በሰበታ ሁከት ፈጣሪዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ40 ሺህ በላይ ሰራተኛን የያዙ 11 ፋብሪካዎችና 60 ተሽከርካሪዎች ወድመዋል
ዛሬ በአከባቢው ቅኝቱን ያደረገው ሪፖርተራችን ሳይገን ዲማ፣ ቱቱ ጨርቃጨርቅ፣ አባቦ ጉና፣ አባቦ ሀይላንድ እና ሮቶ ፕላስቲክን ጨምሮ በጠቅላላው 11 ፋብሪካዎች መቃጠላቸውን ታዝቧል።
ፋብሪካዎቹ ከ40 ሺህ በላይ ሰራተኛን የያዙ ሲሆን፥ አብዛኛዎቹም የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው ነው ፖሊስ የገለፀው።
ንብረትን በግፍ የማውደም ተግባሩ ቀጥሎ 62 የህዝብና የተቋማት ተሽከርካሪዎችን በከፊልና በሙሉ አውድመዋል።
ሪፖርተራችን በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩ ሰዎች በአከባቢው ብዙም የማይታወቁና ነዳጅና ጎማን ጨምሮ እንጨት በመያዝ ድርጊቱን ሲፈፅሙ እንደነበር እንዲሁም የሚንቀሳቀሱትም በተሽከርካሪ መሆኑን ነው የገለፁት።
ግለሰቦቹ ዛሬ ቀትር አጋማሽ ድረስ የንግድ ቤቶች እንዳይከፈቱና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ሲሯሯጡም ነበር።
ከወለቴ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የንግድ ቤቶች መዘጋታቸውንና የሰዎች እንቅስቃሴም ከወትሮ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ታዝበናል።
የጸጥታ ሀይሎችም በመስመሩ በመመላለስ የጽጥታውን ሁኔታ ሲቃኙም ነው የተመለከትነው።
የአከባቢው እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘው ከማክሰኞ ጀምሮ መሆኑንም ነው ነዋሪዎች የገለፁልን።
ማምሻው ላይ የተወሰኑ ንግድ ቤቶች እየተከፈቱ ሲሆን የሰዎች እንቅስቃሴም በከፊል ወደ ቀድሞ መልኩ በመመለስ ላይ ይገኛል።
የከተማው አስተዳደር ድርጊቱ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የተፈጸመ በመሆኑ ሁሉንም ጥፋቶች ለመከላከል አልተቻለም ነበር ብሏል።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ አራርሳ መርዳሳ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ችግሩን በቁጥጥር ስር ማዋል በመቻሉ ህብረተሰቡ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ እንዲመለስና ለዚህም አስተዳደሩ ሀላፊነት እንደሚወስድ ለጣቢያችን ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎች ግን ከዚህም ባለፈ መንግስት እነዚህን የጥፋት ሀይሎችን ለእያንዳዱ ጥፋታቸው ተጠያቂ እንዲያደርግ ነው ያሳሰቡት።
የሰበታ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ድርጊቱን ፈጻሚዎችን በመከታተል በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባሩን አሁንም እንደቀጠለና አጣርቶ ለህግ እንደሚያቀርብ ተናግሯል።
በሀይለኢየሱስ ስዩም