአገራችን ህዝቦች በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅታችን እየተመሩ በሁሉም የህይወት መስኮች አንፀባራቂ ድሎች የተጎናፀፉበት አንደነበር አረጋግጧል፡፡ በዴሞክራሲ፣ በልማትና በሰላም አጀንዳዎች ዙሪያ በተካሄደው አገራዊ የተሃድሶ እንቅስቃሴ አገራችን በብዙ እርምጃዎች ወደፊት ተጉዛለች፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በአንድ በኩል ከአገራዊው እድገቱ ጋር ተያይዘው የተቀሰቀሱ አዳዲስ የህዝብ ፍላጎቶች በመኖራቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከራሳችን አመራር ጀምሮ በሚፈፀሙ ድክመቶች የተነሳ የህዝብ ቅሬታ መበራከት የታየበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ የተነሳ ልማታችን በፈጠራቸው አዳዲስ የህዝብ ፍላጎቶችና በጊዜ ባልተፈቱ የልማት ጥያቄዎች ሳቢያ አሳሳቢና ፈጣን ለውጥ ማምጣትን የሚጠይቅ ሁኔታ የተበራከተባት ሆናም ትገኛለች፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን ኢህአዴግ ህዝቡን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩ ዙሪያ መርቶ እያታገለ ለከፍተኛ ለውጥ ያበቃውን ያክል ዛሬም እየተፈታተኑት የሚገኙትን እነዚህን ችግሮችን በህዝቦች ተሳትፎና ወሳኝ ሚና እያስተካከለ በመጓዝ ጅምሩን የለውጥ ሂደት አጠናክረን ዳር ልናደርሰው ይገባል ብሎ ያምናል፡፡

ከ15 አመታት በፊት ድርጅታችን የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አገራችን አስተማማኝ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ የተረጋገጠባት አገር ከመሆኗም በላይ አለምን ባስደነቀ ልማታዊ ፍጥነት ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ ዴሞክራሲያችን ስፋትና ጥልቀት እያገኘ ተጉዟል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደትም በተቀመጠለት አቅጣጫ ቀጥሏል፡፡

በኢኮኖሚው መስክ በተከተልነው ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ አገራችን ላለፉት 13 አመታት በአለማችን ፈጣን እድገት ከሚያመጡ አገሮች አንዷ ልትሆን በቅታለች፡፡ መሬት የመንግስት ሆኖ አርሶ መጠቀም ለሚፈልግ ሁሉ በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲያለማ በመደረጉ አገራዊ የግብርና ምርታችን ከተሃድሶው መጀመር በኋላ ብቻ በአራት እጥፍ አድጓል፡፡ መላ የአገራችን አርሶ አደሮች በተከበረላቸው የምርት ነፃ ተጠቃሚነት መብት የተነሳ በገጠር የተካሄደው ልማት ተጠቃሚ አርሶ አደሩና ቤተሰቡ ሆነዋል፡፡ በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተካሄደ ልማታዊ እንቅስቃሴም የአገራችን አርብቶ አደሮች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የእድገት ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡ በከተሞች ከአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት እስከ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚዎች መሆን ጀምረዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በየጊዜው በሚመዘገቡ ስኬቶች ወደፊት ስትራመድ የቆየች ብትሆንም ከዚሁ ስኬት ጋር የተያያዙ ተጨማሪ አዳዲስ ፍላጎቶች የተፈጠሩባትና ምላሽ የሚሹ የህዝብ ጥያቄዎች ያሉባት አገርም ሆናለች፡፡ በ25 አመታት ጉዞዋ ከሞላ ጎደል በእጥፍ ያደገው የህዝባችን ቁጥር የህብረተሰባችንን ታዳጊ የመሻሻል ፍላጎት በመጠንም በአይነትም ማርካትን ተጨማሪ ስራ የሚጠይቅ አድርጎታል፡፡ ከህብረተሰባችን 29 በመቶ የሆኑትን ወጣቶች እንዲሁም የህብረተሰባችን ግማሽ የሆኑትን ሴቶችን ፍላጎት ማርካት ብቻ እጅግ ብዙ ስራዎችን በፍጥነትና በፍትሃዊነት ማከናወን የግድ የሚል ሆኗል፡፡ ትምህርት በአገራችን ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ ታዳጊ ጥያቄዎች እየበዙ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ አርሶ አደራችን በገበያ ቅኝት የሚያመርት እየሆነ በሄደ ቁጥር እየሰፋ የመጣውን ልማታዊ ጥያቄ ለማሟላትም ፋታ የማይሰጥ ሆኗል፡፡

ከተሞቻችን ወርድና ስፋታቸው በጨመረና በውስጣቸው ያሉ ነዋሪዎች ፍላጎታቸው ባደገ ቁጥር ይህን እርካታ በሚፈጥር ደረጃ መስራት ከባድ ጥረትና ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ በዚህ ላይ አገራችን ብዙ ሃብት የሚፈጠርባት እየሆነች ባለችበት በዚህ ወቅት ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየሰፋ የመጣው ሙሰኝነትና ብልሹ አሰራር በመንግስት የማስፈፀም አቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ በመሄዱ የህዝባችንን ፍላጎት ለማርካት ተጨማሪ ፈተና የሚደቅን ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም እናንተኑ የሃገራችንን ህዝቦች በስፋት በማሳተፍ የፀረ ሙስናና ብልሹ አሰራር ትግል ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጎልበት እንዳለብን ምክር ቤቱ ያምናል፡፡ ይህም በቂ ዝግጅት ተደርጎ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ምክር ቤቱ በሙሉ ስምምነት ወስኗል፡፡

የድርጅታችን ምክር ቤት ባለፉት 15 አመታት በተጓዝንበት የተሃድሶ ሂደት የተመዘገቡ ለውጦችንና ያጋጠሙ ድክመቶችን በዝርዝር ከገመገመ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ዋነኛው የስርዓታችን ፈተና ለመንግስታዊ ስልጣንን ያለን እይታ የተዛባ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ይህም ስልጣንን የራስ ኑሮን መሰረት፣ የግል ጥቅም ማስከበሪያና የሃብት ማከማቻ እንዲሆን አድርጎ ከመመልከትና ከመንቀሳቀስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ ይህ ዝንባሌ ከመንግስት አልፎ በድርጅታችን ላይም የራሱን ተፅዕኖ በማሳደሩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራሞቻችንን በውጤታማነት ተግባራዊ የማድረግ ችሎታችንን ለብዙ ፈተናዎች እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ምክር ቤታችን በመንግስት ስልጣን አጠቃቀም ዙሪያ የተከሰተው ጉድለትና የዚህ መገለጫ የሆኑ አስተሳሰቦችን በአግባቡ ታግሎ ለማስተካከል ከ15 አመት በፊት ለተጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄያችን አዲስ ስፋትና ጥልቀት በመስጠት ወደተሟላ የለውጥ ንቅናቄ መሸጋገር እንደሚገባ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ ተሃድሷችን በአዲስ ስፋትና ጥልቀት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የወሰነው በአንድ በኩል በ15 አመታት የተሃድሶ ንቅናቄያችን የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ በሌላ በኩል አዳዲስ የተፈጠሩ የህዝብ ፍላጎቶች ደረጃ በደረጃ ምላሽ መስጠት እንደሚገባና በጊዜ ባልታረሙ ድክመቶች ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችንና የህዝብ ቅሬታዎችን በተሟላ ሁኔታ ለመቅረፍ እንዲቻል ነው፡፡ ይህ ስራ በድርጅታችን ውስጥ በሚካሄድ ትግል ብቻ ሊስተካከል እንደማይችል ሁሉ ህዝቡ በተናጠል ብቻውን በሚያካሂደው ትግልም የሚፈለገውን ለውጥ ሊያስመዘግብ እንደማይችል ይገነዘባል፡፡ ለውጡ የተሟላና ህዝብን የሚያረካ ሊሆን የሚችለው በጋራ ትግል ሲፈፀም ብቻ ነው፡፡ ምክር ቤታችን ለተሃድሶ ንቅናቄያችን ስፋትና ጥልቀት በመስጠት ለመጓዝ የወሰነው ከህዝባችን ጋር በተባበረ ትግል በከባድ መስዋዕትነት ያስመዘገብናቸውን ድሎች ለማስፋትና ለማጎልበት፣ ድክመቶቻችንን ደግሞ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ ነው።

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች !

በአገራችን ተግባራዊ የተደረገው ፌዴራላዊ ህገ መንግስታዊ ስርዓት የብሄሮችን፣ የብሄረሰቦችንና የህዝቦችን እኩልነት ያረጋገጠ ስርዓት ነው፡፡ የሚገነባው ስርዓት በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባትና አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለመ ሲሆን ባለፉት የታሪክ ሂደቶች የተፈጠሩ የታሪክ እሴቶችን በማጠናከር የተዛቡ ግንኙነቶችን ደግሞ በማረም ላይ የተመሰረተ መሆኑም ለማንም ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ባለፉት 15 የተሃድሶ አመታትም ሆነ ቀደም ባሉት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጊዜያት የአገራችን ህዝቦች በመካከላቸው ዴሞክራሲያዊ አንድነትን እያጠናከሩ እጅ ለእጅ ተያይዘው የጋራ ፕሮጀክታቸው የሆነውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ጀምረዋል፡፡

በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለው ይህ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ለዘመናት በማሽቆልቆል ሂደት ውስጥ ያለችውን አገራችንን በልዩ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ለዜጎችና የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች አሳዛኝ ህልፈት ምክንያት የሆኑ ግጭቶች የተከሰቱ ቢሆንም፣ አገራችን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ጥንካሬና ምቹ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ምቹ ሁኔታ በአሁኑ ገዜ በስርዓቱ ውስጥ ጎልቶ በመታየት ላይ ያለውን በመንግስት ስልጣን ካለአግባብ የመጠቀም አዝማሚያ በመግታት ይበልጥ እንዲጠናከር ለማድረግ ከተቻለ አገራችንን በርግጥም ወደ አዲስ ከፍታ ልናወጣት እንደምንችል ይታመናል፡፡

ምክር ቤቱ ከዚህ በመነሳት የተከሰቱ ድክመቶችን በማረም ልማታችንና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ይቻል ዘንድ ለተሃድሷችን ስፋትና ጥልቀት በመስጠት ልንጓዝ እንደሚገባን ወስኗል፡፡
ምክር ቤቱ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደርና በአጎራባች የትግራይ ወረዳ መካከል ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ በተነሳው ጉዳይ በህወሓትና ብአዴን አመራር በኩል መፍትሄ ከመስጠት አኳያ የተከሰተው መዘግየት ተገቢ እንዳልሆነ በመገምገም ሁለቱ ድርጅቶች ከዚህ ድክመት ተላቀው ፈጣንና ህዝብን ማዕከል ያደረገ መፍትሄ እንዲሰጡ ወስኗል፡፡ በትግራይ ክልል ከወልቃይት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ እንዲታይ ወስኗል፡፡ እነዚህና ለግጭት መነስኤ የሆኑ ወቅታዊ ገዳዮችም ከህዝብ ጋር በመመከከርና በመግባባት እንዲሁም የህግ የበላይነት በተከበረበት አኳኋን እንዲፈታ መደረግ እንዳለበትም ወስኗል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች !

በጥረታችሁና በድካማችሁ የአገራችን እድገት እንዲፋጠንና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አድርጋችኋል፡፡ ድርጅታችንና ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ድክመት ሲያጋጥማቸውም ለማስተካከል ብርቱ ጥረት አድርጋችኋል፡፡ ይሄው ያልተቆጠበ ጥረታችሁ ውስጣዊ ችግሮቻችንን እንድናይና በፍጥነት ማስተካከል እንድንችል ረድቶናል፡፡ አሁንም የመልማት ፍላጎታችሁን ለማሳካትና የምታነሷቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታች ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በመሆኑም በአንድ በኩል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ በመታገል የላቀ ሚናችሁን እንድትጫወቱ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የከተማ ነዋሪዎችና ባለሃብቶች !

የሀገራችን ከተሞች በከፍተኛ ለውጥ ውስጥ መግባት የቻሉት ከድርጅታችንና ከመንግስት ጎን ሆናችሁ ባደረጋችሁት ርብርብ ነው፡፡ ዛሬ ከተሞችና በከተሞች ያለው ለውጥ በላቀ ደረጃ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ይሁንና የከተማ ነዋሪዎች በአጠቃላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ተዋናዮች እንዲሁም በየደረጃው በኢንዱስትሪ ልማት ላይ የተሰማራው ባለሃብት በተለይ የተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ እንደሆናችሁ እንገነዘባለን፡፡ በየጊዜው የሚያጋጥማችሁን ችግር ለድርጅታችንም ለመንግስትም ለማሳወቅ ያደረጋችሁትን እንቅስቃሴ ምክር ቤቱ ያደንቃል፡፡ እስካሁን ምላሽ መስጠት የተጀመረባቸውን ጉዳዮች ይበልጥ ለማስፋትና፣ መፍትሄ ያላገኙ ችግሮችን ለመቅረፍም ድርጅታችን ቁርጠኛ አቋም በያዘበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን በሚያደርገው የጠለቀ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ድርሻችሁን በመወጣት የተጀመረውን መልካም አስተዳደር የማስፈንና ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲን የማረጋገጥ ጉዟችንን እንድታስቀጥሉ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ወጣቶችና ሴቶች !

ድርጅታችን ኢህአዴግና ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የወጣቶችንና የህብረተሰቡን ግማሽ ክፍል የሚሸፍኑትን ሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ግልፅ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም ማስፈፀሚያ የእድገት ፓኬጆችን ቀርፆ ርብርብ በማድረጉ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይሁንና በገነባናቸው ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶችና ሌሎች ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ወጣቶች በስራ ለመሰማራት እየፈለጉ ያልተመቻቹላቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ምክር ቤቱ አፅንኦት ሰጥቶ ተወያይቶበታል፡፡ በመሆኑም የወጣቶችንና የሴቶችን ቀጥተኛ ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን በፍጥነት ወደ ስራ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደሚገባና ሌሎች ወጣቱን የሚመለከቱ ጥያቄዎች በአግባቡ መፍትሄ ለመስጠት ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ የምክር ቤቱን ውሳኔ ለመተግበርም ድርጅታችንና መንግስት በሚያደርጉት ሰላምን የማስከበር፣ ዴሞክራሲን የማስፋት እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቦላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን የፀጥታ ሃይሎች !

ባለፉት አመታት በአገራችን አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆን በህዝባዊነት መንፈስ ለፈፀማችሁት አኩሪ ተጋድሎ ምክር ቤቱ አክብሮቱን ይገልፃል፡፡ በቅርቡም በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለማስወገድ የከፈላችሁትን የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ምክር ቤቱ በአድናቆት ይመለከተዋል። አሁንም በጥረታችሁና በከፈላችሁት መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩትን ሃይሎች የተለመደው ህዝባዊ ባህሪያችሁ ሳይለያችሁ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዘብ እንድትሆኑ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

በመጨረሻም የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወዳችሁና ፈቅዳችሁ የመሰረታችሁት ህገ መንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርዓት እንዳይሸራረፍ በዴሞክራሲ አንድነት መርህ ላይ ተመስርታችሁ ህግና ስርዓት እንዲከበር እንዲሁም የተጀመረውን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት እንዲቀጥል ብሎም ያነሳችኋቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ድርጅታችንና ልማታዊ መንግስታችን ከጎናችሁ ቆሞ እንደሚረባረብ እየገለፅን እንደተለመደው እጅ ለእጅ ተያይዘን የጀመርነውን የህዳሴ ጉዞ እንድናሳካ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ህዝባዊነታችን ለህዳሴያችን !
ክብርና ሞገስ ለትግላችን ሰማዕታት !

የኢህአዴግ ምክር ቤት
ነሃሴ 22 ቀን 2008 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy