Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በኦታዋ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲስ አመቱን ምክንያት በማድረግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አካሄዱ፤

0 800

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቅዳሜ ዕለት ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በኦታዋ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የተሳካ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡የ2009 ዓ.ም አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ምሽት ኦታዋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ህዳሴ ም/ቤት ከኤምባሲው ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ ከ 150 በላይ የሚሆኑ በኦታዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በኦታዋ የሚገኙ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣የአገራቱ የዳያስፖራ ተወካዮችና ታዋቂ ግለሰቦች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ የዝግጅቱ አስተባባሪና በኦታዋ የኢትዮጵያ ህዳሴ ም/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኪዳኔ ገ/ማሪያም ለታዳሚው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ በኦታዋ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ዕለት ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸው እንዳልተለየና ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ የሚካሄድ ለ6ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመቀጠልም የግድቡ ግንባታ ባሁኑ ወቅት ወደ 70% የደረሰ መሆኑን ጠቅሰው ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ”እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን !” ብለዋል፡፡ከካርልተን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩት የመጡት ሱዳናዊው ፕሮፌሰር Taj Elkhazin የእለቱ ተጋባዥ እንግዳና ንግግር አቅራቢ የነበሩ ሲሆኑ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በአባይ ዙሪያ የተደረጉ ቀደምት ስምምነቶች ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያላሳተፉና ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብን በመገንባት ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ አካባቢያዊ ትስስርን ለማጠናከር እየሰራች ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡የኦታዋ ከተማ ም/ቤት አባልና በዕለቱ የከተማውን ከንቲባ ወክለው የተገኙት Mr.Michael Qaqish በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በኦታዋ ነዋሪ የሆኑት የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አባላት ተሰባስበው በትውልድ አገራቸው የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት በማድነቅ ይህ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡በኦታዋ የናይጄሪያ ኮሙኒቲ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ- ካናዳ አሶሲየሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ናይጄሪያዊው Dr.John Adeyepa በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ለታዳሚዎቹ ባደረጉት ንግግር ናይጄሪያን ጨምሮ በአፍሪካ ካለው የሀይል እጥረት አንጻር በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድህነትን ለማሸነፍ እየተደረገ ካለው ትግል አንጻር ለመላው አፍሪካ ተስፋ ሰጪ ነው ካሉ በኋላ ሁሉም አፍሪካዊ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በኦታዋ የሱዳን ኮሙኒቲ አባል የሆኑት Dr.Amira Ali ባደረጉት ንግግር ደግሞ በቅርቡ በሪዮ (ብራዚል) ኦሎምፒክ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያመጧቸውን ውጤቶች በመዘርዘር በተለይ ደግሞ አልማዝ አያና ለሀገሯ ወርቅ ከማስገኘቷ በተጨማሪ አዲስ ፈጣን ክብረወሰን ማስመዝገብ በመቻሏ አድናቆት የሚገባት ብርቅዬ አትሌት መሆኗን ገልጸው አትሌቷ ለወደፊትም አገሯ ትልቅ ተስፋ የምትጥልባት አትሌት ናት በማለት በኦሎምፒኩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባስመዘገቡት ውጤት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም በኦታዋ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ተ/ጉዳይ ፈጻሚ የሆኑት አቶ ነቢያት ጌታቸው ኤምባሲውን በመወከል ለታዳሚው ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ”እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን!” በሚል መርህ የሀገራችን ህዝብ ያለውን ገንዘብ፣ዕውቀትና ጉልበት ተጠቅሞ አገራችንን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ትልቅ ድርሻ ያለውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የልማት ውጥኖች ከዳር ለማድረስ አሁንም ተባብሮ መስራት እንደሚስፈልግ በመጠቆም እንደ እስካሁኑ ሁሉ የዳያስፖራ ማህበረሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን በማቅረብ እስካሁን ለተደረገው የጋራ ርብርብ በኤምባሲውና በራሳቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡በሌላ በኩል በኦታዋ የኢትዮጵያ ህዳሴ ም/ቤት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጉግሳ ወርቅነህ ለዕለቱ የዝግጅቱ ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር በዚህ ለ 6ኛ ጊዜ በሚካሄደው የግድባችን ገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የተገኘውን ታዳሚ በሙሉ በማመስገን ግድቡ አገራችን ከድህነት ለመውጣት ያላትን ቁርጠኝነት የምታሳይበት በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ያላሳለሰ ድጋፋችንን እናደርጋለን ካሉ በኋላ ይህ ብቻ ሳይሆን አገራችን ከድህነት ለመውጣት የምታደርጋቸውን ቀጣይ የልማት ስራዎች ሁሉ እንደግፋለን በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡ በመጨረሻም በዕለቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፋይናንስ ድጋፍ ከስጦታ፣ከጨረታ፣ከሎተሪ፣ ከመግቢያ ትኬትና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ታዳሚዎች በሙዚቃ ዝግጅት ሲዝናኑ አምሽተዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy