Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአየር ኃይል ራዳርንና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅን በቦምብ ለማውደም ሲንቀሳቀሱ ተደረሰባቸው የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

0 754

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአየር ኃይል ራዳርንና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅን በቦምብ ለማውደም ሲንቀሳቀሱ ተደረሰባቸው የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

በቢሾፍቱ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ተማሪ በነበረ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል አማካይነት የአየር ኃይል ራዳርንና ቢሾፍቱ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅን በቦምብ ለማውደም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሲንቀሳቀስ ነበር የተባለ ግለሰብና 16 ግብረ አበሮቹ የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ይማር የነበረው ተከሳሽ ሙሉ በለጠ የኦነግ አባል ነው፡፡ በኮሌጁና በራዳሩ ላይ ጥቃት ለማድረስ ቦምብ ይዞ ሲንቀሳቀስ እጁ ላይ በመፈንዳቱ አንድ እጁ ተቆርጧል፡፡

ሙሉ በለጠ የተባለው ተጠርጣሪና ሌሎች 15 ተከሳሾች ድሪብሳ ዳምጤ በተባለ የኦነግ አባል የተመለመሉ መሆናቸውን የሚጠቁመው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ የድርጊቱ ዋና ጠንሳሽ ኑሮውን አሜሪካ ያደረገው ጃዋር መሐመድ መሆኑን ያብራራል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አንደኛ ተከሳሽ ያደረገው ድሪብሳ ዳምጤ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ወደ ጫካ በመግባት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና በመውሰድ ለመዘጋጀት ከጃዋር 50,000 ብር ተልኮለታል፡፡ ተከሳሹ ኔዘርላንድ ከሚገኝ የኦነግ አባልም 22,000 ብር ከተላከለት በኋላ አዲስ አበባ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤት ተከራይቶ እየኖረ፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞንና ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ፣ በአዲስ አበባና በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶችን በመመልመል የኦነግ አባል ማድረጉን ክሱ ያስረዳል፡፡

ድሪብሳ የተባለው ተከሳሽ ቢሾፍቱ ለሚኖር አንበሳ ጐንፋ ለተባለ የኦነግ አባል ስልክ በመደወል፣ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሚሠራና የኦነግ አባል በመሆን መሥራት የሚችል እንዲመለምልለት መጠየቁን የሚገልጸው ክሱ፣ በቢሾፍቱ አየር ኃይል ውስጥ ግራውንድ ቴክኒሻንና የጤና ባለሙያ (ሁለቱም በክሱ ተካተዋል) አባል መሆናቸውን በመግለጽ ደብረ ዘይት በሚገኘው ማቲ የእንግዳ መቀበያ ሆቴል ተገናኝተው በመመካከር፣ የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ መከፋፈላቸውን በክሱ ተገልጿል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ መንግሥት እየተጨቆነና እየተጨፈጨፈ መሆኑን ድሪብሳና ጐንፋ የተባሉት ተከሳሾች ከተወያዩ በኋላ፣ ሌሎች በክሱ የተጠቀሱትን ተከሳሾች ኦፋ የሚባል ጫካ ውስጥ ወስደው ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት፣ ዋቆ መርጋ የተባለው ተከሳሽና የአየር ኃይል ሠራተኛ የአየር ኃይል እንቅስቃሴን በጥናት እንዲያቀርብ ተልዕኮ እንደተሰጣጡ በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ተከሳሾቹ ከአየር ኃይል ራዳርና መከላከያ ኮሌጅ በተጨማሪ፣ በደብረ ዘይት በሚገኘው የሔሊኮፕተር ነዳጅ ማደያና የከተማው መናኸሪያ ላይ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ስምምነት ላይ መድረሳቸውም በክሱ ተጠቁሟል፡፡

ተከሳሾቹ ሙሉ ትኩረታቸውን ቢሾፍቱ በሚገኘው አየር ኃይልና የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ላይ በማድረጋቸው፣ የድርጊቱ ዋና ተዋናይ ያደረጉት በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ተማሪ የነበረው የኦነግ አባል መሆኑ የተገለጸው ሙሉ በለጠ ቢሆንም፣ ዕርምጃውን ለመውሰድ በመንቀሳቀስ ላይ እያለ ቦምብ እጁ ላይ በመፈንዳቱ መጎዳቱንና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሊውል መቻሉንም ክሱ ያስረዳል፡፡

እጁ ላይ በፈነዳው ቦምብ አንድ እጁ የተቆረጠው ተከሳሹ መከላከያ ሆስፒታል ተኝቶ በመታከም ላይ እያለ፣ በሆስፒታሉ የምትሠራ ሌሊሳ መርጋ የተባለች ሌላዋ ተከሳሽ፣ ሚስጥር እንዳያወጣ አሳምና እንድታስመልጠው የተደረገው ቅንብርም ሳይሳካ መቅረቱን ክሱ ይገልጻል፡፡

ተከሳሾቹ በቢሾፍቱ በሚገኘው አየር ኃይል ምን ያህል አውሮፕላኖች እንዳሉ፣ የጥበቃውን ሁኔታ፣ ያለው የጦር መሣሪያ ብዛት፣ የወታደራዊ መኮንኖች ብዛት፣ የጦር ኃይሉ ብዛት፣ ያሉ ራዳሮችና ሌሎች መረጃዎችን የማጥናት ተልዕኮ ለተሰጠው ሐንቢሳ ጎንፋ ለተባለው ተከሳሽ መረጃ የተላለፈለት ቢሆንም፣ ምኞታቸው ሳይሳካ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው ዕቅዳቸው መክሸፉ ተገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ የመጀመሪያ ዓላማቸው የአየር ኃይል ራዳርንና መከላከያ ኢንጂነሪንግን ለማውደም ቢሆንም፣ በቀጣይ ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ አውሮፕላን ለመምታትና በመንግሥትና በግል ተቋማት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንደነበሩም ተጠቅሷል፡፡

በተለይ በዱከም ከተማ ውስጥ ሆነው ለመንግሥት መረጃ ይሰጣሉ ባሏቸው ባለሀብቶችና ተቋሞቻቸው ላይ ጥናት አጠናቀው፣ በኢሜይል ውጭ ላሉ የኦነግ አባላት ጭምር ለመላክ ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ ቢሾፍቱን ዓላማ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦነግ አባላት ቡድን ወጣቶችን በመመልመልና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሥልጠና በመስጠት፣ ለጥፋቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በማቅረብ፣ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ትዕዛዞችን በመቀበልና ጥቃቱን ለማድረስ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማቅረብ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ድርጊቱን ከመፈጸማቸው በፊት ስለተደረሰባቸውና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 35፣ 38፣ 32(1ሀ)ንና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4ን በመተላለፋቸው የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ክሱ ያስረዳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ ክሱን በንባብ ካሰማቸው በኋላ ጠበቃ ለማቆም አቅም እንደሌላቸው ለገለጹት ተከሳሾች፣ የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ጠበቃ እንዲመድብላቸውና በግላቸው ጠበቃ ማቆም የሚችሉት ተማክረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ለመጠባበቅ ለጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy