የተሻለ ምርምርና ፈጠራ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት መሸለም ለዘርፉ ዕድገት የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል፡- ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ህዳር 10፣ 2009
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መስኮች የተሻለ ምርምርና ፈጠራ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት መሸለማቸው ለዘርፉ ዕድገት የተሰጠውን ልዩ ትኩረት እንደሚያሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ መስክ ልዩ የምርምርና የቴክኖሎጂ ስራ ላስመዘገቡ የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችና መምህራን፣ ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ሰልጣኞችና አሰልጣኞች፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለቤቶች ሽልማት ተሰጥቷል።
“ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከእርምጃ ወደ ሩጫ” በሚል መሪ ሃሳብ ለ7ኛ ጊዜ በተደረገው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽልማት ውድድር መስፈርቶችን ያሟሉ 140 የፈጠራ ባለቤቶች ናቸው የተሸለሙት። ከመካከላቸውም 24ቱ ሴቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በሽልማቱ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት በአገሪቷ ምርምርና የፈጠራ ስራ ለሚሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና በመስጠት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዕድገት ልዩ ትኩረት ይሰጣል።
የሚመዘገቡ ውጤቶችን በአይነትና በብዛት ከፍ ለማድረግ በሁሉም የትምህርት እርከኖች የሚሰጡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስልጠናዎችና ምዘናዎች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በትጋት መስራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
አገሪቷን ወደ መካከለኛ ገቢ ለማስገባት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ወሳኝ በመሆኑ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራና ለተሸላሚዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
“የዜጎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የዕውቀትና የክህሎት ክምችቶች እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ዋነኛ ሃብቶች ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎች በራሳቸው ውጤት ከመሆናቸው ባሻገር ለሌሎች የልማት ዘርፎች ቁልፍ ተግባራት ስኬት መልህቅ በመሆናቸው ዘርፉን በፈጣን ሁኔታ ማሳደግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነም አስረድተዋል።
ይህን ለማሳካት የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው 70/30 መደረጉና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ኮሌጆች ወደ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትነት ማደጋቸው ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ነውም ብለዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢነጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው የአገሪቷን የግብርና ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ምርት ለማግኘት ዘርፉን በሚገባ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ልዩ ተሰጥኦና የሳይንስ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች ለማስተማር የሚውል ብሄራዊ የታለንት ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዲዛይን መጠናቀቁንና ግንባታውም የሚጀመር መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት፣ ብሄራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየም እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂን ባህሉ ያደረገ ዜጋ ማፍራት የሚያስችሉ የሳይንስና የባህል ግንባታ ስራዎች ያከናውናል ብለዋል።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአገሪቱን ልማትና ዕድገት መደገፍ እንዲችል የ10 ዓመት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም አክለዋል።
ምንጭ፡- ኢዜአ