‹‹የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የፓርቲውን ንብረቶች አሽሽቷል›› የፓርቲው ሊቀመንበር

‹‹እኔን ማንም ሳይጠይቀኝ የሊቀመንበሩ ቡድን ቢሮ ሰብሮ ገብቷል›› የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

ሰማያዊ ፓርቲ ኃላፊነት ሳይሰጣቸው በሕገወጥ መንገድ የፓርቲው የጽሕፈት ቤትና አስተዳደር ኃላፊነትን ይዘዋል የተባሉት አቶ እንደሻው እምሻው፣ የፓርቲውን ንብረት ማሸሻቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የጽሕፈት ቤቱና አስተዳደር ኃላፊ ሆነው እየሠሩ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ እንደሻው ደግሞ፣ የፓርቲው ንብረት መጥፋቱን የሰሙት የፓርቲው ሊቀመንበር የሚመሩት ቡድን በፓርቲው ድረ ገጽ ባወጣው መረጃ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንደሚሉት፣ አቶ እንደሻው የፓርቲውን ንብረት እንዲያስረክቡ በተደጋጋሚ ተጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ ምንም ምላሽ ካለመስጠታቸውም በተጨማሪ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሥራ ላይ አለመገኘታቸውንና ንብረት እያሸሹ መሆናቸውን መረጃ ደርሷቸው ሲያጣሩ፣ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል፡፡

የፓርቲውን ንብረት እያሸሹ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ የፓርቲው የጥናትና ስትራቴጂ ኃላፊ አቶ እስክንድር ጥላሁን፣ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ይድነቃቸው አዲስ፣ አይኤስን ለማውገዝ መስቀል አደባባይ በተጠራው ሠልፍ ምክንያት ታስረው በቅርቡ የተፈቱት አቶ ማትያስ መኩሪያና የፓርቲው አባል አቶ ቴዎድሮስ አሰፋ የተካተቱበት ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡

ሊቀመንበሩ ያቋቋሙት ኮሚቴ አቶ እንደሻው በቢሮአቸው ተገኝተው ንብረት እንዲያስረክቡ በደብዳቤና በስልክ ሲጠይቋቸው ምላሽ ባለመስጠታቸው፣ በዕለቱ የነበሩ የጥበቃ ሠራተኞችንና ተጨማሪ አባላትን እማኝ በመያዝ የአቶ እንደሻውን ቢሮ ከፍተው መግባታቸውንም አክለዋል፡፡

በአቶ እንደሻው ኃላፊነት ሥር የነበሩ የፓርቲው ንብረቶች፣ ላፕቶፖች፣ ኮምፒዩተሮች፣ ፍላት ቴሌቪዥን፣ ሁለት የቪዲዮ ካሜራዎች፣ ሳውንድ ሲስተም፣ የፓርቲው ማኅተምና ሌሎች በርካታ ንብረቶች አለመኖራቸውን አረጋግጠው በቃለ ጉባዔ እንዳሳወቋቸው ኢንጂነር ይልቃል ተናግረዋል፡፡

ለጊዜው በፓርቲው ጽሕፈት ቤት የሚታወቁና ፊት ለፊት የሚታዩ ንብረቶች ለመጥቀስ ያህል እንጂ፣ እጅግ በጣም ብዛት ያላቸው ሰነዶችና ሌሎች ንብረቶችም ሊኖሩ እንደማይችሉ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ የኮሚቴውን ቃለ ጉባዔና የምስክሮችን ቃል በማያያዝ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዓድዋ ድልድይ ፖሊስ ጣቢያ ዓርብ መስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ማመልከቻ ማስገባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢንጂነር ይልቃል ከንብረቶቹ በላይ ያሳሰባቸው የፓርቲው ማኅተም መሆኑን ገልጸው፣ ከመስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ማኅተሙን በመጠቀም ወጪ የሚደረጉ ማንኛቸውም ደብዳቤዎች ሕገወጥ መሆናቸውን ኅብረተሰቡ አውቆ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል፡፡

አሁን እየተደረገ ያለው ቀደም ብሎ በፈጸሙት ጥፋት በመሰናበታቸው ምክንያት ቢሮ ሰብሮ በመግባትና ሰነዶችን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ሴራ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ፣ የፓርቲው ጽሕፈት ቤትና አስተዳደር ኃላፊ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ እንደሻው ናቸው፡፡

እንጂነር ይልቃል ላለፉት ሦስት ወራት ሥራ ገብተው እንደማያውቁና እንዳልተገናኙ የሚናገሩት አቶ እንደሻው፣ ከምክር ቤቱ አባላትና ከኦዲት ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ጋር በመሆን መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማንም ምንም ዓይነት ጥያቄ ጠይቋቸው እንደማያውቅ የሚናገሩት አቶ እንደሻው፣ ቢሯቸው መሰበሩንና ንብረትም እንደጠፋ የሰሙትና ያዩት በፓርቲው ድረ ገጽ ላይ መስከረም 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት መሆኑን አክለዋል፡፡

ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ወይም ያለ እሳቸው ፈቃድ ለምን ቢሮአቸው ሊገነጠል እንደቻለ ለፖሊስ በማመልከት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውንም አክለዋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል፣ አቶ ስለሺ ፈይሳና አቶ ወረታው ዋሴ ቀደም ብሎ በሠሩት ጥፋት የተሰናበቱበትን ሰነድ ለማጥፋት ሆን ብለው የፈጸሙት ድርጊት ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸው የገለጹት አቶ እንደሻው፣ ሁሉም ነገር መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ውሳኔ እንደሚያገኝ አስረድተዋል፡፡

መስከረም 14 ቀን 2009 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት ጉባዔ ከፓርቲው ቀረበልኝ ባለው ጥያቄ መሠረት እንዲራዘም ማድረጉን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ አይዘነጋም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አረጋግጠው፣ ኢንጂነር ይልቃልና ሌሎች አካላት ጠቅላላ ጉባዔውን ከማደናቀፍ ተግባር እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል በበኩላቸው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ሲጠራም ሆነ ምርጫ ቦርድ ሲያግደው አለማወቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ውሳኔውንም በመቃወም በትክክል ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ቃል ገብተዋል፡፡

http://www.ethiopianreporter.com/