NEWS

ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል የአርማታ ብረት በ15 ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ጭነው የተሰወሩ 23 ተጠርጣሪዎች ከነ ንብረቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓሊስ አስታወቀ።

By Admin

November 27, 2016

ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል የአርማታ ብረት በ15 ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ጭነው የተሰወሩ 23 ተጠርጣሪዎች ከነ ንብረቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓሊስ አስታወቀ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ኮንስትራክሽን የግንባታ ግብአት ኦፊሰር ኃላፊን ጨምሮ 12 የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችና 11 ሹፌሮች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ በምርመራ እየተጣራ ይገኛል። በአዲስ አበባ የፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ የወንጀል እና የትራፊክ አደጋ ምርመራ ድቪዥን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ጋሻው ፅጌ እንደገለጹት፤ በፖሊስ ክትትል የተያዘው ንብረት አምስት ሚሊዮን ብር ይገመታል። ከተዘረፈው ንብረት የጠፋ የለም ብለዋል። በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብለው ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል የኢንተርፕራይዙ ሠራተኞች፣ የመርካቶ ብረት ነጋዴዎች፣ደላሎችና ሹፌሮች መኖራቸውን ሃላፊው ገልጸዋል። የኢንተርፕራይዙ የግንባታ ግብአት ኦፊሰር ኃላፊ ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር በመሆን ወንጀሉን ፈፅሟል ተብሎ በመጠርጠሩ በቁጥጥር ስር ውሏል። እንደ ምክትል ኮማንደር ጋሻው ገለፃ፤ የግንባታው ብረት የተዘረፈው ህዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም ጎፋ ወረዳ 6 ልዩ ስሙ እርሻ ሰብል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለ40/60 ቤቶች ግንባታ እንዲውል ከተቀመጠበት መጋዘን ነው። በዕለቱ በኢንተርፕራይዙ ውስጥ የሚሰሩ ኃላፊዎች ለጥበቃ ሰራተኞች ሀሰተኛ የንብረት ማውጫ ሰነድ አሰናድተው በመስጠት ንብረቱን ጭነው መውጣት ችለዋል። በመሆኑም የጥበቃ ሠራተኞቸ በወንጀሉ ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው ተረጋግጧል ብለዋል። ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሰረት የምርመራ ቡድን በማቋቋም በሁለት ቀናት ውስጥ ሌሊትና ቀን በመስራት ወንጀል ፈፃሚዎችን ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ምክትል ኮማንደሩ ገልጸዋል። ወንጀሉን አቀነባብሯል ተብሎ የተጠረጠረው የግብአት ኦፊሰር ኃላፊ በመርካቶ ተክለኃይማኖት አካባቢ ለሚገኝ አንድ ነጋዴ የተሰረቀውን ብረት በኪሎ 18 ብር ለመሸጥ ተስማምቶ ነበር ተብሏል። በዚህ መሰረት ንብረቱን ወደ ሰበታ አካባቢ ወደ ተዘጋጀ አንድ መጋዝን 90 በመቶ የሚሆነው ንብረት የተጓጓዘ ሲሆን፤ ቀሪው ሁለት የሲኖትራክ ተሽከርካሪ ጭነት ደግሞ አዳማ ለሚገኝ ነጋዴ ደርሶ ለገበያ ተዘጋጅቶ እንደነበር ተገልጿል። ቀደም ሲል ተመሳሳይ ወንጀል አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ኮማንደሩ፤ ይሄኛው ግን በጠራራ ፀሃይ የተፈፀመ ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል።