ኢትዮጵያ የሶማሊያን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደምትሠራ ገለጸች
ህዳር 16፣2009
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከሶማሊያና ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዱረሺድ አሊ ሼርማክን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እያደረገችው ባለው ጥረትና የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ዙሪያ መክረዋል፡፡
በተጨማሪው በሶማሊያ እየተካሄደ ስላለው የምርጫ ሂደት፣ የፋይናንስና ሲቪል ሠርቪስ ጉዳዮች ሶማሊያ በምትጠናክርበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሶማሊያ የምትፈልገውን ድጋፍ እንደምታደርግና የሶማሊያን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከሶማሊያና ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በቃል አቀባያቸው ተወልደ ሙሉጌታ በኩል ገልፀዋል፡፡
ሪፖርተር:-ሜሮን በረዳ