CURRENT

በኢትዮጵያ ሁከት እንዲቀጥል የሚቀሰቅሱ የግብጽ ተቋማት የሀገሪቱ መንግስት ያቋቋማቸውና የሚደግፋቸው መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ

By Admin

October 11, 2016

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ሁከቶችን ተከትሎ በሀገሪቱ ሁከቶች እና አለመረጋጋቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚቀሰቅሱ ሀሳቦች የሚንጸባረቁባቸው የግብጽ ተቋማት የሀገሪቱ መንግስት የደገፋቸው እና ያቋቋማቸው መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህም በግብጽ መገናኛ ብዙሃን የሚንጸባረቁ አቋሞች የመንግስትም ስለመሆናቸው ማሳያም ነው ብለዋል ያነጋገርናቸው አንድ ምሁር።

በኢትዮጵያ ተፈጥረው ከቆዩ ሁከቶች ጀርባ በግብጽ መንግስት ድጋፍ የሚያገኙ ተቋማት እና ቡድኖች እጃቸው አለበት የሚሉ ምሁራን ባለፈው ሳምንት በመገናኛ ብዙሃን ተሰምተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን ሲከፈቱ ባደረጉት ንግግር ላይም የግብጽ መንግስት ተቋማት በዚህ ላይ ሚናቸው እንዳለ አረጋግጠዋል ።

ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ዘገባዎች ሲሰሙ ከግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ ጽህፈት ቤት ጉዳዩን የሚያስተባብል፤ ካይሮም ከኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ምንም እንደማትጠቀም የሚያሳይ መግለጫ ተሰምቷል።

ሆኖም ከሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የሚሰማው ግን ተቃራኒው ነው።

ከፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ማስተባበያዎች ይሰሙ እንጂ በግብጽ ከፍተኛ የፖሊሲ ተጽእኖን በማሳረፍ ከሚታወቀው “አል አህራም ሴንተር ፎር ፖሊቲካል ስትራቴጂክ ስተዲስ” ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሚና ጦኤል የሚሰማው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው።

እሳቸው አልቃድ አልረቢ ከተባለ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅም ሆነ ከሌሎቹ የግብፅ ምሁራን እንደሚሰማው በኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት ብሄሮችን አማርጦ ስለመጠቀም ሲተነትኑ ከሰሞኑ ተሰምተዋል ።

ኢትዮጵያ አባይን ተጠቅማ እንዳትለማ የሚያስችሉ ቀመሮችን በመስራት በግብጽ ውስጥ ያሉ የጥናት ተቋማት ዋናውን ድርሻ እንደሚጫወቱ ይነገራል፤ አል አህራም ሴንተር ፎር ፖሊቲካል ስትራቴጂክ ስተዲስ በእነዚህ ውይይትች በዋነኝነት ስሙ ይነሳል።

ለመሆኑ ይህ ተቋም ማነው…?

በፈረንጆቹ በ1968 አል አህራም ፋውንዴሽን በተባለ ማእቀፍ ውስጥ እንደተመሰረተ የሚነገርለት ይህ ተቋም በጸረ-ጺዮናዊነት ላይ ጥናቶችን ይሰራ እንደነበር ስለተቋሙ የተጻፉ ፅሁፎች ያስረዳሉ።

በአባይ ወይንም በናይል ተፋሰስ ላይ ግብጽ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መነሻ ሀሳብ የሚሰራበት እንደሆነም ይነገራል።

ለስድስት ዓመታት በካይሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዲፕሎማትነት ያገለገሉትና የግብጽ ኢኮኖሚ እይታ ከአባይ ወንዝ አንጻር የሚል መጽሀፍን የጻፉት አቶ ግርማ ባልቻም ይህን ያረጋግጣሉ።

አል አህራም ሴንተር ፎር ፖሊቲካል ስትራቴጂክ ስተዲስ ስለ ማንነቱ የሚገልጸው ጽሁፍ ከመንግስት ያልሆነ እና ነጻ ሆኖ የተቋቋመ እንደሆነ እንዲሁም የተቋሙ ምሁራን በግብጽ መገናኛ ብዙሃን ሀሳባቸውን ሲያቀርቡ ከመንግስት ተጽእኖ ነጻ መስለው ነው የሚናገሩት ይላሉ።

እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ ስለዚህ ተቋም በቅርበት የሚያውቁም አል አህራም ሴንተር ፎር ፖሊቲካል ስትራቴጂክ ስተዲስ በስሩ ላቀፋቸው ምሁራን መንግስት የገንዘብ ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ።

አቶ ግርማ ከሆነ ይህ የጥናት ተቋም ለስራው ባህሪ ሲባል አደረጃጀቱ ይለይ ይሆናል እንጂ ከመንግስት ጀርባ አለ መንግስትም ከሱ ጀርባ አለ ይላሉ።

ከአል አህራም ሴንተር ፎር ፖሊቲካል ስትራቴጂክ ስተዲስ ምሁራን ከሚሰሙ ትንተናዎች ኢትዮጵያ ግብጽን አስመልክቶ የምትከተለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማየት ይቻላል ።

ፖሊሲው በግብፅ ትኩረቱ ኢኮኖሚ ላይ ሳይሆን ፖሊቲካ ላይ የሚሰራ መንግስት ሲመጣ በናይል ወንዝ ላይ ተስማምቶ ለመስራት አዳጋች መሆኑን ያስቀምጣል።

አሁን ያሉት ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ በኢኮኖሚ ትኩረታቸው መልካም ስም ቢኖራቸውም፤ መንግስታቸው የሚደግፋቸው ተቋማት ግን አባይን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጡት ሀሳብ አልተቀየረም።

በውስጣቸው ያሉ ምሁራን የሁልጊዜ ትንተናቸውም ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ መጠቀም ስለሚፈልጉት አኮረፈ የሚሉት ብሄር ተኮር ቡድን ነው።

አቶ ግርማ እንደሚሉትም፥ ኢትዮጵያ አባይን አልምታ እንዳትጠቀም የሚያስችሉ ስልቶች የሚነደፉት በእነዚሁ መንግስት ካቋቋማቸው እና ከሚደግፋቸው ተቋማት ነው።

እንደ አቶ ግርማ ከሆነ አሁን ላይ በግብጽ መገናኛ ብዙሃን እየተንጸባረቁ ያሉ አቋሞችም የመንግስት አይደሉም ለማለት የሚያስችሉ ማሳያዎች የሉም። የካይሮ ተቋማት ስልት ደግሞ ከምእራባውያን ይለያል ባይ ናቸው።

በካሳዬ ወልዴ