መንግስት የአገሪቷን ህልውና ለማስጠበቅና የሕዝብ ሠላም፣ ፀጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝርዝር ይዘት ይፋ አደረገ።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት፣ ይዘት፣ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የተከለከሉ ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሠዓት እላፊን የሚፈቅድ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ የሠዓት እላፊ ገደብ አልተጣለም።
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ እንደገለፁት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው በአሁኑ ወቅት አደጋ ላይ የወደቀውን የህዝቦችና የአገር ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ነው።
በአገሪቷ ሠላማዊ ሰልፍና ተቃውሞ ማድረግ በህገ-መንግስቱ የተፈቀደና ሲተገበር የቆየ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፤ በአሁኑ ወቅት የሚደረጉ ተቃውሞዎች የመጨረሻ ውጤት ሲታይ ሁከትና ብጥብጥ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
በህዝቦችና በሃይማኖቶች መሀከል የእርስ በርስ ግጭትና ብጥብጥ በመፍጠር በአገሪቷ በሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት በመደበኛ የህግ ማስከበር መከላከል ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገሪቷ እየታየ ያለው ሁከትና ብጥብጥ በመሳሪያና በደፈጣ የሚታገዝ በመሆኑ ይህንን ለመከላከል እንዲቻል አዋጁ አስፈላጊ ሆኗል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ ሁከትና ብጥብጡ በሰው ህይወት ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ የአገሪቷን የኢኮኖሚ አውታሮች በማውደም ዕድገቷን የሚያደናቅፍ ነው።
ሁከትና ብጥብጡ የዜጎችን ሰርቶ መግባትና በነጻነት መንቀሳቀስ የገታ፣ የህዝብ ጥያቄዎችን ጠልፎ ለእኩይ ዓላማ ያዋለ፣ በውጭ ኃይሎች እየተደገፈ የአገሪቷን ዕድገት የሚያደናቅፍበትና በመደበኛ የህግ ማስከበር የማይፈታበት ደረጃ የደረሰ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሁከትና ብጥብጡ የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ በመምጣቱ የአገሪቱ ህዝብ “መንግስት የለም” የሚል ጥርጣሬ ስለተፈጠረበት “መንግስት የለም” እስከማለት መድረሱን አስረድተዋል።
የተፈጠሩት ሁኔታዎች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያገኘች የመጣችውን ተሰሚነትና ሚና ወደኋላ የሚጎትት በመሆኑ ችግሮቹን መፍታት አስፈላጊ ሆኗል።
“በተጠቀሱት ምክንያቶች መንግስት የህዝቡን ፍላጎት መመለስና የአገሪቷን ህዳሴ ማሳካት የሚቻለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻ መሆኑን በማመኑ ይህንኑ አድርጓል” ብለዋል አቶ ጌታቸው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አራት ክፍሎችና 14 አንቀጾች ያሉት ሲሆን፤ የአዋጁ አስፈላጊነት፣ ይዘት፣ የሚወሰዱ እርምጃዎች፣ የተከለከሉ ጉዳዮችና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን አካቷል።
አዋጁን የሚያስፈጽምና በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ ኮማንድ ፖስትም ተቋቁሟል።