ግብፅ ለምን የተሳሳተ መንገድ መረጠች?
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በጥናት አረጋግጣ ወደ ግንባታ የገባችው ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ አጋምሳለች። ሀገሪቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ጥርጣሬ ለመፋቅ አለም አቀፍ ባለሙያዎች በግድቡ ላይ ጥናት አካሂደው ምክረ ሀሳብ እንዲለግሱ እስከ ማድረግ ዘልቃለች። የጥናት ቡድኑ ሪፖርትም ግድቡ በታችኛቸው ተፋሰስ ሀገሮች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት እንደማያስከትል አረጋግጧል፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና መምህሩ ዶክተር መሰለ ሃይ፣ ከሃይድሮ ፓወር ሳይንስ አንፃር ሲታይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም ይላሉ።
ሱዳን የአባይ ውሃን ተጠቅማ መረዌ ከሚባል ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ታገኛለች። ግብፅ መስኖዋን አጠጥታ፤ የዜጎቿን ጉረሮ አርሳ፤ በአባይ ውሃ ከአስዋን ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል ታገኛለች። የአባይ ውሃ በክረምት ወቅት ይህንን ሁሉ ተግባር ከውኖ የተረፈው የሜዲትራንያን ባህርን ይቀላቀላል። አስዋን በብዙ ቢሊየን ኪዩቢክ ሊትር የሚለካ ውሃን በትነት ያጣል፡፡ የአባይ ውሃ ከኢትዮጵያ ጠራርጎ በሚወስደው አፈር የአስዋን እና የመረዌ ግድብን በደለል ሞልቶ ከተሞቻቸውን በጎርፍ ያጥለቀልቃል። እናም ታለቁ የህዳሴ ግድብ ሀገራቱን ከዚህ ችግር የሚታደግ መሆኑን ነው ምሁሩ የተናገሩት።