Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብአዴን የለውጥ ኃይል የሆነ አመራር በየደረጃው ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው- የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን

0 560

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ ህዝባዊ ኃላፊነትን በአግባቡ በመወጣት የለውጥ ኃይል የሆነ አመራር በየደረጃው ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ብአዴን “በጥልቀት በመታደስ ክልላዊና አገራዊ ህዳሴያችን እናፋጥን!” በሚል መሪ ቃል የከፍተኛ አመራር ኮንፈረንስ በባህርዳር ከተማ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በመድረኩ ላይ እንደገለጹት “ብአዴን በአስተሳሰብና በአፈጻጸም የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በጥልቀት የመታደስ መርህን ተግባራዊ ያደርጋል።”

ሊቀመንበሩ እንዳሉት ባለፉት 15 ዓመታት በግብርና ምርታማነት፣ በኢንዱስትር ልማት መስፋፋት፣ በአገልግሎት ዘርፉ የመጡ ለውጦች በስኬት የተመዘገቡ ናቸው።

በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች የማህበራዊ ልማት ዘርፎችም የተመዘገቡ ለውጦች አመርቂ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በክልሉ ሁለንተናዊና ፈጣን ልማት በማስመዝገብ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማፋጠንና የመልካም አስተዳደር በማስፈን የተገኙ ለውጦች ተገምግመው ቀጣይነታቸው ይረጋግጣልም ብለዋል።

ከህብረተሰብ ኑሮ መሻሻል፣ ከስራ አጥነት፣ ከመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በጋራ ለመረባረብ ኮንፈረንሱ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በዚህም ባለፈው ሳምንት የሰላምና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ሰነድ በማዘጋጀት የማዕከላዊ ኮሚቴው መክሮ መግባባት ላይ መድረሱን አውስተዋል።

አሁን የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮችን ያሳተፈ ኮንፈረንስ ማከሄድ መጀመሩ የሚስተዋሉ ተግዳሮችን በላቀ ንቅናቄ ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የድርጅቱ ባህሪ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን በማስፈን የህዝብ እርካታን በቀጣይነት ማረጋገጥ ነው ያሉት ደግሞ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለምነው መኮንን ናቸው።

“ባለፉት ዓመታትም ውጤታማ ፖሊሲዎቻችንና ስትራተጅዎችን ወደ ተግባር በማሸጋገር ክልሉም ሆነ አገራችን በለውጥ ምህዋር ውስጥ በመግባት የህዳሴ ጉዞ ተጀምሯል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የመንግሥት ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም፣ ብዝሃነትን የሚጻረር የትምክህት፣ የጠባብነትንና የጥገኝነት አሰትሳሰብና ተግባር በአመራሩ መስተዋላቸውን ጠቁመዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ይህም ህዝቡ ከስራ አጥነትና ከሌሎች ጋር የተያያዙ መሰረታዊና ወቅታዊ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ አስገድዶታል።

ኮንፈረንሱም የተስተዋሉ ችግሮችን መንስኤዎች በመለየትና የመፍትሄ ቀመሮች ላይ በመግባባት ለተግባራዊነታቸው በቁርጠኝነት መነሳሳትን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በቅርቡ የተስተዋለው አለመረጋጋት በዘላቂነት ለማስወገድ ብአዴን የካበተው ልምድና አቅም አለው ያሉት አቶ ዓለምነው መላ የድርጅቱ አመራሮች፣ አባላትና ህዝቡ ከመስመሩ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ እስከ መስከረም 7 ቀን 2009 ድረስ በሚካሄደው የአመራር ኮንፈረንስ ላይ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከልማት ድርጅቶች የተውጣጡ ከ2 ሺህ የሚበልጡ ከፍተኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy