አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ የምሥራቅ ናይል የቴክኒክ የቀጣና ጽሕፈት ቤት (Eastern Nile Technical Regional Office/ENTRO) ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ አቶ ፈቅአህመድ ይህን ኃላፊነት ከሁለት ዓመት በፊት ከመረከባቸው በፊት ለብዙ ዓመታት በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሠርተዋል፡፡ ከያዙት ኃላፊነት በተጨማሪ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የወሰን ተሻጋሪ ውኃዎችን በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንና መንግሥትን የሚያማክረው የብሔራዊ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢም ናቸው፡፡ በአቶ ፈቅአህመድ የሚመራው ኢንትሮ ከስዊድን ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ለምሥራቅ ናይል ሚዲያ ባለሙያዎች ሥልጠናና ግድቡን የመጎብኘት ፕሮግራም አከናውኗል፡፡ በሥልጠናውና በጉብኝቱ የተሳተፈው ሰለሞን ጎሹ በዚሁና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ አቶ ፈቅአህመድን አናግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ወክለው ለበርካታ ዓመታት በውኃ ጉዳይ እንደ መሥራትዎ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርገው ኢንትሮን መምራትን እንዴት አገኙት?

አቶ ፈቅአህመድ፡- እ.ኤ.አ. በ1999 የናይል ተፋሰስ አገሮች ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ለማስፈን የናይል ትብብር መድረክ (Nile Basin Intiative/NBI) አቋቁመዋል፡፡ ይህ የትብብር መድረክ ሦስት ማዕከላት አሉት፡፡ አንደኛው በኡጋንዳ ኢንቴቤ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ ማዕከል በአብዛኛው መተማመንን የሚያጎለብቱ፣ አቅምን የሚገነቡ፣ አደረጃጀቶችን፣ ፖሊሲዎችንና የውኃ ሀብት አስተዳደርን በተመለከተ ይሠራል፡፡ በአሥር የተፋሰሱ አገሮች ይሠራል፡፡ ሁለቱ የቀሩት ማዕከላት የድርጊት መርሐ ግብር ላይ ነው የሚሠሩት፡፡ አንደኛው የናይል ታላላቅ ሐይቆች የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ይህ ጽሕፈት ቤት በሩዋንዳ ኪጋሊ ነው የሚገኘው፡፡ ሌላኛው በአዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን፣ በምሥራቅ ናይል ለሚገኙት ለኢትዮጵያ፣ ለግብፅ፣ ለሱዳንና ለደቡብ ሱዳን ፕሮጀክቶችን እያዘጋጀ የትብብርን ጥቅም በተግባር ለማሳየት የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚሠራው ኢንትሮ ነው፡፡ ስለዚህ ኢንትሮ የናይል ትብብር መድረክ አንድ ክፍል ነው፡፡ ኢንትሮ ያዘጋጃቸው ፕሮጀክቶች በአገሮቹ ይተገበራሉ፡፡ ይኽም በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ወደ ኢንትሮ ከመምጣቴ በፊት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ነበርኩ፡፡ በዚያ ወቅት በናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ ሥር ላሉት ሦስት ማዕከላት ኢትዮጵያን በመወከል የበላይ ተቆጣጣሪ ሆኜ እሠራ ነበር፡፡ ስለዚህ ኢንትሮን በፊትም ቢሆን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ይህ የዋና ዳይሬክተርነት ቦታ በፈረቃ የሚቀያየር በመሆኑ የሥራ ዘመኔ ሦስት ዓመት ነው፡፡ ሁለቱን ስለጨረስኩ አንድ ዓመት ይቀረኛል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተፋሰሱ አገሮች በአጠቃላይና በተለይ ግን ግብፅና ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ የማይግባቡባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ያለፉት ጥቂት ዓመታት አንፃራዊ መሻሻሎች ታይተዋል፡፡  አገሮቹ ተግባብተው ውኃውን በጋራ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ኢንትሮ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ኢንትሮ በዋነኛነት የተቋቋመው ትብብርን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ለመሥራት ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ እንደተቋቋመ የመጀመርያ ሥራው የነበረው አገሮቹ የተስማሙበት ሰባት ፕሮጀክቶችን መተግበር ነበር፡፡ ከእነኚህ ውስጥ ቁልፍ ተደርጎ የሚወሰደው ፕሮጀክት የምሥራቅ ናይል የኃይል ንግድን የተመለከተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ፣ በግፅብና በሱዳን መካከል ኃይል የመሻሻጥ ሥራዎችን ያጠና ፕሮጀክት ነው፡፡ በጥናቱ መሠረት ኢትዮጵያ ለግብፅና ለሱዳን ከፍተኛ ኃይል መሸጥ ትችላለች፡፡ በመጀመርያው ዙር እስከ 3,200 ሜጋ ዋት አመንጭታ መሸጥ እንደምትችል የሚያሳይ ጥናት ነው፡፡ በጥናቱ ላይ የሦስቱ አገሮች የኢነርጂ ሚኒስትሮች ተስማምተው ተፈራርመዋል፡፡ ለግብፅ 2,000 ሜጋ ዋትና ለሱዳን 1,200 ሜጋ ዋት ኢትዮጵያ እንደምትሸጥ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ከዚያም ባለፈ ለዚሁ የኃይል ማመንጫ የሚሆን አንድ ትልቅ ግድብ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነባ በቅድመ ዝርዝር ደረጃ ሦስቱ አገሮች አማካሪ ቀጥረው አጥንተዋል፡፡ ይኼም ግድብ በወቅቱ የድንበር ግድብ ይባል ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚባለው ፕሮጀክት ነው፡፡ ግብፅና ሱዳን ከትብብር ባይወጡ ኖሮ ከዚህ ፕሮጀክት የተሻለ ተጠቃሚ የመሆን ዕድል ነበራቸው፡፡ ሌላኛው ቁልፍ ፕሮጀክት አገሮቹ በጋራ ለይተው፣ አጥንተው የሚተገብሩት ነበር፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ትላልቅ ግድቦች ተለይተዋል፡፡ እነዚህም መንደያ፣ ቤኮ አቦና የድንበር ግድቦች ናቸው፡፡ እነዚህን ግድቦች በጋራ ለማልማት አገሮቹ እየተነጋገሩ እያለ ነው እ.ኤ.አ. በ2010 ከትብብሩ ግብፅና ሱዳን የወጡት፡፡ አገሮቹ ይኼን ፕሮጀክት ረግጠው ሲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁጭ ብሎ መጠበቅ የለበትም፡፡ ከነዚህ ውስጥ ግዙፍ የሆነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሱ አቅም ወደ ማልማቱ ሄዷል፡፡ ግብፅና ሱዳን ከትብብሩ የወጡት ለ12 ዓመታት ያህል ድርድር ሲካሄድበት የነበረው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን የላይኛው ተፋሰስ ስድስት አገሮች ሲፈርሙ እሱን በመቃወም ነው፡፡ ግብፅና ሱዳንን ወደ ትብብሩ ለመመለስ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 እሰከ 2013 ድረስ ኢትዮጵያ ብቻ ናት ኢንትሮን ትደግፍ የነበረው፡፡ በነገራችን ላይ እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 20 ቀን 2012 ላይ ኢንትሮ ሊፈርስ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም የሦስት አገሮች የጋራ ጽሕፈት ቤት ስለሆነ አንድ አገር ብቻውን ይዞት ሊቀጥል አይችልም፡፡ በአብዛኛው የልማት አጋሮች መስማማት አለባችሁ የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ስለዚህ እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 20 ቀን 2012 አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ የተደረሰው ስምምነት ግብፅና ሱዳን በአስቸኳይ ወደ ትብብሩ እንዲመለሱና ዘላቂ የሆነ ትብብር ከኢትዮጵያ ጋር የሚፈጠርበትን ማዕቀፍ ለማጥናትና ለማዘጋጀት ነው፡፡ ስምምነቱ ቢፈረምም ግብፆች ስምምነቱ የሚፀድቀው በአገሮቹ መንግሥት ድጋፍ ሲሰጠው ብቻ ነው የሚል አንድ አንቀጽ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያና ሱዳን በነጋታው አጽድቀው አሳወቁ፡፡ ከአራት ዓመትም በኋላ ግብፅ እስካሁን አላጸደቀችም፡፡ ሱዳን ወደ ትብብሩ የተመለሰችው ከዚህ ስምምነት በኋላ ነው፡፡ አሁንም ግብፅን ወደ ትብብሩ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የዚህ ጥረት ዋኛው አካል ጥናቶችን ማካሄድ ነው፡፡ ጥናቶቹ ግብፅ ወደ ትብብሩ ብትመለስ ከማንም በላይ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ያሳያሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ሚኒስትሮቹ በተገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ይነጋገራሉ፡፡ በተለይ የሱዳኑ ሚኒስትር ግብፅ እንድትመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከውኃው ጋር በተያያዘ ግብፆች ለረዥም ጊዜ የፈጠሯቸው አመለካከቶች አሉ፡፡ ይህን ማለፍ ተስኗቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከትብብር ዋነኛ ተጠቃሚዎች ግብፆች ናቸው፡፡ መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ ለመመለስ ግን ማትጊያ ይፈልጋሉ፡፡ ይኼን ማትጊያ ማን እንደሚሰጥ ግን አይታወቅም፡፡ የማትጊያውን ጉዳይ ወደ ጎን ትተው ወደ ትብብሩ ቢመለሱ የተሻለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያለ በቂ መረጃና ማስረጃ በስሜት የሚወሰኑ ነገሮችን በማስቀረት ዕውቀት ተኮርና ሳይንሳዊ በሆነ ውሳኔ ለመቀየር የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን ትሠራላችሁ፡፡ ይህ ሱዳን አቋሟን እንድትቀይር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይታመናል፡፡ ግብፅ በተመሳሳይ እነዚህን ጥቅሞች ማየት የተሳናት ለምንድን ነው? ጥናትና ምርምሮቹ ላይስ ግብፆች ይሳተፋሉ?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ግድቡንና ከግድቡ ባሻገር ያሉ ጉዳዮችን ስናጠና የምናገኛቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ግብፅና ሱዳን ለበርካታ ዓመታት የናይል ውኃን የግል ንብረታቸው አድርገው ይቆጥሩት ነበር፡፡ ሁለቱ ብቻ የውኃው ባለቤት እንደሆኑ የሚያምኑ በርካታ ዜጎች በአገሮቹ ውስጥ አሉ፡፡ ይህን አመለካከት የፈጠረው ያለፉት የአገሮቹ መሪዎች የሰጧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ናቸው፡፡ ይህን መቀየር ረዥም ጊዜ ይፈጃል፡፡ እውነታው የናይል ውኃ የናይል ተፋሰስ አገሮች ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የሚጠቀሙበት ሀብት ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ለብቻቸው ይጠቀሙ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ ግብፅ ወደ ትብብሩ ስትመጣ ሌሎች አገሮች ውኃውን እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል የሚል ፍራቻ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ውኃውን ማልማት ጀምረዋል፡፡ ይህ ማለት የሚመጣው ተፅዕኖ በሙሉ የሚያርፈው ግብፅ ላይ ነው፡፡ አሁኑ በመጠናት ላይ ካሉ ጥናቶች ውስጥ አንዱ ሁሉም አገር የራሱ ዕቅድ እንዳለውና ጥናቶቹም ግዙፍ እንደሆኑ ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ሁሉንም ዕቅዶች ለመተግበር ውኃው በቂ እንደማይሆን ይደመድማል፡፡ ውኃው በቂ የሚሆነው አገሮቹ ሲተባበሩ ብቻ ነው፡፡ የጥናቱ የመጀመርያ ደረጃ ውጤት የሚያሳየው አገሮቹ በተናጠል ወደ ልማት ከገቡ በጣም ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጥረት እንደሚኖር ነው፡፡ የዚህ የውኃ እጥረት ሰለባ የምትሆነው ደግሞ ግብፅ ነች፡፡ በትብብር ከሠሩ ግን እጥረቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎ በጥናቶቻችን የግብፅ ምሁራን ይሳተፋሉ፡፡ በናይል ላይ ለበርካታ ዓመታት የሠሩ ምሁራን አሏቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻቸውንና በኢንተርንሺፕ ተማሪዎቻቸውን እናሳትፋለን፡፡ በጥናቶቹ ላይ ያላቸውን አስተያየት ይፋዊ ባልሆነ መልኩ እናገኛለን፡፡ በግድቡም ላይ የተሠሩት ጥናቶች ይህንኑ ነው የሚያመለክቱት፡፡ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል? በተለይ በአሞላልና ኃይል ማመንጨት ሲጀምር የሚኖረው ጥቅምና ጉዳት ምን ይመስላል? የሚሉት ጉዳዮች ይጠናሉ፡፡ ስለዚህ በተለያየ መልኩ እነኝህን ዕውቀቶች የመፍጠር፣ በእነኚህ ዕውቀቶች ላይ ተመሥርተው ውሳኔ እንዲወስኑ የመርዳት ሥራ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢንትሮ በተዘጋጁ መድረኮች ከቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎችና ውይይቶች ለመረዳት እንደሚቻለው የተፋሰሱ አገሮች በኢኮኖሚ ደካማ የሚባሉና በበርካታ ችግሮች የተከበቡ የተፈጥሮ ጥበቃ አያያዛቸውም አመርቂ ያልሆነ ነው፡፡ ይህ የውኃውን ሕልውናና ጥራት አደጋ ላይ እንደጣለው ይነገራል፡፡ ስለዚህ ትብብሩ አለመተግበሩ  በአብዛኛው ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ጊዜያዊ ጥቅም ቢያስገኝም፣ ዘለቄታዊ ጉዳቱ ግን በዘገየ ቁጥር ወደ ማይመለስ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ሥጋት አለ፡፡ ይህ ሁሉ የጥናት ውጤት እነ ግብፅን ወደ ትብብር ለመሳብ እንዴት አልቻለም?

አቶ ፈቅአህመድ፡- የወሰን ተሻጋሪ ውኃን ማነው የሚያስተዳድረው? የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የወሰን ተሻጋሪ ውኃን በተመለከተ ጥናቶችን የማጥናት፣ ልማቶችን የማካሄድ፣ ውኃውን የመንከባከብ፣ ዓለም አቀፍ ድርድሮችን የማድረግና የመፈረም፣ ስምምነቱን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው ለውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ነው፡፡ ሌሎቹ ድጋፍ ነው የሚሰጡት፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ውኃ የቴክኒክ ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውም ውኃን በተመለከተ ያሉ ጉዳዮችን በቴክኒክ ደረጃ መፍታት ይቻላል የሚል እምነት ነው ኢትዮጵያ ያላት፡፡ ሱዳንን ጨምሮ በአብዛኛው የተፋሰስ አገሮች ውኃ የቴክኒክ ጉዳይ ነው፡፡  ግብፅ ጋር ስንሄድ ግን የተለየ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ውኃን በሦስት ዓይነት መልኩ ማስተዳደር ይቻላል፡፡ በቴክኒክ ደረጃ የውኃ ሚኒስትሮች፣ በፖለቲካ ደረጃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ያስተዳድሩታል፡፡ በግብፅ የውኃ አስተዳደሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ተንጠልጥሎ ነው የሚገኘው፡፡ የቴክኒክ መሥሪያ ቤቱ ያለውን ችግር በደንብ ይረዳል፡፡ ጥናቶችን በትክክል ተረድቶ ጉዳዩ መፍትሔ ያስፈልገዋል እያለ ያለው የግብፅ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር ነው፡፡ ግን ውሳኔ የሚሰጠው እነሱ ጋር አይደለም፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የናይል ካንውስል ናቸው የሚወስኑት፡፡ የናይል ካውንስል በፕሬዚዳንቱ የሚመራ ሲሆን፣ ውስጡ የደኅንነት አካላትና የመከላከያ አካላት አሉበት፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር በጣም ትንሽ ሚና ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የግብፅ የውኃ አስተዳደር ከሌሎች ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ በናይል ስብሰባ የሚሳተፉት የውኃ ሚኒስትሩ፣ የሚኒስቴሩ ዋና ዋና ኃላፊዎችና የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡ በግብፅ በኩል ግን የውኃ ሚኒስትሩ ይመጣል፣ አንድ ባለሙያ ይኖራል፣ ሌላው በሙሉ ግን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከደኅንነት ነው፡፡ ማነው ውሳኔውን የሚሰጠው? የሚለውን ራሱ ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይኼ ሁኔታውን ያወሳስባል፡፡ ከትብብር አገሮቹ ይጠቀማሉ፡፡ ሁለተኛ ወንዙ ራሱ ይጠቀማል፡፡ እያንዳንዱ አገር ተፋሰሱን ይንከባከባል፣ የውኃ ብክለት ይቀንሳል፡፡ ቀጣናው ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ያገኛል፡፡ ከወንዙ ባሻገር የሚደረጉ ትብብሮችም ይኖራሉ፡፡ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪና በንግድ የጠነከረ ግንኙነት መፍጠር ይቻላል፡፡ አለመተባበር በጣም ትልቅ ዋጋ ነው የሚያስከፍለው፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ይህን ትልቅ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ ሌላኛው በግብፅ በኩል ያለው ችግር የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (ሲኤፍኤ) ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሲኤፍኤ ከናይል ትብብር መድረክ የተለየ ነው፡፡ ሱዳን ለምሳሌ ሲኤፍኤን አልፈረመችም፡፡ ግን ትብብሩ ውስጥ አለች፡፡ ግብፅ ሁለቱን የመቀላቀል ሥራ ነው የጀመረችው፡፡ በስምምነቱ ስላላመንን ወደ ትብብሩ አንመለስም ነው የምትለው፡፡ ግብፅ ወደ ትብብሩ ትመለሳለች ወይ? አዎ ትመለሳለች፡፡ መቼና እንዴት? የሚለውን ግን መመለስ አዳጋች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንትሮ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ በግድብ ደኅንነት ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ነው፡፡ ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ መጠኔን ይቀንሰዋል ከሚለው ሥጋቷ በተጨማሪ በግድቡ ደኅንነት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ታነሳለች፡፡ የእናንተ ፕሮጀክት ይህን ከመቀየር አኳያ ምን አስተዋጽኦ አለው?

አቶ ፈቅአህመድ፡- በምሥራቅ ናይል ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከ30 በላይ ትላልቅ ግድቦች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ በጣም ያረጁና ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው አሉ፡፡ የግድብ ደኅንነት በምሥራቅ ተፋሰስ ውስጥ በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም በመገንዘብ ኢንትሮ የግድብ ደኅንነትን በተመለከተ በርካታ ሥራዎች ሠርቷል፡፡ ትልቁ የአቅም ግንባታ ነው፡፡ ግድብ ዲዛይን ሲደረግ፣ ሲገነባ፣ እንዲሁም ሥራ ሲጀምር መደረግ ያለበት የደኅንነት ጥንቃቄ ላይ ያለው አቅም አናሳ ነበር፡፡ በየአገሮቹ ያሉ ግድቦች ተመርጠው የደኅንነት ደረጃቸው ምን ይመስላል? ያሉ ችግሮች እንዴት ነው የሚቀረፉት? በዲዛይን ሥራ የግድቡ ደኅንነት በምን መልኩ ነው መረጋገጥ ያለበት? የሚለውን በተመለከተ እንደዚሁ ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ዩኒቨርሲቲዎች ካሪኩለማቸው ውስጥ እንዲካተቱና እንዲያስተምሩ አድርገናል፡፡ ለመምህራኖቻቸውም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ የሚያስተምሩበት ካሪኩለምና መመርያ ተቀርጾ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለአገሮቹም የግድብ ደኅንነትን በተመለከተ ማኑዋል ተዘጋጅቶ፣ አገሮቹ ተስማምተውበት በመተግበር ላይ ነው ያለው፡፡ የግድብ ደኅንነት ደንብ ዝግጅትም እየተጠናቀቀ ነው፡፡ እያንዳንዱ አገር ውስጥ የግድብ ደኅንነትን በተመለከተ የሚሠራ ተቋም መኖር አለበት የሚል እምነት ላይ ደርሰን ሁሉም አገሮች በክፍል ደረጃ አቋቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በዳይሬክቶሬት ደረጃ አቋቁሟል፡፡ የግድብ ደኅንነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አንደኛ ከሕዝብ ሕይወት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ግድቡ ከፈረሰ ታች ያሉ ሕዝቦች ሕይወት አደጋ ላይ ነው የሚወድቀው፡፡ ንብረትም ይወድማል፡፡ ራሱ የግድቡን ሀብት ማጣት ይመጣል፡፡ ግድቡ የሚሰጠው አገልግሎት ይቋረጣል፡፡ የተለያዩ ግድቦች የደኅንነታቸው ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን አይተናል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብንም በተመለከተ በተለያየ አቅጣጫ የደኅንነቱ ሁኔታ ምንድነው? የሚመስለው የሚለውን አይተናል፡፡ ግድቡ የደኅንነት ችግር የለበትም፡፡ ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ፓናል ግድቡ የደኅንነት ችግር እንደሌለበት የራሳቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ሱዳኖችም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሱዳን በግድቡ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አላት፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ችግር ቢገጥመው ታች ያለው ሱዳን ነው ቅድሚያ የሚጎዳው፡፡ ሱዳኖች ባለሙያዎቻቸውን በመላክ ግድቡን አጥንተዋል፡፡ የደኅንነት ችግር የለበትም የሚል ሪፖርት ነው ያወጡት፡፡ ለሚዲያ ባለሙያዎች በተሰጠው ሥልጠና ተሳታፊ የነበሩት የሱዳኑ የናይል የውኃ ዘርፍ ኃላፊ ፕሮፌሰር ሰይፈዲን ግድቡ የደኅንነት ችግር እንደሌለበት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ይኼ ትልቅ ምስክርነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢንትሮ አማካይነት የምሥራቅ ናይል አገሮች የሠሯቸው የጋራ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ወደፊት ይሠራሉ ተብለው ዕቅድ የወጣላቸውም አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው የትብብር ሪከርድ አኳያ በዕቅድ የተያዙት እንደሚሳኩ ምን ያህል ትተማመናላችሁ?

አቶ ፈቅአህመድ፡- ባለፉት 16 ዓመታት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በተለይ በጎርፍ መከላከልና ቅድመ ትንበያ፣ በመስኖና ፍሳሽ፣ በተፋሰስ እንክብካቤ፣ በኃይል ንግድ ላይ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በርካታ ጥናቶችም ተጠንተዋል፡፡ በቀጣይነት እየሠራን ያለው ሥራም አለ፡፡ ግብፅ እየተሳተፈች አይደለም፡፡ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ግን እየተሳተፉ ነው፡፡ ንዑስ ተፋሰሱን በተመለከተ ከግብፅ ጋር በመንግሥት ደረጃ ግንኙነት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ቀጥተኛ የሆነ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት በማይኖርበት ወቅት ሐይድሮ ዲፕሎማሲ (Track Two Diplomacy) ነው የምንጠቀመው፡፡ ሐይድሮ ዲፕሎማሲ ማለት ቀጥተኛ ግንኙነት በማይኖርበት ወቅት ሌሎች አካላትን በመጠቀም ግንኙነት የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ለምሳሌ የአገር ሽማግሌቶችን፣ የሃይማኖት መሪዎችን፣ የቀድሞ ዲፕሎማቶችንና ሚኒስትሮችን በማገናኘት በአገሮቻቸው መንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር ወደ ትብብር የሚመጡበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ እንሠራለን፡፡ ሚዲያ ሌላኛው አማራጭ ነው፡፡ ኢንትሮ ሚዲያ ላይ በጣም ነው የሚያተኩረው፡፡ ምክንያቱም ሚዲያ ስለትብብር የሚናገርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ሌላው ሳይንሳዊ ጥናቶችን ለማጥናትና ምሁራንን በማምጣት በቴክኒክ ደረጃ እንዲነጋገሩ ማድረግ ነው፡፡ ቀጣይ ፕሮጀክቶችን እየቀረፅን ነው፡፡ አንድ ጥናት እያጠናን ነው፡፡ በጥናቱ በአገሮቹ ውስጥ ያሉ በመስኖ፣ በኃይል ማመንጨትና ንግድ፣ በተፋሰስ እንክብካቤና ከመሳሰሉት ፕሮጀክቶች መካከል በማኅበረሰቡና በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርሱትን እየመረጥን እያዘጋጀን ነው፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች ለአገሮቹ በመስጠት የሚተገብሩበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው፡፡ ጥናቱ በቅርቡ ተጠናቆ ይጸድቃል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ በዚህ ጥናት ላይ የግብፅ ተሳትፎ በጣም አናሳ ነው፡፡ አገሮቹ በትብብር ወደ ልማት የሚሄዱበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ ከሁሉም ይበልጥ ግን ተፋሰሱን መንከባከብ፣ ብዝኃ ሀብቱን መንከባከብ፣ እንዲሁም የትብብር መድረኮችን የማስፋት ሥራ ላይ ነው በአሁኑ ጊዜ አተኩረን እየሠራን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅ በይፋ አቋሟን ባትቀይርም በሲቪል ማኅበራት፣ በምሁራን፣ በሚዲያና በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ግን ትብብርን የሚደግፉ አናሳ ድምፆች ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች የግብፅን አቋም ለመቀየር ምን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ?

አቶ ፈቅአህመድ፡- የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት የላቸውም፡፡ ሁሉም አገር የተስማማበት ሕጋዊ ማዕቀፍ የለም፡፡ ሲኤፍኤ እስካሁን አልጸደቀም፡፡ ከሚፈለገው ስድስት አገሮች ውስጥ ሦስቱ ብቻ ናቸው ያጸደቁት፡፡ ስለዚህ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶችን ቀድሞ የማሳወቅ አሠራር የለም፡፡ ያ በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ይኼንን ግድብ የመገንባት ሉዓላዊ መብቷ ነው፡፡ እርግጥ ይህ መብት ወሰን አለው፡፡ ይኽም በሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ነው፡፡ ይህ ግድብ ሲገነባና የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ሥጋት እንዳላቸው ሲገልጹ ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ፓናል በማቋቋም አገሮቹ በግድቡ ላይ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው አድርጋለች፡፡ የፓናሉ ሪፖርት ከወጣ በኋላ የሦስትዮሽ ድርድሮች ነበሩ፡፡ ከዚያም አልፎ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡ የሚኒስትሮችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ ጉባዔም ነበር፡፡ የመርሕ መግለጫ ስምምነት (DOP) ተፈርሟል፡፡ እነዚህን ሒደቶች ስናይ እውነታውን የመቀበል አዝማሚያ አለ፡፡ አሁን ግድቡ መሬት ላይ እውነት ሆኗል፡፡ በቅርቡ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ግድቡ መሬት ላይ ያለ ክስተት ነው ብለዋል፡፡ ይህን ክስተት መቀበልና በዚህ ክስተት ውስጥ እንዴት ነው የተሻለ ተጠቃሚ የምንሆነው የሚለው ላይ ብናተኩር ይሻላል ብለዋል፡፡ ግብፆች ከግድቡ የሚያገኙት ጥቅም ላይ ቢያተኩሩ ጥሩ ነው፡፡ ግድቡ ግብፅ ላይ ተፅዕኖ የለውም ማለት ሳይንሳዊ አይደለም፡፡ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ትልቁ ነገር ያ ተፅዕኖ ጉልህ ነው? ወይስ አይደለም? ማካካስ ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚገኘው ጥቅምና የሚያመጣው ተፅዕኖ ሚዛኑ ምን ይመስላል? የሚለውን መመርመር ነው፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ እኮ በዓባይ ላይ የመጀመርያው ግድብ እንጂ የመጨረሻው አይሆንም፡፡ ዓባይ ወንዝ ላይ ብቻ አራት ግድቦች አሉ፡፡ በህዳሴው ግድብ ላይ ስንስማማ በሌሎችም ላይ ተመሳሳይ አሠራር ይኖራል፡፡ ሁላችንም በተናጠል ልንቋቋመው የማንችለው አደጋ የከባቢ አየር ለውጥ ነው፡፡ ይኼ የከባቢ አየር ለውጥ ሲመጣ ወይ  ጎርፍ አልያም ድርቅ ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ ጎርፍ ይዞ ሲመጣ በጎርፍ መልክ የመጣውን ውኃ ኢትዮጵያ ውስጥ አከማችቶ ቀስ በቀስ ለነሱ መልቀቅ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የአስዋን ግድብ ትልቅ  ጎርፍ ሲመጣ መሸከም አይችልም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 የናይል ወይዝ ወደ 43 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ውኃ ነው ይዞ የሄደው፡፡ ያ የአስዋን ግድብ ሊያፈርሰው ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ቶሎ ነቅተው ወንዙን ቶሽካ በርሃ ላይ በመልቀቅ ሐይቅ ፈጥረዋል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቢኖር ኖሮ ያንን ውኃ እዚህ አከማችቶ በማቆየት የአስዋን ግድብ ዝቅ ሲል መልቀቅ ይቻል ነበር፡፡ ሌላኛው የከባቢ አየር ለውጥ ችግር ድርቅ ነው፡፡ ድርቅ ሲፈጠር አስዋን ላይ ትልቅ የውኃ እጥረት ይኖራል፡፡ ትብብር ካለ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከማቸ  ውኃ ስለሚኖር እሱን መልቀቅ ይቻላል፡፡ ከአቀማመጣቸው የመጣ ፍራቻ አለ፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ግድብ ትነገባለች ብለውም አልገመቱም፡፡ ከዚያ እየነቁ ነው፡፡ ግብፆች በደንብ የነቁ ዕለት ወደ ትብብሩ ይመጣሉ፡፡