Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በውጤታማነት እንደቀጠለ አስታወቀ

0 923

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በውጤታማነት እንደቀጠለ አስታወቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2009
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በውጤታማነት መቀጠሉን የግንባሩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በግምገማ ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱን በጥልቀት ለማደስ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣም ህዝቡ የተለመደ ገንቢ ሚናውን በመጫወት የለውጡን ሂደት የማይቀለበስ ደረጃ ላይ እንዲያደርስ ጥሪውን አቅረቧል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከጥቅምት 14 እስከ 17 ቀን 2009 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን ማካሄዱን ጠቅሶ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ማምሻውን ለኢዜአ መግለጫ ልኳል፡፡ በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት መግለጫ እንደተመለከተው፤ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች የቀረቡለትን በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ አፈፃፀም ሪፖርቶች በዝርዝር ተመልክቶ ሂደቱ በተቀመጠለት አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ ብሄራዊ ድርጅቶች ባለፉት አስራ አምስት የተሃድሶ ዓመታት በየክልሉ ያከናወናቸውን ስኬታማ ተግባራትና በሂደት ተፈጽመው የህዝብን ምሬት ያስከተሉ ችግሮችን በዝርዝር በመገምገም በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተሟላ መግባባት ላይ መድረሱም ተገልጿል፡፡ ኢህአዴግና አባል ብሄራዊ ድርጅቶች ልማትን፣ ዴሞክራሲና ሰላምን ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት መጓዛቸውን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አመልክቶ፤ በአገሪቷ ለሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቀ ፈጣን እድገት መመዝገብ መቻሉን መግለጫው ጠቁሟል። በዚህም ቀደም ሲል ለዘመናት የተሄደበትን የማሽቆልቆል ጉዞ በአስተማማኝ ደረጃ በመቀልበስ ወደፊት መራመድ መቻሉን ገልጿል። ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለፉት የተሃድሶ አመታት በአገሪቷ የተመዘገቡ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ድሎች እንደተጠበቁ ሆኖ በአመራር የአሰራር ጉድለቶች ምክንያት የታዩ ችግሮች ስርዓቱ ለአደጋ መጋለጥ ጀምሮ እንደነበርም በግምገማው አረጋግጧል፡፡ ይህም በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ወቅታዊና መሰረታዊ ሆኖ የተከሰተበት አይነተኛ ምክንያትም መሆኑን ጠቁሟል። ድርጅቱን በጥልቀት ለማደስ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣ ህዝቡ የተለመደውን ገንቢ ሚና በመጫወት የለውጡን ሂደት የማይቀለበስ ደረጃ ላይ እንዲያደርሰው ጥሪውን ማቅረቡ በመግለጫው ተመልክቷል። ኢህአዴግና አባል ድርጅቶች ድክመቶቻቸውን በዝርዝር ገምግመው ራሳቸውን ለማስተካከል የጀመሩት እንቅስቃሴ ከመላ አባላትና ከህዝብ ተሳትፎ ውጭ ይሳካል ተብሎ እንደማይገመት የገለጸው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ብሄራዊ ድርጅቶች በከፍተኛ አመራር ደረጃ የጀመሩት ራስን የማጥራት እንቅስቃሴ በየደረጃው ባሉ አመራር አባላት፣ በአባላትና በህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደረግም አብራርቷል። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ራስን በራስ ከማረም ጎን ለጎን ዓመታዊ የልማትና የዴሞክራሲ ተግባሮች በላቀ ትጋት እንዲፈፀሙ ለማድረግ በልዩ ትኩረት ለመረባረብ መዘጋጀቱንም አመልክቷል፡፡ ግምገማውን መሰረት በማድረግ የሰው ሀይል ምደባ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ያሳሰበው መግለጫው፤ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግስት የአመራር ምደባ በውጤታማነት ላይ ተመስርቶ ማስተካከያ በማድረግ ዓመታዊ ስራው በተጠናከረ አቅጣጫ እንዲፈፀም ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክቷል። የመግለጫው ሙሉ ቃል ቀርቧል ከኢህአዴግ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በውጤታማነት እንደቀጠለ የግንባሩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በግምገማ አረጋገጠ፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከጥቅምት 14-17/2009 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች የቀረቡለትን በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ አፈፃፀም ሪፖርቶች በዝርዝር ተመልክቶ ሂደቱ በተቀመጠለት አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ባለፉት አስራ አምስት የተሃድሶ አመታት በአንድ በኩል በየክልሉ ያከናወናቸውን ስኬታማ ተግባራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሂደት የተፈፀሙና የህዝብን ምሬት ያስከተሉ ችግሮችን በዝርዝር በመገምገም በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተሟላ መግባባት ላይ ደርሶባቸዋል፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግና አባል ብሄራዊ ድርጅቶች የህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄ የሆኑትን ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡ በአገራችን ለሩብ ምዕተ አመት የዘለቀው ፈጣን እድገት ቀደም ሲል ለዘመናት የተጓዝንበትን የማሽቆልቆል ጉዞ በአስተማማኝ ደረጃ ቀልብሶ ወደፊት እንድንራመድ አስችሎናል፡፡ ለሃያ አምስት አመታት አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም መገንባት ጀምረናል፡፡ መላ የአገራችን ህዝቦች አገራቸውን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ትግል የተመዘገበው ይህ ውጤት ህብረተሰባችን ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የመልማትና የማደግ እድል እንዲጎናፀፍ አስችሎናል፡፡ ባለፉት በርካታ አመታት የተካሄደውን ትግልና የተመዘገቡትን መልካም ውጤቶች አጠናክረን እስከቀጠልንባቸው ድረስ በርግጥም አገራችን ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ማህበረሰቦች ለመቀላቀል ትችላለች፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለፉት የተሃድሶ አመታት በአገራችን የተመዘገቡ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ድሎች እንደተጠበቁ ሆኖ በአመራር የአሰራር ጉድለቶች ምክንያት የታዩ ችግሮች ስርዓቱ ለአደጋ መጋለጥ ጀምሮ እንደነበርም በግምገማው አረጋግጧል፡፡ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴያችን ወቅታዊና መሰረታዊ ሆኖ የተከሰተበት አይነተኛ ምክንያትም ይኽው ነበር፡፡ በቅርቡ ለተከሰቱት የሰላምና መረጋጋት ችግሮችና ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ጉዳቶች መንስኤ የሆነውን ጉድለት ከኢህአዴግና ከብሄራዊ ድርጅቶቻችን ከፍተኛ አመራሮች ጉድለቶች ግምገማ በመጀመር የወሰነው እንደገና በጥልቀት የመታደስ አቅጣጫ በሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች ትክክለኛ ፈር ይዞ እየቀጠለ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ የአገራዊ ለውጡ ዋና ቀያሽና ግንባር ቀደም አንቀሳቃሽ የሆነው ድርጅታችን ኢህአዴግ መላውን የአገራችንን ህዝቦች በማሳተፍና የለውጡ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ያስመዘገባቸው ህብረተሰባዊ ለውጦች የመንግስትን ስልጣን በአግባቡ በመጠቀሙ ምክንያት የሆነውን ያህል በሂደቱ የታዩበትን ጉድለቶችም ምንጫቸው ይኼው የህብረተሰባዊ ለውጥ ማምጫ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግለው የመንግስት ስልጣን ወደ ግል ኑሮ ማሻሻያነት ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ እንደሆነ በየብሄራዊ ድርጅቶቹ በተደረጉ ግምገማዎች በድጋሚ አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን የመንግስት ስልጣንን አገር ለመለወጥና ይህንኑም መላውን የሀገራችንን ህዝቦች እኩል ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችል ቅኝት በመራባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ሀገራችን ወደፊት ተራምዳለች፡፡ ህዝባችንም ደረጃ በደረጃ ተሳትፎውንና ተጠቃሚነቱን እየሰፋ መጥቷል፡፡ ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም ከመጣው ለውጥ በበቂ ሁኔታ ያልተጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የወጣቱ ህብረተሰብ ክፍል የፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጉድለት እንዲስተካከልላቸው የሚሹና የሚጠይቁ መሆኑን በአፅንኦት በመገንዘብ እነዚህን ህዝባዊና ፍትሃዊ ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ ለመመለስ መስራት እንዳለብን ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጉድለቶች በተከሰቱባቸው ዘርፎችና አግልግሎቶች ሁሉ ዋናው የጉድለቶቹ ምንጭ የመንግስትን ስልጣን ለህብረተሰባዊ ለውጥና ለህዝቡ ቅንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከመጠቀም ይልቅ ለግል ኑሮ መጠቀሚያ ማድረግ እንደሆነ በአንክሮ በመረዳት ይህንኑ ለማስተካከል በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን ማጎልበትና ዳር ማድረስ እንደሚገባ በጥብቅ ታምኖበታል፡፡ ድርጅታችንን በጥልቀት ለማደስ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣም መላ የአገራችን ህዝቦች የተለመደ ገንቢ ሚናቸውን በመጫወት የለውጡን ሂደት የማይቀለበስ ደረጃ ላይ እንዲያደርሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግና አባል ድርጅቶች የየራሳቸውን ድክመቶች በዝርዝር ገምግመው ራሳቸውን ለማስተካከል የጀመሩት እንቅስቃሴ ከመላ አባላትና ከህዝብ ተሳትፎ ውጭ ይሳካል ተብሎ አይገመትም፡፡ በመሆኑም ብሄራዊ ድርጅቶች በከፍተኛ አመራር ደረጃ የጀመሩት ራስን የማጥራት እንቅስቃሴ በየደረጃው ባሉ አመራሮች፣ በአባላትና በህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ራስን በራስ ከማረም ጎን ለጎን አመታዊ የልማትና የዴሞክራሲ ተግባሮቻችን በላቀ ትጋት እንዲፈፀሙ ለማድረግ በልዩ ትኩረት ለመረባረብ ተዘጋጅቷል፡፡ ግምገማውን መሰረት በማድረግ የሰው ሀይል ምደባ ማስተካከያዎች እንዲደረጉና በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግስት የአመራር ምደባ በውጤታማነት ላይ ተመስርቶ ማስተካከያ በማድረግ አመታዊ ስራው በተጠናከረ አቅጣጫ እንዲፈፀም ለማድረግ አቅጣጫ አስቀምጦ ተጠናቋል፡፡ የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ጥቅምት 2009 ዓ.ም አዲስ አበባ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy