CURRENT

በቶሮንቶና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ብሄር ብሄረሰብ ኮሚዩኒቲ መሪዎች በትውልድ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ያወጡት የአቋም መግለጫ

By Admin

October 14, 2016

ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ. ም በቶሮንቶና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ብሄር ብሄረሰብ ኮሚዩኒቲ መሪዎች በትውልድ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ያወጡት የአቋም መግለጫ በቶሮንቶና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ብሄር ብሄረሰብ ኮሚዩኒቲ መሪዎች በትውልድ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በስፋትና በጥልቀት ከተወያዩ በኋላ ለኢትዮጵያ መንግስት፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለተቃዋሚዎች እንዲሁም አገራችንን ኢትዮጵያን ማተራመስ ለሚፈልጉ ለውጭ ጠላቶች ከዚህ በታች የሚከተለውን የአቁም መግለጫ አውጥተዋል። በመጀመሪያ መንግስት በኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ በተለመው የተሀድሶ ዕቅድ መሰረት ላለፉት ሁለት አሰርት አመታት የአገራችንን ኢኮኖሚ በሁለት አሀዝ በማሳደግ፣ እንዲሁም ከራስዋም የተደላደለ ፀጥታ አልፋ የሌሎች ሀግራትን ፀጥታ በማስከበር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላም የማስከበር ስራ የጎላ ድርሻ ያበረከተች አገር መሆኗ የማይካድ ሀቅ ነው። ዳሩ ግን ይህ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት የማይመቻቸው ስትራቴጅካዊ የዘወትር ጠላቶቻችን የኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ማደግ ለህልውናችን ያሰጋናል በሚሉ የጠላቶቻችን ስልታዊ አካሄድ የመንግስታችንን የመልካም አስተዳደር ድክመትና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ምክንያት የተነሳውን የህዝባችንን ህጋዊ ጥያቄ ተንተርሰው በመግባት በብዙ ዋጋና ልፋት የተገኘውን መሰረተ ልማት ተቋማት በማውደም ላይ ይገኛሉ። ስለዚህ ይህ እድገታችንን ተከትሎ የመጣውን የህዝብ ጥያቄና መንግስታችን ያመነበትን የመልካም አስተዳደርና ሙሰኝነት ችግሮች ካጤንን በኌላ እና የጠላቶቻችንን ስልታዊ ከፋፋይ እና አውዳሚ የጥፋት ሀይል ለያይተን በማየት የውስጥ ችግራችንና ድካማችንን በሰላማዊ መንገድ ከህዝብና ከመንግስት ጎን ሆነን ለመፍታት ጠላቶቻችንን ደግሞ በፍፁም የኢትዮጵያዊነትና ታሪካዊ አንድነት ለመዋጋት እንደምንፈልግና ከህዝብና ከመንግስት ጎን ለመቆም የተስማማንበትን የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው አውጥተናል። 1ኛ/ የውስጥና የውጭ ፀረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች የተጀመረውን አንፀባራቂ የልማት ጉዞ ለመቀልበስና አገሪቱን ለማፈራረስ ባካሄዷቸው ሁከቶች በሲቪሉ ህዝብና በፀጥታ ሀይሎች ላይ በደረሰው የህይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት የተሰማንን ከፍተኛ ሀዘን እንገልጻለን፡፡

2ኛ/ የኢትዮጵያ መንግስት በብዙዎች መስዋእትነት የተገኘውን የብሄር ብሄረሰብ እኩልነት በመልካም አስተዳደር ብልሹነትና በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያየ ጊዜ ከተለያየ የኢትዮጵያ ክልሎች ለዘመናት ተከባብረው በሰላም ይኖሩበት ከነበረው መኖሪያቸው በብሄር ማንነታቸው ምክንያት በመፈናቀላቸው በቶሮንቶና አካባቢዎቹ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እጅግ በጣም አዝነናል። ሰለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት በያዘው ጥልቅ ተሀድሶ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የመኖርና የመስራት ህገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው ተከብሮላቸው በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ አናሳስባለን። 3ኛ/ ውድ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍትሀዊ ጥያቄዎቻችሁ የእኛም ጥያቄ ናቸው፡፡ እኛም ከእናንተ ጎን እንቆማለን። ዳሩ ግን ይህን ፍትሀዊ ጥያቄያችሁን ተንተርሰው በውጭ ሀይሎች ተልከው ሰርገው የገቡና የጋራ ጠላታችንን ድህነትን ለመቀነስ ታስቦ የተገነቡትን የልማት ተቋማት በማውደም፣ የዘርና የሃይማኖት ግጭቶችን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ለመክተት የተላኩ ፅንፈኞች ስላሉ ስላማዊና ህጋዊ የህዝብ ጥያቄን ከጥፋት መልእክተኞች ነጥለን በጋራ እንድንታገላቸው እንጠይቃለን። 4ኛ/ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ለምትሉ ህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገራችን ኢትዮጵያን ከአመፅና ከእርስበርስ ጦርነት ለመከላከል እና በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የህዝብን ህይወትና ንብረት ለማዳን የሚያስችል ሰላማዊ ትግል በማድረግ ኢትዮጵያን ከሁከት፣ የእርስ በርስ ግጭትና የህዝብ ንብረት ውድመት ለመታደግና ብሄራዊ አንድነትን በማስጠበቅ ከህዝብና ከመንግስት ጎን ቆማችሁ በሰላማዊ ትግልና በውይይት እየታገላችሁ ሀገራዊ ድርሻችሁን እንድትወጡ በአክብሮት እንጠይቃለን። 5ኛ/ አገራችን ኢትዮጵያ ለማተራመስ ገንዘብ እና የተለያዩ ቁሳዊ እርዳታዎች ከጠላቶቻችን በማግኘት በኢትዮጵያ ህዝብንና መንግስትንና ህዝብንና ህዝብን ለማጋጨት እንዲሁም የሀይማኖት ጦርነትን ለማምጣት በግልፅና በስውር የምትሰሩ የግብፅና የሻእቢያ ተላላኪዎች የሆናችሁትን ግንቦት ሰባት እና ኦነግ የምትባሉትን ፀረ ህዝብ ቡድኖችን ታሪካዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም ልንዋጋችሁ ቃል እንገባለን። 6ኛ/ በሶሻል ሚዲያ ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጭ ችግርን ከመጠን በላይ አጋኖ የሚያቀርብ ያልተፈጠረን ነገር ተፈጥሯል ብሎ አሉታዊና የጥላቻ ስሜት ኮርኳሪ ዜና በማሰራጨትና በሌላ አፍሪካ አገር የተፈጠሩትን ምስሎችና ቪድዮዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደተፈፀመ አድርገው የዘር፣ የጎሳና የሀይማኖት ጦርነትን የሚያነሳሱትን የሶሻል ሚድያ ድህረገፃች እና ግለሰቦች የኢትዮጵያን ህዝብ ከድጡ ወደማጡ ስለሚከት ከዚህ እኩይ ስራቸው እንዲታቀቡ እናሳስባለን። ይህንም ግላዊና ማህበረሰባዊ እኩይ የሳጥናኤል ስራ አጥብቀን እናወግዛለን። 7ኛ/ የመንግስት ተቋማት፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ያላችሁ የኢትዮጵያ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ መምህራንና ወላጆች በህዝብና በመንግስት መካከል ያሉትን ልዩነቶች በማጥበብና የህዝብ ተቋማትን ከውድመት በመከላከል ብሄራዊ የጋራ ጥቅምን በማስጠበቅና ዘላቂ መፍትሄ በማምጣት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በጥብቅ እንጠይቃለን። 8ኛ/ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በመካሄድ ባለው ሁኔታ መንግስት አስፈላጊውን ጥያቄ በመቀበል በአፋጣኝ ለህብተረሰብ ወይም ለህዝብ ምላሽ ለመስጠት ያስቀመጠውን የተሀድሶ እንቅስቃሴ እንዲያፋጥን እንጠይቃለን፡፡ 9ኛ/ መንግስት በራሱ ውስጥ ብልሹ አሰራር እና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ መነሳቱን እና የጀመረውን የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንዲያስቀጥልና እንዲያጎለብት የበኩላችንን አሰተዋጽኦ ለማድርግ ቃል አንገባለን፡፡ 10ኛ/ የኢትዮጵያ መንግስት ለተጠየቁት የህዝብ ጥያቄዎች በታሳቢነት በአስቸኮይ መልስ እንዲሰጥ እንዲሁም በሀገራችን ውስጥ በመታየት ላይ ያለውን የንብረት ማውደም ዘመቻ እና በህዝብ ተቋማት እና ሀይማኖት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያስቆም እየጠየቅን፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስደውን ትክክለኛ እርምጃዎች እንደምንደግፍ እናረጋግጣለን። 11ኛ/ በመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት በማድረግ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ የጥፋት ሀይሎች የግልና የመንግስት እንዲሁም የህዝብ መገልገያ ተቁማት የማፍረስና የማቃጠል ተግባራት በፅኑ እንቃወማለን፡፡ 12ኛ/ በሀገር ውስጥ ያሉ የጥፋት ሀይሎችና በውጭ የሚኖሩ ፅንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ኢትዮጵያ ሀገራችን እያካሄደች ላለው የፀረ ድህነት እንቅስቃሴ የውጭ መንግስታት ድጋፍ እንዳያደርጉ የሚካሄዱትን ቅስቀሳ እናወግዛለን ። 13ኛ/ የካናዳ መንግስት የፀረ-ሰላም ሀይሎች እያሰራጩ ያሉትን አገር የማፍረስ ፕሮፖጋንዳ ባለመቀበል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማትና የዲሞክረራሲ ስርአት ግንባታ በቀጣይነት እንዲደግፍ እና በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩሉን ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ አበክረን እንጠይቃለን ። 14ኛ/ በውጭ አገራት የሚገኙ ፅንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ሀገሪቱን ወደ አለመግባባት ለመምራት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያስራጩአቸውን ከእውነት የራቁ የጥፋት ፕሮፓጋንዳዎች አጥብቀን እንቃወማለን ። ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!! በቶሮንቶና አካባቢዉ የሚኖሩ የኢትዬጵያ ብሄርና ብሄረሰብ ኮሚዩኒቲ መሪዎች ቶሮንቶ /ካናዳ/ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 13 ቀን 2016 (ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ.ም)