Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በክልሉ የወጣቶችን የስራ እጥነት ችግር ለመፍታት አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

0 814

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በክልሉ የወጣቶችን የስራ እጥነት ችግር ለመፍታት አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በአማራ ክልል የወጣቶችን የስራ እጥነት ችግር ለመፍታት አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በትኩረት መስራት እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አስገነዘቡ።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የስራ እድል ፈጠራ የንቅናቄ መድረክ ላይ እንደገለፁት ዜጎችን በማንኛውንም የገቢ ማስገኛ መስክ እንዲሰማሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል የመስሪያ ቦታም ሆነ ለብድር አገልግሎት የሚውል የመንቀሳቀሻ ገንዘብ እጥረት እንደሌለ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የተሰሩና በርካታ ዜጎችን ተጠቀሚ ያደረጉ የጥቃቅንና አንስተኛ ኢንተርፕይዞች የካበተ ልምድና እውቀት እንዳለም ገልፀዋል።

እስካሁን የተሰሩት ስራዎች የሚበረታቱ ቢሆንም ከስራ ፈላጊዎች ቁጥር አንፃር ሲመዘን ገና ብዙ የሚቀር ተግባር እንዳለ መገምገሙን ጠቁመዋል።

ለችግሩ መከሰት ደግሞ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ባለው ሃብት ልክ ቁርጠኛ ሆኖና የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ ያለመንቀሳቀስ እንደሆነ አብራርተዋል።

”አመራሩ የወጣቱን የተዛባ አስተሳሰብ ለማስተካከል በግንዛቤ ፈጠራ ትኩረት አድርጎ በመስራት የረጅም ጊዜ ራዕይ ያለውና ለስራ ጉጉ የሆነ ሃይል ማፍራት ይጠበቅበታል” ብለዋል።

ወጣቱን በእውቀት በክህሎትና በአመለካከት በመገንባት በዘርፉ በትክክል ለውጥ ለማምጣት ቁጭት ፈጥሮ መንቀሳቀስ እንደሚገባም አቶ ገዱ አብራርተዋል።

በሚኒስትር ማእረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል የኢንዱስትሪ ጥናትና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው መንግስት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጣራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“በተለይም ከገጠር ወደ ታዳጊ ከተሞች የሚስተዋለውን ፍልሰት ለመከላከል ወጣቱ ባለበት አካባቢ ዘላቂነት ያለው የገቢ አማራጭ እንዲኖረው በትኩረት መስራት ይገባል” ብለዋል።

የግብርና ዘርፍን ከልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ ዘመናዊና የተሻሻሉ አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባም ተናግረዋል።

”በከተሞች ያሉ የስራ እድል አማራጮችን በመጠቀም በጥቃቅንና አነስተኛ ወጣቶችን በአመለካከትና በእውቀት አንጾ ወደ ተግባር ማስገባት ይገባል” ብለዋል።

የስራ እደል ፈጠራ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት ችግሩን ለመፍታት አዳዲስ አሰራሮችንና ከፍተኛ ገንዘብ መመደቡን ጠቁመው ለተግበራዊነቱም የመንግስት መዋቅሩ ጠንካራ መሆን እንዳለበት አቶ በረከት ገልፀዋል።

በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ከ878 ሺህ 500 ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ላቀ አያሌው ናቸው።

“ለብድር አገልግሎት የሚውል ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ከአበዳሪ ተቋማት ተመቻችቷል” ብለዋል።

ለእቅዱ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተደራጀ የልማት ሰራዊት ንቅናቄ በመፍጠር ከእስካሁኑ በተለየ አካሄድና አሰራር ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በባህር ዳር ከተማ ታህሳስ 8 እና 9 ቀን 2009 በተካሄደው የስራ እድል ፈጠራ ንቅናቄ መድረክ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy