CURRENT

የጁነይዲን ሳዶ 4 ውሸቶች

By Admin

October 18, 2016

አንድ ወዳጀ የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲን ሳዶ ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ከሲሳይ አጌና ጋር ቆይታ እንዳለው ነገሮኝ ቃለመጠየቁን ተከታተልኩት። ከሞላ ጎደል ኦቦ ጁነይዲን ያው ከዚህ ቀደም ወያኔነት በቅቶናል ብለው አሜሪካ ሀገር እንደከተሙ የቀድሞ የወያኔ ካድሬዎች ምንም የተለየ ነገር ሳይነግረን እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ስደተኛ ወያኔዎች እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ ጲላጦስ ነኝ ብሎናል። ቃለመጠይቁ የፖለቲከኛ ሳይሆን መኮንን ላእከ ወይም ክበበው ገዳ ኢሳት ላይ ኢንተርቪው የሚደረግላቸው ይመስላል። አይን ያወጣ ውሸት እና ቅጥፈት የሞላበት ኢንተርቪው ነበረ። እኔ በዋነኝነት ሰውዬው በቃለመጠይቁ ከገለፃቸው የሚከተሉት አብይ ጉዳዮችን ላይ የበኩሌን ማለት እፈልጋለሁ።

1, የኦህዴድ አባል አልነበርኩም ይህንን ያለው ጁነይዲን ነው። ነገሩ ሳቅ የሚጭር ከመሆኑም በላይ ሰውዬው እውነቱን ከሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሀይምና የማያውቅ አድርጎ የሚያስብ ይመስለኛል። ሰውዬው ኦህዴድ ከመሆንም አልፎ ኦህዴድ ኢህአዴግን ወክሎ ምርጫ የተወዳደረ ከዛም አልፎ በወያኔ አጠራር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበረ ግለሰብ ነው። ሆኖም ሰውዬው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የሆንኩት የኦህዴድ አባል ሳልሆን ነው ብሎ የተለመደ ቅጥፈቱን አሳይቶናል። መቼም የወያኔን ባህሪይ የሚያውቅ በሙሉ ወያኔ ኦሮሚያን ለገለልተኛ ሰው አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ከዚህ ቀደም የወያኔ አመራሮች በመንግሥት ስልጣን ላይ የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ እንደመኮንን ማንያዘዋል ያሉ ግለሰቦች ይገኛሉ ብለው ፈገግ እንዳደረጉን ልብ ይሏል። ታድያ ኦቦ ጁነይዲን ኢህአዴግ አባል ያልሆኑ ባለስልጣናት ያሉት ጥሩ ድርጅት ነው ማለት ፈልጎ ይሆን?

2, ስኮላርሽፕ ተልኬ ገንዘብ አጥቼ ነው የተመለስኩት ይሄ ነው ሌላኛው የኦቦ ጁነይዲን ሳታየር ኮሜዲ። ኦቦ ጁነይዲን ከተሰደደ በዃላ ወይ ጨዋታ ጨምሯል ወይ ነገሮች ተምታተውበታል። ስኮላርሽፕ ትምህርቴን ያልጨረስኩት በገንዘብ ምክንያት ነው ቢልም አሁንም ድረስ በለገጣፎ እና በቦሌ ቡልቡላ የሚገኙ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ባለቤት ነው። ሆኖም ሰውዬው ትምህርቱን በገንዘብ ምክንያት ነው ያቋረጠው ሲባል ከመሳቅ ውጭ መረብ ማድረግ እንችላለን።

3, ሳልፈልግ ነው የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆንኩት፤ እኔ ሳላውቅ ምርጫ አወዳደሩኝ

እነዚህ ሦስተኛ ቅጥፈቶቹ ናቸው ሆኖም እውነታው ይህ ነው። ህወሀት በተገነጣጠለበት ወቅት ከእነስዬ ቡድን የነበሩት እነኩማ ደመቅሣ ሲቀጡ ብልጣብልጡ ጁነይዲን ግብ ከአሸናፊው የመለስ ዜናዊ ቡድን ጋር በመሆኑ ምክንያት ከስዬ ጋር ሲሰሩ የነበሩትን የኦህዴድ አባላት አጋልጦ ነው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የሆነው ነገር ግን ሳላውቅ ነው ይላል። ታድያ እነኩማን ያስመታው ፕሬዚዳንት ለመሆን ካልሆነ ምቀኝነት ይዞት ነውን?

4, የኦህዴድ አባላት ክልሉን አናውቀውም በማለት ከሥልጣን ይሸሹ ነበረ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ስብስባ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በሙሉ ተነስቷል የሚለው ቅጥፈት ተጨማሪ ውሸቱ ነው። በዚህ አባባሉ ኦህዴድ ለኦሮሞ ህዝብ የቆመ ድርጅት ነውና ለማለት ነው ይዳዳዋል። በዚህ ጉዳይ ላይም ምንም ማለት አልፈልግም። ድፍን የኦሮሚያ ህዝብ እውነታውን ያውቀዋል። ይልቁስ በጣም ያሳቀኝን ነገር ላጫውታቹህ ኦህዴድ በወቅቱ ጠንካራ ነበረ ብሎ ከብሔራዊ ባንክ ዘርፈው ህወሀቶች ኤፈርትን ስላቋቋሙበት ሲጠየቅ ከ77 ረሀብ እህል ሳይሆን ጆንያ ነው የሰረቁት እናም ያንን ጆንያ ሸጠው ባጠራቀሙት ገንዘብ ኤፈርትን እንዳቋቋሙ መለስ እንደነገሯቸው ገልጿል ወዳጆቼ ጆንያው ግን ከምን ቢሰራ ነው እንዲህ በውድ የተሸጠው?

ኤርሚያስ ቶኩማ