ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደ አዲስ አበባ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሥራ ተጠናቀቀ
– ሁለት ተርባይኖች ከግድቡ ኃይል ለማመንጨት በዝግጅት ላይ ናቸው
– ከባለሀብቶች ቃል የተገባው በበቂ ሁኔታ አልተሰበሰበም
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ያለፈውን ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በመገመገም አዲስ ዕቅድ አፅድቋል፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት ስምንተኛ መደበኛ ጉባዔውን በሸራተን አዲስ ሲያካሂድ፣ የምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች አመራሮቹና ሚኒስትሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደ አዲስ አበባ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የኢኮኖሚና ፋይናንስ ክላስተር አስተባባሪ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ እስካሁን የነበረው የግድቡ ሥራ እጅግ የተወሳሰበና መሠረት የመጣል መሆኑን አስረድተው፣ ግንባታው በታቀደው መሠረት እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገለጻ፣ ከአሁን በኋላ የቀረው ሥራ ቀላልና እምብዛም ብዙ ጊዜ የማይወሰድ ነው፡፡ ጎን ለጎን ግድቡ ከበለስ ጋር እንዲገናኝ መደረጉን፣ ከግድቡ ወደ አዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርም ተሠርቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሁለት ተርባይኖች ተከላቸው ተጠናቆ በቅርቡ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ ‹‹የግድቡ ሥራ እንደተባለው ለሰከንድም ሳይቋረጥ እየተካሄደ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የግድቡ ግንባታ በአንዳንድ ሚዲያዎች 70 በመቶ ደርሷል ተብሎ የቀረበውን ዘገባ መሠረት አድርገው አንዳንድ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ቀርበዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ ግን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 51 በመቶ ከፍ በማለት 54 በመቶ መድረሱን ያለፈው ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያመለክታል፡፡ 70 በመቶ የተባለው ያለፈው ዓመት የአፈጻጸም መጠን እንደነበር ተገልጿል፡፡
ከአንድ አባል የቀረበው ጥያቄ በሦስቱ ክልሎች (ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ) ለግድቡ የሚደረገው የሕዝብ ድጋፍ ከፍተኛ ሥራ የተሠራበትን ያህል፣ ከሌሎች ከተቀሩት ክልሎች (በተለይ ደግሞ አፋር፣ ኢትዮጵያ ሱማሌ፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ) እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አልተሠራም ተብሎ ቅሬታ የቀረበ ሲሆን፣ ከአንዳንድ ተወካዮች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኦሮሚያ ተወካይ፣ ባለፈው ዓመት ክልሉ በሁከትና በብጥብጥ ቢያሳልፍም እስካሁን ሦስት ዞኖችን ሳይጨምር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በአንድ ሠራተኛ አስተባባሪነት የሚሠራ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ተወካይ፣ ጽሕፈት ቤቱ በበቂ ደረጃ የሰው ኃይል የማደራጀት ችግር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ጽሕፈት ቤቱን ለማደራጀት እንደታሰበበት አስረድተዋል፡፡
በሪፖርቱ እንደቀረበው እስካሁን የኅብረተሰቡ አጠቃላይ ተሳትፎ 8.9 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የክልል ቅርንጫ ጽሕፈት ቤቶች በሚገባ ተደራጅተው እንዳልሠሩና በባለሀብቶች የተገባው ቃልም በአግባቡ እንዲሰበሰብ ባለመደረጉ በምክር ቤቱ አባላት ቅሬታ ቀርቧል፡፡
እንዲሁም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ስም የተዘጋጀው የሽልማት ዕጣ አሰጣጥ ችግር እንደነበረበት፣ የትንንሽ ዕጣዎች ዕድለኞች ከክልል ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንዲወስዱ መደረጉ አግባብ እንዳልነበረም ቅሬታ ተሰምቷል፡፡
ግድቡን በተመለከተ ደግሞ በሚዲያ በቂ የሆነ ቅስቀሳ አለመካሄዱን፣ የቦንድ ግዢና ሽያጭ የአመላለስ ችግር፣ የምክር ቤቱ አባላት በበቂ አለመሳተፍና ሌሎች ተመሳሳይ ቅሬታዎች ተነስተዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎች ከጉድለትም ቢሆን የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ካለው አነስተኛ የሰው ኃይልና ሙያተኛ አንፃር ጥሩ የሚባል ሥራ መሥራቱን የሚገልጹ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ በተመለከተም አንዳንድ ቅሬታዎች ተነስተዋል፡፡
በዚህ ዓመት የውጭ የቦንድ ግዢ መቀዛቀዝና በአሜሪካ አጋጠመ ተብሎ በተለይ በጋዜጠኛ ሚሚ ስብሐቱ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በአሜሪካና በሌሎች አገሮች የተካሄደው የቦንድ ግዢና ሽያጭ ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሜሪካ አንድ ተቋም ባቀረበው የሕግ ጥያቄ መሠረት በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የገዙት ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የቦንድ ሽያጭ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ ከአሜሪካ ሕግ ጋር በመቃረኑ ለባለቤቶቹ እንዲመለስ የተደረገው የቦንድ ሽያጭ ገንዘብ፣ የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መልሶ ለመሰብሰብ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም አክለዋል፡፡
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አደረጃጀትም የአወቃቀር ችግር እንደነበረበትና ሊያቅፋቸው የሚገቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች (በተለይ ሲቪል ማኅበረሰቡን) አለማካተቱን፣ አሁን ግን እንደ አዲስ በራሱ የመተዳደሪያ ደንብ እንዲኖረው በሒደት ላይ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በግድቡ ሥራ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ታይቷል ተብሎ ለቀረበው አስተያየት ምላሽ የሰጡት የውኃ፣ ኤሌክትሪክና መስኖ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ በአንዳንድ የውጭ ኃይሎች የሚወራ አሉባልታ መሆኑንና የግድቡ ግንባታ በጤናማ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ እስካሁን የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ያልፈረሙ አባል አገሮችን በተመለከተም አስረድተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከቦንድ ግዢ ጋር ተያይዞ የቀረበው ችግር በአስቸኳይ እንዲፈታና ግድቡ ተገንብቶ የሚጠናቀቅበት ግልጽ ዕቅድ እንዲኖር ጠይቋል፡፡ ‹‹አሁን ያለንበት ጊዜ ግድቡ ይጠናቀቅበታል በተባለው አምስተኛ ዓመት ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ ገና ግማሽ ላይ ነው፡፡ ግድቡ ተገንብቶ የሚያልቀው መቼ ነው? አለበለዚያ ግድቡ ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን እኛንም ይጨርሰናል፤›› በማለት ጠንከር ያለ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡
ዶ/ር ደብረ ጽዮን በሦስቱ አገሮች (በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ) እየተካሄደ ስላለው ድርድር አንስተው ጥያቄውን ሲመልሱ ግድቡ፣ ‹‹በማናለብኝነት ሳይሆን ከእነሱ ጋር ተግባብተንና ተረዳድተን እየሠራን ነው፡፡ ግድቡ የሚጠናቀቅበት ዕቅድም አለው፡፡ ምናልባት የውኃ ሙሌቱን ጊዜ በተመለከተ እንነጋገርበት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የቀረቡትን ማሳሰቢያዎችና ድክመቶች ተቀብለው፣ ለተያዘው ዓመት በቀረበው ዕቅድ የምክር ቤቱን ሐሳቦች በግብዓትነት በመጠቀም ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡ ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ ከመሥራትና ከቦንድ ግዢና ሽያጭ አመላለስ፣ እንዲሁም ከሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ጋር ተያይዘው የተነሱ ጉድለቶች መታረም ያለባቸው መሆናቸውን ተቀብለዋል፡፡ ‹‹ግድቡ ሕይወት የሚኖረው ሕዝቡ ሁሌም ሲነጋገርበትና የራሱ ሲያደርገው ነው፡፡ ሞቅ ቀዝቀዝ የሚለውን አካሄድ አርመን የሕዝቡን ግለት በጠበቀ ሁኔታ ነቅተን መሥራት ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡