CURRENT

የጨለምተኞች አስተሳሰብ ገሃድ ይውጣ!

By Admin

August 30, 2016

የጨለምተኞች አስተሳሰብ ገሃድ ይውጣ!

አንዳንድ ወገኖች ከሰሞኑ በድርጅታችን ኢህአዴግ በመካሄድ ላይ ያለውን ግምገማ ልክ ድርጅቱ ሊፈራርስ እንደተቃረበ እና ከፍተኛ ሹም ሽር ከማድረግ ጋር አያይዘው እያቀረቡት ይገኛል፡፡ ያው እነዚህ ወገኖች ሁል ጊዜም መቼም የሚነገራቸውን ገልብጠው ማንበብ የሚቀናቸው ሆኑ እንጂ ኢህአዴግ የሚታወቀው ሁሌም ጠንካራ እና በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ ግምገማዎችን በማድረግ ነው ፡፡ ኢህአዴግ ያለ ግምገማ ቀጣይ ህልውና አይኖረውም፡፡ ለነገሩ የእነዚህ ወገኖች ዋነኛ አላማ የታወቀ ነው፡፡ ድርጅቱንና አካሄዱን በሚገባ ስለሚያውቁት ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ በተሳሳተ መንገድ ትልቅ ለውጥ ይመጣል ብሎ እንዲጠብቅ ያደርጉትና ወይ ድርጅቱ በህዝቡ ግፊት ተገዶ የማፈራረስ ስራ እንዲሰራ አልያም ደግሞ የተጋነነ የለውጥ ወሬ በማውራት ከፍተኛ ለውጥ እንዲጠብቅ ካደረጉት በኋላ ህዝብ የድርጅቱ የግምገማ ውጤት እነሱ በሳሉለት መንገድ አለመሆኑን ሲያይ አላልኳችሁም. ይሄ ድርጅት እኮ ግምገማ ይላል እንጂ ለውጥ አያመጣም !! ብሎ የሚመጣውን ለውጥ ለማንኳሰስ የሚጠቀምበት ስልት ነው፡፡ ይሄ ደሞ በአራዶች ቋንቋ የተበላበት ሙድ ነው አይደል የሚባለው፡ ለምን እንደዚህ እንደሚያደርጉ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በመሰረቱ በድርጅታችን ከሰዎች ለውጥ በላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የአስተሳሰብ ለውጥ ጉዳይ ነው፡፡ የድርጅቱ ትግል የህዳሴውን ጉዞ ሊመራ የሚችል የነጠረ አስተሳሰብ መገንባት ላይ ነው፡፡ ይህ የሰዎች ሹም ሽር ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ከአስተሳሰብ ለውጡ እና ከአስተሳሰብ ከፍታው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለውጦች ሊኖሩ ቢችሉም ዋነኛ ማጠንጠኛው ግን ከጥገኛ ጎራ መደበላለቅ የሚያጠራ ትግል በህዝቡና በድርጅቱ ውስጥ የመለኮሱና የመቀጣጠሉ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁም ሌላው ከዙሁ ግምገማ ጋር ከሰሞኑ ከሚናፈሱ ጉዳዮች አንዱ ተሃድሶ እያደረገ ነው ኢህአዴግ የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ በየትኛውም የመንግስትም ሆነ የድርጅት ሚድያ ተሃድሶ ይደረጋል ተብሎ በግልፅ አልተነገረም፡፡ መልሰን እነዚህን መረጃዎች ማንበብ እንችላለን፡፡ ይልቁንም የ15 ዓመት የተሃድሶ ጉዟችንን ወደ ኋላ መለስ ብለን እንገመግማለን በሚል ነው የተላለፈው መልእክት፡፡ የ15 ዓመት የተሃድሶ ጉዟችን መገምገም በሌላ ወቅት ስናደርጋቸው ከነበሩ ግምገማዎች መሰረታዊ የሆነ ለውጥ የለውም፡፡ ምናልባት የግምገማው ጥልቀትና ጥንካሬ እንዲሁም አስፈላጊነት ከወቅታዊ ሁኔታዎችም ጋር አያይዞ ማየት ይቻላል፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግ በ1990ዎቹ መጀመርያ ወቅት ካጋጠመው የጥገኛ ዝቅጠት (ቦናፓርቲዝም ) አደጋ እና ከነበረ የአስተሳሰብ ብዥታ ነጥሮ የወጣበትና በአዲስ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ያስገባው የተሃድሶ አቅጣጫ ዛሬም ቢሆን ነገም ቢሆን የዚህች ሃገር የለውጥ እና የህዳሴ ጉዞ ዋስትና እና መድህን ነው፡፡ ይህ የተሃድሶ መስመራችን በተቀመጠለት ትክክለኛ አቅጣጫ መጓዙን ግን 15ኛ አመቱን አስታኮ ማድረጉ ወሳኝና አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የመስመሩን ደህንነት መፈተሽና ወቅቱ በሚፈልገው የአስተሳሰብ ከፍታ መምራት እንዲሁም ጊዜ አመጣሽ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረ ቅኝት ማስቀመጥ የሚጨምር ድርብ ተልእኮ ያነገበ መሆንም ይኖርበታል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስርአቱን እየተፈታተነው የመጣው የጎራ መደበላለቅ እና የጥገኝነት ባህርይ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ድርጅታችንና ልማታዊ መስመራችን እየተፈታተነው እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመራችን ጥራት የሚረጋገጠው ከገበያው እና ከጥቅም ትስስር ነፃ የሆነ ከባለ ሃብቱ ኪስ የማይገቡ ግንባር ቀደሞች በመጀመርያው የመሪነት መስመር ማሰለፍ ሲቀጥል ነው፡፡ ይህ እንዲሆን እንደ ሁልጊዜውም ህዝቡን በነቂስ ያሳተፈ ትግል ማካሄድ ይገባል፡፡ ህዝቡ ድርጅቱን እና መስመሩን ያጠራዋል ፤ ከህዝቡ የወጡ ግንባር ቀደሞች በሚመሩት ድርጅት ደግሞ ህዝቡን በለውጥ ምህዋር ውስጥ ያስገቡታል፡፡ በዚህ ተተካኪ የለውጥ አዙሪት ውስጥ በማስገባት ለሚቀጥሉት አመታት የማይቋረጥ ሃገራዊ የለውጥ ጉዞ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በድርጅታቸን እየተከናወነ ያለው ግምገማ በመሰረቱ ኢህአዴግ ሁሌም እንደሚያደርገው ግምገማ ችግሮቹን የሚያይበት ፍፁም ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን የሚከተል በመሆኑ የሚጠፋፋ እና የሚደበላለቅ መንደር የለም፡፡ እንደውም ከፍተኛ የመነቃቃትና አዲስ ወኔ የሚሰነቅበት መድረክ ነው፡፡ ይህ የሚፈጠረው ዲሞክራሲ በደጃፋቸው ባላለፈባቸው በነእንትና ሰፈር ነው፡፡ ኢህአዴግ ግምገማ ሲቀመጥ ለጠላት ሁሌም መርዶ ነው( መቼም ጠላት የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ለአስተሳሰብ ጠላቶች መሆኑን ይሰመርልኛል ብዪ አስባለው)፡፡ ዛሬ ሳይሆን ያኔ በትጥቅ ትግል ወቅት እንኳን የሃሳብ ልዪነት በመድረክ እንዲስተናገድና በመድረክ እንዲወሰን ከማድረግ ውጪ ምንም ምርጫ እንዳይኖር የወሰነ ድርጅት ነው፡፡ በታሪካዊው ደጀና ቤዝ በተደረገ ርእዮተ አለማዊ ልዪነት የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መሃከል በነበረ የሃሳብ ልዪነት እንኳን በመድረክ ሰፊ ክርክር እንዲካሄድበት ከተደረገ በኋላ በአስፈሪው የትግል ወቅት በሃሳብ የተለየው ግለሰብ ምናልባት ለጠላት መጠቀሚያ ሊሆን እንደሚችል ቢታሰብ እንኳን የግለሰቡ የመሄድ መብት ተከብሮ በነፃ በደህናው ከሃገር እንዲወጣ እስከመሸኘት የደረሰ የአስተሳሰብ ጥልቀት የተላበሰ ድርጅት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እናም አሁንም እንደሌላው ጊዜ የገጠመንን ችግር የምንወጣው መጀመርያ ራሳችንን በማጥራት ነው በሚል አስተሳሰብ ሁሌም ጓዳውን ለማፅዳት የሚነሳው ድርጅታችን ኢህአዴግ፡ ምንም እንኳን የችግሮቹ አልፋና ኦሜጋ የውስጥ ችግር ብቻ ባይሆንም ነገር ግን እንደ ሁልጊዜው የራሱን ቤት በቅድሚያ መፈተሸ ጀምሯል፡፡ ይህ ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ የአስተሳሰብ ጥራትና አንድነት ተይዞ የውጪውን ችግር ጠራርጎ ለማጥፋት እና ለቀጣይ ገድሎች ምቹ መደላደል የሚፈጥር እንደሆነ ባለፉት አመታት ተሞክሮ የሚታወቅ ነው፡፡ መልካም ጊዜ!

Aderech Arada