የኦሮሚያና ደቡብ ክልልሎች ከ8ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህግ ታራሚዎች ምህረት አደረጉ
ጳጉሜ 4፣2008
የኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለ8 ሺህ ላይ የህግ ታራሚዎች ምህረት ማድርጋቸንውን አስታወቁ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከ5ሺ 4 መቶ በላይ ታራሚዎቹ ምህረት የተደረገላቸው በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው እና የእርምት ቆይታቸውን በግማሽ ያጠናቀቁ ናቸው ተብሏል፡፡
በሙስና፣ በሽብርተኝነት፣ በሰው መግደል እና አስገድዶ መድፈር የተፈረደባቸው ታራሚዎች በምህረቱ አልተካተቱም፡፡
ምህርት የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለሀገሪቱ ሰላም እና ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ሪፖርተራችን ሙባረክ ሙሃመድ ዘግቧል።
በተያያዘ የደቡብ ክልል መንግሥት አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ከ3 ሺህ ለሚበልጡ የህግ ታራሚዎች ምህረት ማድረጉን ገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች በተለያዩ ወንጄሎች በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጣቸው ናቸው፡፡
ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች በቆይታቸው በፈጸሙት ወንጀል የተጸጸቱ፣ ትምህርት ያገኙና የበደሉትን ህብረተሰብ ለመካስ ዝግጁ መሆናቸው መረጋገጡንም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡
የህግ ታራሚዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የበለጠ ውጤታማ ሆነው ህብረተሰቡን መካስ እንደሚኖርባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበው፤ ህብረተሰቡም በፍቅር እንዲቀበላቸው ጥሪ አስተላለፏል ሲል ኢዜአ ዘግቧል ።