Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የኢትዮጵያ ምርጫ ህግ ይሻሻላል – ፕሬዚዳንት ሙላቱ

0 551

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ አመት የስራ ዘመን ዛሬ ተከፍቷል።

ከመክፈቻው በፊትም በቅርቡ በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ በነበረው ሁከት እና ግርግር እንዲሁም በአንዳነድ የሃገሪቱ አበበቢዎች ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

የምክር ቤቶቹን የስራ ዘመን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳነት ሙላቱ ተሾመ፥ ባለፈው ዓመት ሃገሪቱ በብዙ መስኮች ወደፊት ከመራመዷ ጎን ለጎን የተለያዩ ችግሮች የተከሰቱበት ወቅት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሁከቶችና ግጭቶች መቀስቀሳቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፥ በዚህም የበርካታ ዜጎችና የጥታ ሃይሎች ህይዎት መጥፋቱን ተናግረዋል።

ሃገሪቱ ባለፉት አመታት የገነባችው ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እንዳስቻላት ጠቅሰው፥ በዚህ መስክ የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጎልበትና የፖለቲካ ምረሩን ለማስፋት በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጉን የማሻሻል ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ያጋጠሙ ችግሮች፦ ሃገሪቱ ባጋጠማት የድርቅ አደጋ ሳቢያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለርሃብ ከመጋለጣቸው ባሻገር በእንስሳት ሃብቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ጠቅሰው፥ መንግስት ችግሩን በራስ አቅም ለመፍታት ባደረገው ጥረት ሊደርስ ይችል የነበረን ሰብዓዊ ቀውስ ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም መንግስት በራስ አቅም ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት ለጋሽ ሃገራት ከሰጡት እርዳታ ጋር ተዳምሮ የድርቁ አደጋ በዜጐች ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንዲያልፍ ማስቻሉንም ነው የተናገሩት።

በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶች

ወቅታዊውን የሃገሪቱን ሁኔታ ባነሱበት ንግግራቸው፥ በህብረተሰቡ ዘንድ የተነሱ ፍትሃዊ ጥያቄዎችን ተገን በማድረግ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች ቅሬታን ወደሁከትና አውዳሚ እንቅስቃሴ ለመቀየር መረባረባቸውን ተናግረዋል።

በንግግራቸው ሃገሪቱ በእድገት ጎዳና መገስገስ መጀመሯን አንስተው፥ ይህን የማይደግፉ አንዳንድ ሃይሎች ሃገሪቱን ለማተራመስ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ለበርካታ ዓመታት አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖባት በቆየችው ሃገር የተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች የተሳተፉባቸው ሁከቶችና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም የወጣቶችና ሌሎች ዜጎች እንዲሁም የፀጥታ ሃይሎች ህይወት መጥፋቱን አንስተዋል።

በዚህ ሳቢያም የዜጎች የዕለት ተዕለት እንቃሴ መስተጓጎሉንም ነው የተናገሩት፤ ችግሩን ለመፍታት የተሟላ የመፍትሄ ሃሳብ በማዘጋጀትና ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው መሆኑን በመጥቀስ።

በተለይም ግዙፍ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች በራስ አቅም መገንባት መጀመራቸው ያልተዋጠላቸው እነዚህ ሃይሎች ሃገሪቱን ለማተራመስ በቀጥታ እየተረባረቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በዚህም በሃገሪቱ በአሸባሪነት የተፈረጁት ኦነግና ግንቦት ሰባት ከግብፅ መንግስትና ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለሃገሪቱ ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ያላቸውን ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች ተቋማት በማጋየት ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል ነው ያሉት፡፡

እነዚህ ሃይሎች በቅርቡ ታላቁን የኢሬቻ በዓል ከማወክ ጀምሮ በልዩ ልዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያካሄዱት ውድመትና ቃጠሎ በማንኛውም ሚዛን ፍትሃዊነት የሌለው መሆኑንም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

በመሆኑም መንግስት ይህን የመሰለው አፍራሽና ከባድ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ታዝሎ የመጣ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እንዲመከትና ወንጀለኞቹም በጥብቅ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ለዚሁ ሲባልም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታውን ገምግሞ ተግባራዊ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡

ግብርና እና ኢንዱስትሪ

ሃገራዊ እድገቱን ለማስቀጠል ትልቅ ፋይዳ ባለው የግብርና ኘሮግራም ላይ ዘንድሮም ልዩ ትኩረት እንደሚደረግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፥ ጥሩ እድገት ሲያሳዩ የቆዩ የግብርና መስኮችን ለላቀ ውጤታማነት ለማብቃት መቀሳቀስ እንደሚገባ አንስተዋል።

በተለይም በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና በሰብል ምርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ የሰብል ምርት ካለው ፋይዳ አንጻር በሙሉ አቅም አነረባረባለን ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ከፍተኛ ዋጋ ወዳላቸው ምርቶች ለማሸጋገር ቅድመ ሁኔታ የማሟላት ጉዳይ በእቅዱ መሰረት ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

ለዚህም በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ የሚለሙ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ደኖችና የእንስሳት ሃብት ልማት ተግባራዊ ይደረጋል።

ከዚሁ ጋር ተመጋጋቢ እንዲሆን የሚፈለገው ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማስፋፋት ልዩ ልዩ ኘሮጀክቶች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሲሆን፥ በዚህ ረገድ በዋና ዋና ማዕከላት ላይ የሚነቡ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ሃገራዊ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ካላቸው ተሳትፎ ባሻገርም፥ የውጭ ባለሃብቶች ለሃገራዊ ልማት ስትራቴጅው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም በሃገሪቱ ኢንዱስትሪያዊ ልማትን በማፋጠን ለማምጣት የሚፈለገውን ሽግግር አስተማማኝ ለማድረግ ለገጠር ኢንዱስትሪ ልማት የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች፦ የሲቪል ሰርቪሱን ጨምሮ ሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡

የሃገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ ከእድገቱ ጋር ተመጋጋቢ በሆነ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ እንዲሄድ ለማድረግ በየወቅቱ የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያ ይደረጋል፡፡

የምርጫ ህጉን ስለማሻሻል፦ ባለፈው ምርጫ የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት በመስተዋሉ ምክንያት በሃገሪቱ ምክር ቤት ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጐት ያላቸው ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

ይህን የመሰለው ሁኔታ ስርዓቱን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ፥ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የህዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማሻሻልም ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጉ የሚሻሻል ጉዳይ ይሆናል፡፡

ሃገሪቱ የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ ሃገራት እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የህግ ማሻሻያ ይደረጋል፡፡

ስለሆነም የምርጫ ህጉ የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል የሚደረግ ይሆናል፡፡

የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ በሚደነግገው መሰረት በሁሉም ክልሎች ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች በተቻለ ፍጥነት የተሟላ እልባት እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡

በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የአስተዳደር አካላት በየክልላቸው የሚገኙ እውቅና ያልተሰጣቸውን ማህበረሰቦች ጉዳይ በአፋጣኝና በማያዳግም ሁኔታ የሚያስተካክሉ ይሆናል።

ከዚህ ባለፈም በዘንድሮው ዓመት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣውን አዋጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች የሚወጡ ይሆናል፡፡

የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ ይቋቋማል

መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ፓኬጆችን ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን አንስተው፥ በአፈጻጸም ጉድለትና በተለያዩ ምክንያቶች ግን የታሰበው እቅድ አለመሳካቱን ጠቅሰዋል።

የወጣቱን የኢኮኖሚ ፍላጎትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግ፥ ወጣቱን በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን ባሳተፈ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ወጣቶች የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያም ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋ እንዲሄድ ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ለዚህም የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የፕሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባት ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው፥ በተያዘው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል ብለዋል፡፡

ለፈንዱ ማቋቋሚያ አሥር ቢሊየን ብር የተመደበ ሲሆን፥ የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል ተብሏል፡፡

ኘሮግራሙ በየጊዜው እየተገመገመ አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድበት እንዲሆን ይደረጋልም ብለዋል በንግግራቸው፡፡

የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተመለከተ

የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መነሻ በማድረግና ከልብ በመቀበል መንግስት ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማፅዳት ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ከዚህ በመነሳት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስራውን በሚጀምርበት በሚቀጥለው ወር የፌደራል መንግስትን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል፡፡

በዚህ መሰረት የመንግስት ስልጣንን ካለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ የሚገታና በውጤት አልባነት የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ የመንግስት ምክር ቤት የማደራጀት እንቅስቃሴ ይካሄዳል፡፡

የአርሶ አደሮች መፈናቀል

በከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች የተከሰተው የአርሶ አደርና የአርብቶ አደሮች መፈናቀል ከሃገራዊ እድገቱ እና እየተስፋፋ ካለው የኢንዱስትሪና ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዘ መሆኑንም በንግግራቸው አንስተዋል።

በመሆኑም ዘመናዊ እርሻዎችና ትልልቅ ግድቦች መስፋፋታቸው ቀጣይ በመሆኑ፥ ሁኔታውን ከአርሶና አርብቶ አደሩ መብትና ጥቅም ጋር በተጣጠመ አኳኋን መፈፀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተያዘው አመት ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል አቅጣጫ በመያዝ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለማስፋት ትኩረት ጠጠጠው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይ ደግሞ አይቀሬ ከሆነው የከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ የገጠር መሬትን ለላቀ ጥቅም ለማዋል የሚደረግ እንቅስቃሴ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን መሰረታዊና ታዳጊ ጥቅሞች አሳልፎ በማይሰጥ መንገድ እንደሚፈፀም ይረጋገጣል፡፡

በዚህ ረገድ ክፍተት ያለባቸውን ነባር ህጎችና አሰራሮች በማስተካከል፣ በአፈፃፀም የሚታዩ ስህተቶችን ታግሎ በማረም፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን

በማዘጋጀትና ከሁሉ በላይ ደግሞ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በሚያሳትፍ አኳኋን እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ለሃገራዊ እድገቱ ካበረከቱት አስተዋፅኦ በላይ አላግባብ የመጠቀም አዝማሚያ የተጠናወታቸው ጥቂት ኃይሎች በመኖራቸው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ሊፈተሽ የሚገባው መሆኑን ነው ያነሱት ፕሬዚዳንት ሙላቱ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy