Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌደራል መንግስት በአዲስ መልክ ይዋቀራል ፕ/ት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ

0 661

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌደራል መንግስት በአዲስ መልክ ይዋቀራል ፕ/ት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ

 

የፌደራል መንግስትን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አስታወቁ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ አመት የስራ ዘመን የመክፈቻ ስነ ስርአት ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የ2009 ዓ.ም የመንግስት አቅጣጫ እና እቅድ ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንቱ የኢሬቻን በዓል ላይ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን በመመኘት ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡

ያለፈው ዓመት አገሪቱ  በብዙ መልኮች ወደፊት የተራመደችበትና ችግሮች የተከሰቱበት ነበር ያሉት ዶ/ር ሙላቱ ጠንካራ ጎኖችን በማስፋትና ደካማዎቹን መቅረፍ ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያረጋግጥና የሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የማፋጠን ጊዜ ላይ ደርሰናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ካለፈው ችግር በመነሳት ለመፍትሄዎቹ በላቀ ርብርብ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በኤልኒኖ ምክንያት የተከሰተውን ድርቅ በወሳኝነት በራስ አቅም ለመፍታት ተሰርቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በውጤቱም ሰብአዊ ጉዳት ሳይደርስ ለመፍታት ተችሏል ብለዋል፡፡

ድርቁን ለመቋቋም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላደረገው ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በድርቅ በተጠቃንበት ዓመት ከመኸር ግብርና የተገኘው 26 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን ምርት ከዚህ ዓመት በፊት ከነበረው ተመሳሳይ መሆኑ የሀገሪቱን የግብርና ልማት አቅጣጫ ትክክለኛነት ያረጋግጣል ብለዋል፡፡ የ2008/09 ግብርና ምርት ከፍተኛ ጭማሪ የሚታይበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ወጣቶች የተሳተፉባቸው ሁከቶችና ግጭቶች  መከሰታቸውን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀው ይህም ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለችግሩ ምክንያት ወቅታዊ ጉዳዮች ቢኖሩም መሠረታዊ ችግሮቹን በመለየት ህዝቡን በማሳተፍ መፍታት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡

የተከሰተው ችግር ወጣቶች ያሉባቸውን ችግሮች ስፋት ያሳያል በዚህም የሚሰጠው መፍትሄም ወጣቶችን ያማከለ እንዲሆንና የስራ እና የተጠቃሚነት ዕድልን  መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የወጣቱ የትምህርት ዕድል መስፋፋትን ተከትሎ ከግብርና ውጭ ወዳሉ ስራዎች እንዲያተኩር አድርጎታል ያሉት ዶ/ር ሙላቱ የገቢ ምንጭና የስራ ሁኔታ በአስተማማኝ ዕድል አልተፈጠረለትም ብለዋል፡፡ በዚህም  መንግስት የተለየ ርብርብ ካላደረገ በስተቀረ ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ አይቀርም፡፡

ከ3ኛው ምርጫ በኋላ መንግስት ወጣቶችን ለመጥቀም እየሰራ ቢሆንም እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ አይደለም ብለዋል፡፡ ለዚህም የወጣቶችን ችግር መፍታት ጊዜ የማይሰጠው መሆን አለበት ብለዋል፡፡

መንግስት ድህነትን ለመቀነስ በትኩረት ሰርቷል ብለዋል ዶ/ር ሙላቱ በመክፈቻ ንግግራቸው፡፡

የአርሶ አድርና አርብቶ አደርን ጥቅም ለማስጠበቅ ተመጣጣኝ የካሳና የመቋቋሚያ ክፍያ ሲደረግ አልነበረም  ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህን ችግር ለመፍታት ዘንድሮ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከሀገሪቱ ዕድገት በተገቢው ደረጃ መጠቀም ያልጀመሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለማቃለል በተለየ ትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ በራሳችን አቅም ለመገንባት መቻላችን ያላስደሰታቸው ሀገሮች ከጽንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር በመቀናጀ  ሀገሪቱን ለማተራመስ  እየተረባረቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በዚህም በተለያዩ ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ የህብት ውድመትና የሰው ህይወት መጥፋት የተሳተፉ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው ሀገሪቱን ለማፈራረስ የሚያደርጉትን ሙከራ ለመመከት ህዝብና መንግስት በጋራ ይሰራሉ ብለዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዲሞክራሲ ስርዓቱ ቢሰራበትም አሁንም ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ ታይቷል፡፡ እነዚህ ችግሮችም በዴሞክራሲ ማዕቀፉ ሊፈቱ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት በሠላም መኖራችን የፌደራል ስርዓቱ ችግር ፈጣሪ ሳይሆን ችግር ፈቺ  መሆኑን ያሳያል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡

የፌደራል ዴሞክራሲ ስርዓት  ሁሌም እያደገ እንዲጓዝ  ከህብረተሰቡ ጥቅሞች ጋር በማጣጣም መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡

ባለፉት ምርጫዎች የገዢው ፓርቲ የበላይነት ታይቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ግን የማይወከሉ ድምጽች እንዲኖሩ አድርጓል ብለዋል፡፡ በዚህም በምክር ቤቶቹ ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ድምጽ ሊያሰማ የሚችል የምርጫ ህግ ማሻሻያ ይደረጋል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፡፡ አስተያየቶችን በውል አዳምጦ ትክለኛዎቹን በመውሰድ ትክክል ያልሆኑትን በትክክለኛ አመክንዮ መመለስ የሚገባው ነገር  መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የፌደራል መንግስትን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም  ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አስታውቀዋል። በስነምግባርና ስነ ዜጋ የታነጹ ዜጎችን የመፍጠር ስራም ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕደገት ለማስጓዝና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ያለፈው ዓመት አፈጻጸም በተለያዩ ምክንያቶች ተጽእኖዎች  እያሉት ኢኮኖሚው አሁንም በዕድገት ጎዳና ቢቀጥልም ለላቀ ውጤት መስራት የሚገባን ወቅት ላይ ነን ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ ውጤታማ የነበርንባቸው ላይ በትኩት የሚሰራ ሲሆን  የተፈጥሮ ሃብት ልማትንም ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

የገጠር መሬትን ለላቀ ስራ ለማዋል አርብቶ አደርና አርሶ አደሮችን በማይጎዳ መልኩ ይሰራል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም እየተሰሩ ሲሆን ይህም ተወዳዳሪ ለመሆንም ያግዛሉ ብለዋል፡፡

ትርጉም ያለው እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ለአግሮ ፕሮሰሲንግ እና ለማኑፋክቸሪንግ እድገት የሚረዳ በመሆኑ በገጠር ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ይገባል፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመሠረተ ልማት ስራዎች ትኩረት የተሰጠ ሲሆን ይህም ተግባዊ እየተደረገ ነው፡፡ የመሰረተ ልማት ግንባታ በተለይ ትላልቆቹ ፕሮጀክቶች በ2009 በላቀ ቁርጠኝነት የሚቀጥሉ ይሆናል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በአፈጻጸሞች ላይ ያለውን መጓተትና የጥራት ችግር በመቅረፍ  በተለይ ደግሞ ወጣት ባለሃብቶችን ለመፍጠር ለመስራት ይረዳናል ብለዋል፡፡

የወጣቶችን ጥያቄዎችን የመመለስ ስራ ዋነኛ ትኩረት ይሰጠዋል ያሉት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ለዚህ አላማ የሚሆን የወጣቶች ተንቀሳቀሽ ፈንድ የሚቋቋም ሲሆን 10 ቢሊዮን ብርም ተመድቦለታል ብለዋል፡፡

እንደወጣቶች ሁሉ የሲቪል ሰርቪሱን እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለመቅረፍ የደሞዝ ማስተካከያና ሌሎችም ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

የሁሉም ድምጽ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩ የሀገራችን የምርጫ ህግ ከተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የህግ ማሻሻያ ይደረግበታል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን ምልሽ ያላገኙ ከማንነት ጋር የተያያዘዙ ችግሮች  ስህተት መሆናቸውን ጠቁመው በፍጥነት እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት የኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣውን አዋጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች ይወጣሉ ሲሉ ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል፡፡

መንግስት ራሱን ከመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ቁርጠኛ በመሆን ለመስራት እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የፌደራል መንግስትን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ለዚህም አዲስ የመንግስት ምክር ቤት ይዋቀራል ብለዋል፡፡

በተለያዩ መስኮች ረዥም መንገድ ተጉዘናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ እነዚህን መልካም ስራዎች በማስቀጠል መስራት ይገባናል፡፡ የተደቀኑ ችግሮችን አስተማማኝ መፍትሄ መስጠት ይገባል ሲሉ ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡

ሪፖርተር :-ወገኔ  አለማየሁ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy