በአዲስ አበባ በጉዞ ርቀት ልክ በማስከፈል አገልግሎት የሚሰጡ የሜትር ታክሲዎች ታሪፍ ወጣላቸው።
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አገር ውስጥ የገቡትን ሜትር ታክሲዎች የትራንስፖርት ታሪፍ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኜው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ከባለንብረቶች ጋር ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላ ነው ታሪፉ የወጣው።
በዚህም መሰረት አራት ሰው የሚይዙት ሜትር ታክሲዎች (ሊፋን ሳሎን ታክሲዎች) በኪሎ ሜትር 10 ብር እንዲያስከፍሉ ታሪፍ ወጥቶላቸዋል።
እስከ ሰባት ሰው ለሚይዙት ታክሲዎች ደግሞ በኪሎ ሜትር 13 ብር ሆኗል።
የትራንስፖርት አቅርቦቱን ለመደገፍ 836 ሜትር ታክሲዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ነው።
ቀሪ ታክሲዎችም በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ተገልጿል።
26 አክሲዮን ማህበራት እና ሶስት የግል ኩባንያዎች ተቋቁመው ነው ታክሲዎቹ ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት።