ዶ/ር ዘውድነህ በየነ ኃይሌ፣ የግልግል ዳኝነት ሕግ ኤክስፐርትና ዓለም አቀፍ ጠበቃ
ዶ/ር ዘውድነህ በየነ ኃይሌ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ጠበቃ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ ሁለት የዶክትሬት ዲግሪዎች ያሏቸው ሲሆን፣ አንደኛውን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ከሚገኘው በርክሌ ዩንቨርሲቲ ሁለተኛውን ደግሞ
ሩሲያ ከሚገኘው ሞስኮ ስቴት አካዳሚ ኦፍ ሎው አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የማስተርስ ዲግሪ (ኤልኤልኤም) እንዲሁም ሌላ ማስተርስ ዲግሪ በኢንተርናሽናል ኤንድ ኤርያ ስተዲስ ተከታትለዋል፡፡ በሁለቱ የዓለማችን አንኳር የሕግ ሥርዓቶች ማለትም በሲቪል ሎውና በኮመን ሎው የሠለጠኑት ዶ/ር ዘውድነህ በተለያዩ የሕግ ትምህርት ቤቶች በቋሚነት ያስተምራሉ፡፡ የጥብቅና ፈቃድ ባገኙባትና መቀመጫቸውን ባደረጉባት ኢትዮጵያ በፌዴራል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች፣ እንዲሁም በሰበር ሰሚ ችሎቱ ይዘዋቸው በሚቀርቧቸውና በተከራከሩባቸው ትልልቅ ጉዳዮችም ይበልጥ ይታወቃሉ፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ በድርድርና ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነቶች የመንግሥት ኤጀንሲዎችንና በመንግሥት ባለቤትነት የማተዳደሩ ኢንተርፕራይዞችን በአፍሪካ፣ በእስያና በአውሮፓ በመወከል ተከራክረዋል፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ በዓለም አቀፍ ክርክሮች ኤክስፐርት ምስክር ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ ኤክስፐርት ሆነው የሚሠሩባቸው የሕግ ዘርፎች መካከል ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት፣ የመንግሥት ግንኙነቶች፣ የመንግሥት ውል፣ የኮንስትራክሽን ሕግ፣ የኮርፖሬት ሕግ፣ የፕራይቬት ኢኩቲና ሌሎች የኢንቨስትመንት ሕጎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በነዳጅና በጋዝ፣ በማዕድን፣ በማሪታይም፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የአፍሪካ መንግሥታት በተሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነቶች በዋና አማካሪነት ሠርተዋል፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በትምህርት ተቋማት፣ ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶችና ኮርፖሬሽኖች የቦርድ አባል ሆነውም አገልግለዋል፡፡ የወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም የሕግ የበላይነት ዓለም አቀፍ አማካሪዎች አባል በመሆንም ሠርተዋል፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ መቀመጫውን ያደረገው የአዲስ ሎው ግሩፕ ኤልኤልፒን ከመሠረቱ ሁለት ግለሰቦች አንዱ ሲሆኑ፣ በዋና ተጠሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር ዘውድነህ በአዲስ አበባ የሚገኘው የዶ/ር ዘውድነህ በየነ ኃይሌ የሕግ ቢሮ ዋና ተጠሪና የኢማሂዜ ዓለም አቀፍ አማካሪ ጥምር መሥራች ናቸው፡፡ ሰለሞን ጐሹ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነትና የኢትዮጵያ ተሞክሮ ላይ ከዶ/ር ዘውድነህ ጋር በእንግሊዘኛ በኢሜይል ቃለ ምልልስ አድርጓል በአማርኛ እንደሚከተለው ተርጉመነዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ኢትዮጵያ ያላትን ተጋላጭነትና ልምድ እንዴት ይገመግሙታል? በውጤትስ ረገድ የተመዘገበው ሪከርድ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- ከታሪክ አንፃር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ያላት ልምድ የተቀላቀለ ውጤት የተመዘገበበት ነው፡፡ ሪከርዷ እንደሚያሳየው ሙሉ በሙሉ ያሸነፈችባቸው ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል የሚያበሳጩ ውጤቶችም ተገኝተዋል፡፡ ከሚታወቁ ቀደምት ጉዳዮች ውስጥ በአንዱ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሊወድቅ አካባቢ የማዕድን ሚኒስቴር በደል ደርሶብኛል ብሎ ቅሬታ ያቀረበውን በኃይድሮ ካርቦን ፍለጋ ተሰማርቶ የነበረውን የአሜሪካውን ባሩች ፎስተር ኮርፖሬሽንን በሚገባ አሸንፏል፡፡ በሌላ ታዋቂ በሆነ ጉዳይ ሳሊኒ ኮንስትሩቶሪ ኤስፒኤ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር እ.ኤ.አ. በ2001 ባደረገው ክርክር ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ ሰለባ ሆናለች፡፡ ችሎቱ ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ለግልግል ዳኝነት የመረጡት ቦታ አዲስ አበባ ቢሆንም፣ ጀብደኝነት የተንፀባረቀበት የሕግ ንድፈ ሐሳብ ክርክር በማቅረብ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ወደ ጎን በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የማዕድን ሚኒስቴር ባስመዘገበው ግሩም ውጤት የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥትን በእነዚህ መድረኮች መገዳደር ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ሆኗል፡፡ የግልግል ዳኝነቱ መቀመጫውን ጀኔቫ ባደረገው ችሎት የተካሄደው ፔትሮትራንስ ኩባንያ በኢትዮጵያ የነበረው የኃይድሮ ካርቦን ይዞታ የተሰረዘው ያለአግባብ ነው በሚል ቅሬታ በማቅረቡ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ማዕድን ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጋር ጥልቅና ሥር የሰደደ ግንኙነት ያላቸው የጥብቅና ድርጅቶች መከላከያውን እንዲመሩ ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ እምነት በማሳደሩ፣ ኢንቨስተሩ ያቀረበው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ይገባኛል ጥያቄ ውድቅ ሆኗል፡፡ ከኢንቨስትመንት ስምምነት ጋር በተያያዘ የግልግል ዳኝነት በማውቀው ብቸኛ ጉዳይ ካምፓግኒ ኢንተርናሽናል ዲ ሜንቴናንስ የተሰኘው ኩባንያ ከኢትዮጵያ ጋር እ.ኤ.አ. በ2009 ባደረገው ክርክር ችሎቱ ትክክለኛ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ኩባንያው የጠየቀው የንግድ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ ፈረንሣይና ኢትዮጵያ ባደረጉት የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ለ‹‹ኢንቨስተር›› የተሰጠውን ትርጉም አያሟላም በሚል ውድቅ ተደርጎበታል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በዳኝነት ሥልጣን ደረጃ አሸናፊ ሆናለች፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት እጅግ አስቸጋሪ መሰናክሎች መኖራቸው ባይካድም ኢትዮጵያ አግባብነት የሌላቸው ጥያቄዎች ሲቀርቡባት የመከላከል አቅም እንዳላት አሳይታለች፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የንግድ የግልግል ዳኝነትና የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚገዛው የሕግ ማዕቀፍ በሚገባ የዳበረ ነው ብሎ በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- የውጭ ኢንቨስትመንት የሚገዛ የሕግ ማዕቀፍን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሚያስመሰግን መልኩ ትንሽ የማይባል ጊዜና ሀብት በመመደብ፣ በመሠረታዊ ደረጃ የሕግ ድንጋጌዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላቸው አሠራሮች ጋር እንዲጣጣሙ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ የንግድ የግልግል ዳኝነት ጋር በተያያዘ ደግሞ በአገሪቱ ያሉት ሕጎች በንጉሡ ጊዜ በወጡ መሠረታዊ የሕግ መጻሕፍት ውስጥ የተካተቱ መሆናቸው ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡ ከዚያ በኋላ ክለሳ አልተደረገባቸውም ወይም አልተሻሻሉም፡፡ አስፈላጊ የሆኑት ድንጋጌዎች ዘመናዊ የሚባሉ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ከወጡ የጊዜው ዕድገቶች ጋር ግን አይጣጣሙም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ለግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ዕውቅና የሚሰጥና የሚፈጸሙበትን መንገድ የሚያስቀምጥ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሕግ ካላቸው አገሮች አንዷ ነች?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- ከላይ እንዳልኩት በአጠቃላይ የግልግል ዳኝነትን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ያሏቸው በ1952 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግና በ1957 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ዘመናዊ የሚባሉ ቢሆንም፣ የተሟሉና አሁን ዓለም የደረሰበትን የሕግ አተያይ የሚያንፀባርቁ አይደሉም፡፡ የዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት አፈጻጸምን በተመለከተ ወርቃማው የአሠራር ደረጃ የሚገኘው እ.ኤ.አ. በ1958 ወደ ሥራ በገባው የውጭ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ዕውቅና አሰጣጥ አፈጻጸም ኮንቬንሽን ውስጥ ነው፡፡ በተለምዶ የኒውዮርክ ኮንቬንሽን በመባል ይጠራል፡፡ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር እንዳመለከቱት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ኮንቬንሽኑን ለማፅደቅ ጉዳዮችን እያጤነች ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኮንቬንሽኑ ተቀባይ ከሆነች ምክር ቤቱ የሚያወጣው የማስፈጸሚያ ድንጋጌ የተሟላና የኢትዮጵያን ልዩ ሁኔታዎች ከግንዛቤ የሚያስገባ እንደሚሆን እጠብቃለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- አገሪቱ ለተቋማዊ የግልግል ዳኝነት ዕውቅና የሚሰጡ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ስምምነቶች አባል ነች? የተመድ የግልግል ዳኝነት ድንጋጌዎችንስ ተቀብላለች?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- በመሠረቱ የተመድ የግልግል ዳኝነት ድንጋጌዎች ለተቋማዊ የግልግል ዳኝነት ዕውቅና አይሰጥም፣ ወይም ሕጋዊ መሠረት አይሰጥም፡፡ ይልቁንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዓለም አቀፍ የንግድ ሕግ ኮሚሽን ያወጣቸው እነዚህ ድንጋጌዎች ተከራካሪ ወገኖች በግልግል ዳኝነት ሒደት ውስጥ መርጠው የሚጠቀሙባቸውን ሥነ ሥርዓቶች የያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውሉት በጊዜያዊ የግልግል ዳኝነቶች ነው፡፡ ምክንያቱም የግልግል ዳኝነት ተቋማት የራሳቸውን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ያዘጋጃሉ፡፡ ነገር ግን የአብዛኛዎቹ ተቋማት የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች የተመድ ድንጋጌዎች ከፍተኛ ተፅዕኖ ያረፈባቸው ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1976 ለመጀመሪያ ጊዜ የተደነገጉት እነዚህ የተመድ ድንጋጌዎች እ.ኤ.አ. በ2010 በከፍተኛ ሁኔታ ክለሳ ተደርጎባቸዋል፡፡ ድንጋጌዎቹ ለግልግል ዳኝነት ጥልቅ የሆኑና እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የአሠራር ሥነ ሥርዓቶችን በመያዛቸው ይሞገሳሉ፡፡ የተመድ ድንጋጌዎች ለኮሚሽኑ ሞዴል ሕግ መንታ ጥቅም አላቸው፡፡ ይህ ሞዴል ሕግ በተመሳሳይ ስምምነት አይደለም፡፡ ነገር ግን አገሮች በፓርላማቸው ለሚያፀድቁት ብሔራዊ ሕግ እንደ ሞዴል የግልግል ዳኝነት ሕግ የሚያገለግል ነው፡፡ ለአብነት ያህል በዚያ አገር ውስጥ የሚቀመጡ የግልግል ዳኝነት የሚሰጡ ትራይቡናሎች የሚሰጡት ውሳኔ ውድቅ የሚደረግበት ዝርዝር ሁኔታን ያስቀምጣል፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ ቁልፍ የሆነ ሚና ያላቸው በርካታ አገሮች ይህን ሞዴል ሕግ ወይም የተወሰነ ማሻሻያ የተደረገበትን አፅድቀዋል፡፡ በዚህም ከፖሊሲ አንፃር እጅግ ተፈላጊነት ያለው ወጥ አሠራርን በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሕግ ለማስፈን ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ሕጓን ማሻሻል ከፈለገች ይህ ሞዴል ሕግ ውይይቶችን ለመጀመር አንድ መነሻ ነጥብ ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ከማስተናገዷ አኳያ አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነቶች ከኢትዮጵያ ውጪ የሚካሄዱት ለምንድነው? በኢትዮጵያ ቢካሄዱ ሒደቱ በአንፃራዊነት ዋጋ በመቀነስና ፍትሐዊ ሥነ ሥርዓት በመዘርጋት የተሻለ አይሆንም?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- የዚህ ጥያቄ መልስ በዋነኛነት የሚያያዘው ኢትዮጵያ የኒውዮርክ ኮንቬንሽንን ካለማፅደቋ ጋር ነው፡፡ በኮንቬንሽኑ መሠረት አባል አገሮች የውጭ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎችን ዕውቅና የመስጠትና የማስፈጸም ከባድ ዓለም አቀፋዊ ግዴታ ይሸከማሉ፡፡ ኮንቬንሽኑ አባል አገሮች በሌሎች አገሮች የሚሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ጋ ዕውቅና የሚሰጡትና የሚፈጽሙት እነዚህ አገሮች አባል ከሆኑ ብቻ ነው፡፡ ኮንቬንሽኑን አባል ላልሆኑ አገሮች ተፈጻሚ የሚያደርጉት ግን በስምምነት ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት የግልግል ዳኝነቱ የተከናወነበት ቦታ የሚገኘው እንደ ኢትዮጵያ ባለ አባል ያልሆነ አገር ከሆነ አባል አገሮች ዕውቅና የመስጠትና የማስፈጸም ግዴታ የለባቸውም ማለት ነው፡፡ ይሁንና የግልግል ዳኝነት የመሰማት ሒደትን ከሕጋዊ ቦታው ውጭ በየትኛውም ቦታ ማድረግ ይቻላል፡፡ በሌላ አባባል መቀመጫውን ፓሪስ ወይም ስቶኮልም ያደረገ የግልግል ዳኝነት ትራይቡናል የማስረጃ መስማት ሒደቱን በአዲስ አበባ ወይም በአዳማ ለማድረግ የሚፈልገው ነገር የሁሉም ምስክሮችን በእነዚህ ቦታዎች መገኘት ብቻ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ሕጋዊ ውጤቶቹን አይለውጥም፡፡ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች አፍሪካዊ ተከራካሪ ወገኖች ከፍተኛ ወጪን ለመቀነስ የግልግል ትራይቡናሉ ይህን እንዲያደርግ መጠየቅ ቢችሉ ብልህነት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምሁራን እንደሚከራከሩት አብዛኛዎቹ የግልግል ዳኝነት ጥያቄዎች የሚነሱት የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በአግባቡ ስለማይዘጋጁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ አንፃር እነዚህን ጉዳዮች እንዴት እየመራች ነው?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- ስምምነቶችና ውሎች ሲፈጸሙ ብቃት ያለው የሕግ አማካሪን ማሳተፍ ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሰነዶች ለመፈረም በሚደረገው ድርድር እንዳለመታደል ሆኖ የስፔሻሊስቶችን ዕርዳታ ለማግኘት ያለመፈለግ አዝማሚያ ይታያል፡፡ ይህ በዋነኛነት የሚመነጨው ከሰው ልጅ ባህሪ ክፍተቶች ነው፡፡ የተሳካ አጋርነት በመፍጠር የደስታ ስሜት የተሟላ ሰው ይህ ግንኙነት ወደፊት አስቀያሚ የመሆን ዕድል እንዳለው ችላ የማለት ሥነ ልቦናዊ አዝማሚያ ይታይበታል፡፡ ስለዚህም ለስምምነቱ ይዘት በተለይም ወደ ሕጋዊ ክርክር ስለሚወስዱ ጉዳዮች ሙሉ ትኩረት ያለመስጠት ችግር ይኖራል፡፡ ይህ ዓይነት ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ያለመገመት ቸልተኝነት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የተለመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ዓይነት አዝማሚያ የፀዳች አይደለችም፡፡
ሪፖርተር፡- ከንግድ ጋር በተገናኙ የግልግል ዳኝነት ሒደቶች የብሔራዊ የዳኝነት አካሉ ሚና ምንድነው? የግልግል ዳኝነት ሒደቱን በተመለከተ የተፈጸሙ ስምምነቶችና ውሎችን የመተርጎምና መሠረታዊ ነገሮች ጎድሏቸዋል በማለት ውሳኔዎችን የመከለስ ሥልጣን አላቸው?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- የብሔራዊ የዳኝነት አካሉ ሚና የሚወሰነው በአገሪቱ ሕጎች ነው፡፡ የፍርድ ቤቱ የሥልጣን ወሰንም በእያንዳንዱ ጉዳይ ዝርዝር ሁኔታዎች የሚወሰን ነው፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ሕጎች አገሪቱ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር እንደሚጣጣሙ ይጠበቃል፡፡ ከአገር አገር መጠነኛ ልዩነት ቢኖርም ብሔራዊ ሕጎች የዳኝነት አካሉ በጉዳዮች ጭብጥ ላይ ሳይሆን ሒደቱ ፍትሐዊ መሆኑን የማረጋገጥ ሥልጣን እንዲኖረው እንደሚደነግጉ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በሰፊው ተቀባይነት ያገኙና ምክንያታዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ጠብቀው የመሥራት ፍላጎታቸውን ማሳየታቸው ተስፋ ሰጪ አዝማሚያ ነው፡፡ ትክክለኛና ሕጋዊ የግልግል ዳኝነት ስምምነቶች በውል በሰፈሩባቸው ሁኔታዎች ጉዳዮችን አናይም በማለት በቋሚነት የግልግል ዳኝነት ስምምነቶችን እያስፈጸሙ ነው፡፡ በስምምነቶቹ የግልግል ዳኝነት ውሳኔው የመጨረሻ ውሳኔ ነው ተብሎ በግልጽ ከተቀመጠባቸው ስምምነቶች ጋር በተገናኘ፣ ይግባኝ ሲቀርብላቸውና ጭብጦችን በድጋሚ እንዲያዩ ጥያቄ ሲቀርብላቸውም ውድቅ እያደረጉ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በግልግል ዳኝነት ውሳኔዎቹ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ሲፈጸም ጉዳዩን የማየት ሥልጣን እንዳለው ግልጽ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቶች በግልግል ዳኝነት ሒደት ውስጥ ጣልቃ መግባት ያለባቸው ሒደቱን ውጤታማና ፍትሐዊ ለማድረግ ተሳትፎአቸው እጅግ አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ በቅርቡ የእርስዎ የጥብቅና ድርጅት ከኮንስታ ጆይንት
ቬንቸር ጋር ባደረገው የግልግል ዳኝነት ክርክር ላይ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው በዚህ ምክንያት ነው?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- የሼማን ዴ ፈር ጉዳይ በጣም የሚያበሳጭ ቢሆንም ጉዳዩ በፍርድ ሒደት ላይ ያለ በመሆኑ ስለ ዝርዝር ጉዳዮች አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሰነዶች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካቀረብነው አቤቱታ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ለሕዝብ ይፋ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሰነዶች ጥቂት መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ ክርክሩ ካለቀ በኋላ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ እሰጣለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል የሚችሉ በቂ የተካኑና ብቃት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች አሉ?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- እኔና ባልደረቦቼ ስለዓለም አቀፍ የግጭት አፈታት በኢትዮጵያ በሚገኙ የሕግ ትምህርት ቤቶችና በመላው ዓለም እየተዘዋወርን እናስተምራለን፡፡ በዚህ ሒደትም በኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ብቃትና የመማር ፍላጎት ሁላችንም ተደንቀናል፡፡ የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ሕግ መፃኢ ዕድል ለኢትዮጵያም ሆነ ለተቀረው ዓለም ምን እንደሚመስል መገመት አዳጋች ነው፡፡ ነገር ግን ከንግድ ጋር የተገናኙ የግል የውል ስምምነቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶችን ለመቅረፍ ዋነኛው ተመራጭ መንገድ ዓለም አቀፍ የንግድ የግልግል ዳኝነት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ይኼ በሌላ አሠራር የሚቀየር አይሆንም፡፡ ይህ ሒደት በግልግል ዳኝነት ስፔሻሊስቶች የማይታገዝ ከሆነ፣ በጉዳዩ ላይ የሚሳተፉ የሕግ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ መሠረታዊ ጥቅሟን እንዳታስጠብቅ ያደርጋሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 በኦስትሪያ በቪዬና በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፈውን የኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ቡድን በመርዳቴ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በመጪው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን የሕግ ባለሙያዎች ከፍተኛ ተስፋ አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ከንግድ ጋር የተገናኙ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነቶች መሠረታዊ ችግሮች ተብለው የሚጠቀሱት ምንድን ናቸው? በማደግ ላይ ያሉ አገሮችስ በሒደቱ የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶችና ደስተኛ የማይሆኑባቸው ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- የግልግል ዳኝነት ብቸኛው ዋነኛ ማነቆ የግልግል ዳኝነት ስምምነት በውል ሲፈጸም የሚሰጠው ትኩረት በቂ አለመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የግልግል ዳኝነቱ የሚካሄድበት ቦታ ፓሪስ ወይም ጄኔቫ ሆኖ ሲመረጥ ጉዳዩ ከአፍሪካ ተስቦ ወደ አውሮፓ በጥልቀት ይገባል፡፡ ይኼ ምርጫ የግልግል ዳኝነቱን ማንነት በዋነኝነት ይወስናል፡፡ ቦታው አውሮፓ መሆኑ ሦስት አባላት ባሉት ትራይቡናል ሁለቱ አውሮፓውያን የመሆን ዕድላቸውን ያሰፋል፡፡ መልስ ሰጪው ተከራካሪ የአፍሪካ አገር ሲሆን፣ ከታሪክና ከርዕዮተ ዓለም ጋር በተገናኙ ምክንያቶች የኃይል ሚዛኑ የሚፈለገው ዓይነት አይሆንም፡፡ በተወሰነ ደረጃ አድሏዊነትና ያልተገባ ፍረጃ እንዲሁም ከገንዘብና ከመልካም ስም ጋር የተገናኙ ጥቅማ ጥቅሞችም በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ላይ ጫና ማሳረፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ የአፍሪካ ተከራካሪ ወገኖች የግልግል ዳኝነት ስምምነትን በውል ከማሰራቸው በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ስምምነታቸውን እንዲያጤኑት እመክራለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ሒደቶች ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚያዳሉ ናቸው ይባላል፡፡ በዚህ ግምገማ ይስማማሉ?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ሕግ ችግር በዋነኛነት የሚያያዘው በስምምነቶቹ ይዘት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የውጭ ኢንቨስተር አስተናጋጅ አገሮች ላይ ከሚጣለው የኢንቨስትመንት ጥበቃ ግዴታ ጋር ነው፡፡ እነዚህ ግዴታዎች በአብዛኛው የሚገለጹት በአምታችና ክፍት ቋንቋ በመሆኑ በሰፊው ለመተርጎም ተጋላጭ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ጉዳዩ የፍትሕ ክርክር መሆኑ ቀርቶ የተወሰነ ፍልስፍና የሚከተሉ በቂ የፖለቲካ ካፒታል ያላቸው ልሂቅ የግልግል ዳኞችን በመምረጥ ክርክሩን ለማሸነፍ የምትነሳሳበት መድረክ ይሆናል፡፡ ይህን ችግር ይበልጥ የሚያወሳስበው የቀደሙት የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ለተመሳሳይ ጉዳዮች ተፈጻሚ የሚሆኑበት አስገዳጅ አሠራር አለመኖሩ ነው፡፡ በሌላ አባባል የኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ወጥነት የጎደለው መሆኑ ኢፍትሐዊ ለሆነ አሠራር በር ከፍቷል፡፡ በበርካታ አጋጣሚዎች የአፍሪካ ተከራካሪዎች ወገኖች ያላረካቸውን ውጤት ሲያገኙ አይቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ለአንዳንዶች ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት በቅኝ ግዛት ጊዜ የነበረውን የኢኮኖሚ ብዝበዛ ማስቀጠያ ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ በማደግ ላይ ካሉ አገሮች ከሚመጡ ተከራካሪ ወገኖችና እምነት ለማይጣልባቸው ፍርድ ቤቶቻቸው መከላከያ መሣሪያ ነው፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድነው?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- አንዳንድ እውነታዎች የታሪክ መዝገብ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ክርክር አይቀርብባቸውም፡፡ ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጣ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ የበላይነት አክትሟል፡፡ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በቀድሞ ቅኝ ግዥዎቻቸው የተነገራቸው እውነት ያለው መረጃ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚያስቀምጠውን የኢንቨስትመንት ጥበቃ የማይቀበሉ ከሆነና የማይፈጽሙ ከሆነ፣ በተለይም ከአገሮቹ ውጪ በሚገኙ ቦታዎች የሚካሄዱ የግልግል ዳኝነቶች ለመካፈል ፈቃደኛ ካልሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች እንደማይመጡ እነዚህም የኢኮኖሚ ልማታቸው እንደሚደናቀፍ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ አገሮች የግልግል ዳኝነትን የሚገዛውን ኮንቬንሽን (አይሲኤስአይዲ) በብዛት የተቀበሉት፡፡ ይህ ኮንቬንሽን ሲረቀቅ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓና እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከተደረጉት ድርድሮች ውስጥ አንዱን በአዲስ አበባ ማዘጋጀቷ አሁን ካለው እውነታ ጋር ተቃርኖ አለው፡፡ የመጨረሻውን ሰነድ የወቅቱ መንግሥት የፈረመ ቢሆንም ፓርላማው ስላላፀደቀው ወደ ሥራ አልገባም፡፡ ከአፍሪካ ውጪም ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸሙት የኢንቨስትመንት ስምምነቶች የግልግል ዳኝነት ያስቀመጡት በማደግ ላይ ባለ አገርና በቀድሞ ቅኝ ገዥ መካከል ነው፡፡ ለዚህ እንደ አብነት እ.ኤ.አ. በ1969 የተፈጸመውን የኔዘርላንድስና የኢንዶኔዥያ ስምምነትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በብሔራዊ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎች ከዚያ አገር ውጪ በፍጥነት የማይፈጸሙ በመሆኑ፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ከአፈጻጸም አኳያ ትልቅ ድጋፍ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ አገሮች ይህን መድረክ እንዲተውት አልመክርም፡፡ ይህ ከመርህ አኳያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካ በዓለም ኢኮኖሚ ካላት ቦታ አኳያም ጥቅሟን አያስከብርም፡፡ የግልግል ዳኝነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ፍጥረት እንደሆነ መርሳት የለብንም፡፡ ነገር ግን የምንሰጠውን በጎ ፈቃድ ከዚህ በፊት ከነበረን የተሻለ ቦታ ለማግኘትና የተሻለ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረን አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ ያለ በማደግ ላይ ያለ አገር ለውጭ ኢንቨስትመንት ጥበቃ በማድረግና የራሱን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር መካከል ሚዛን መፍጠር የሚችለው እንዴት ነው? ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ጥቅሟን ማሳደግ የምትችለውስ በምን መልኩ ነው?
ዶ/ር ዘውድነህ፡- ኢትዮጵያ 30 የኢንቨስትመንት ስምምነቶች የፈረመች ቢሆንም፣ የአይሲኤስአይዲም ሆነ የኒውዮርክ ኮንቬንሽኖች አባል አይደለችም፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ማለት በግልግል ዳኝነት የኢትዮጵያን የመንግሥት ወይም የግል ተቋም ያሸነፈ የውጭ ኢንቨስተር ተሸናፊው አካል ከኢትዮጵያ ውጪ ንብረት ከሌለው ውሳኔን የማስፈጸም አደጋ ይሸከማል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አደጋ በተቃራኒ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሠርት በርካታ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ስባለች፡፡ በዚህም ብዙዎች የሚቀኑባትና በየትኛውም መሥፈርት በአፍሪካ ምርጥ ከሚባሉት የምትካተት ሆናለች፡፡ በአደጉት አገሮች ኢኮኖሚው በቅርቡ ዓመታት የተዳከመ ቢሆንም እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ግን አልቀነሱም፡፡ ይህ ለእኔ የሚያሳየኝ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ስምምነት ሲፈጸም በተለይ ደግሞ የግልግል ዳኝነት ድንጋጌዎች ሲቀረፁ ኢትዮጵያ የተሻለ ጥቅም የምታገኝበትን ድርድር ለማድረግ የተሻለ ዕድል እንዳላት ነው፡፡ አዲስ አበባ ሁሉም የግልግል ዳኝነቶች የሚካሄድባት ቦታ ትሁን ባልልም የአፍሪካ ደንበኞቼ ለአፍሪካ ቅርበት ያለው ቦታ እንዲመርጡ እመክራለሁ፡፡ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን በተመለከተ የማሰላሰያ ሐሳቦችን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የኮንቬንሽኖቹ አባል ሳትሆንም የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ጠቀሜታ ላይ ያለውን ጥርጣሬ በይቅርታ እንድናልፈው የሚያደርግ ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ሕግ ጠቀሜታን በተመለከተ ከቅኝ ግዛት በኋላ በማደግ ላይ ላሉ የአፍሪካ አገሮች የተሰጠውን ገለጻ በኢትዮጵያ ሲፋለስ አይተናል፡፡ ይሁንና የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ሥር የሰደደ የእርስ በርስ መተማመንና የጋራ ፍላጎት ማንፀባረቂያም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የልማት ጥረት ውጤታማ ሲሆንና ኢንቨስተሮቹ ወደ ውጭ እየሄዱ መሥራት ሲጀምሩ የአገሯ ኢንቨስተሮች የተሻለ ጥበቃ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ግድ ይላታል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው ቻይና ነች፡፡ ቻይና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የተሻለ ሚና መጫወት ስትጀምር የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ማድረጉንም ጨምራለች፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ሕግ ሥርዓት ጀርባዋን እንድትሰጥ አልመክርም፡፡ ነገር ግን መጠየቅ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ የኢንቨስትመንት ስምምነቶቹ አሁን ባላቸው ቅርፅ ታሳቢ ያደረጉትን ዓላማ እያሳኩ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ አሁን እንደ አዲስ እየመጡ ያሉ የኢንቨስትመንት ስምምነት አዝማሚያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የፖሊሲ አቅጣጫዎቹን መቅረፅ ለኢትዮጵያ ብልህነት ነው፡፡