Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዓሉ የህዝቦችን እኩልነት፣ አብሮ የመኖር እና የመቻቻል እሴቶች ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ አለው – ጠ/ሚ ኃይለማርያም

0 390

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዓሉ የህዝቦችን እኩልነት፣ አብሮ የመኖር እና የመቻቻል እሴቶች ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ አለው – ጠ/ሚ ኃይለማርያም

በዓሉ የህዝቦችን እኩልነት፣ አብሮ የመኖር እና የመቻቻል እሴቶች ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ አለው - ጠ/ሚ ኃይለማርያም

የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል የህዝቦችን እኩልነት፣ አብሮ የመኖር እና የመቻቻል እሴቶች ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ አለው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ።

11ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በሀረር ከተማ አው አባድር ስታዲየም ሲከበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ይህን ያሉት።

የሀገሪቱ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ለታሪኳ፣ ባህሏ እና ገናናነቷ አስተዋፅኦ ያደረጉባት ጥንታዊ ሀገር ናት ያሉት አቶ ኃይለማርያም፥ ኢትዮጵያውያን የቀደሙ የተዛቡ ግንኙነቶችን በማደስ መልካም እሴቶችን፣ የጋራ እቅዶች እና አመለካከቶችን ለማክበር የገቡትን ቃል በተግባር እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተጋን ነው፤ ሀገሪቱ በአፍሪካም ሆነ በአለም ተሰሚነቷ እንዲጎለብት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በሁሉም ዜጋ ዘንድ በጥልቀት መስረፅ ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች የራሳቸው ማንነት እንዳላቸው ሁሉ የጋራ የሆነ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ማንነት አላቸው፤ በዚህ በመመራትም እጅግ ፈታኝ በሆነው የአለም ሁኔታ ውስጥ ሀገሪቱ በድል ጎዳና እንድትገሰግስ ሁሉም ወገናዊ ሀላፊነት ተሸክሟልም ነው ያሉት።

የሀገሪቱ ዜጎች ዋነኛ ጠላት የሆነውን ድህነት ለማስወገድ እና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ አሁንም ርብርቡ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የባለፉት 15 አመታት ሀገራዊ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች በህዝቡ ተሳትፎ እና ውጤታማነት በአለም ቀዳሚ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከዚህ ፈጣን እድገትም ህዝቡ ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል።

የተመዘገቡት አስደናቂ ለውጦች ብሩህ የተስፋ ፋና ከመፈንጠቅ ባሻገር የህዝቡን ተጨማሪ የእድገት ጥማት መቀስቀሱንም ነው የገለጹት።

መንግስትም ይህን የህዝብ የማያቋርጥ የእድገት ፍላጎት ለማርካት ከህዝቡ ጋር በመሆን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

በህዝብ ይሁኝታ ያገኘው መንግስት ባለፉት አመታት ፈጣን ለውጥ ማስመዝገብ ቢችልም ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌዎች ታይተዋል።

በጥቂቶች ዘንድም የህዝበ እና የምንግስት ሀብትን አለአግባብ ለራስ ብልፅግና መጠቀም፣ ብልሹ አሰራሮች እና ሙስና መንፀባረቃቸው ታይቷል ብለዋል።

ባለፉት አመታት የሁሉንም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢከናወኑም ህብረ ብሄራዊነትን የማያስተናግዱ የጠባብነት እና ትምክህት አስተሳሰቦች በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ማድረሳቸውንም ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ያስመዘገበችውን አሰደናቂ እድገት ለማጎልበት እና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለማስወገድ በመላ ሀገሪቱ የተጀመረው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።

የተሃድሶ ንቅናቄው በመሪው ኢህአዴግ እና አባል ድርጅቶቹ ተጀምሮ ህብረተሰባዊ የለውጥ እና የተሃድሶ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአስተሳሰብ እና የተግባር ጉድለቶችን ለማረም እንዲሁም ህብረተሰቡ የሚማረርባቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄው ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የተሃድሶ ንቅናቄው ውጤታማ እንዲሆን መላው ኢትዮጵያዊ የነቃ እና የማያቋርጥ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አህመድ አልበሽር፣ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ተወካዮች በአው አባድር ስታዲየም በተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ተገኝተዋል።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አህመድ አልበሽር የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ የኢትዮጰያና ሱዳን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የሁለቱ ሀገራት ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ግንኙነት እደገ መምጣቱን ያነሱት ፕሬዚዳንት አልበሽር፥ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በበኩላቸው፥ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን በአማርኛ እና በአደርኛ ቋንቋዎች አስተላልፈዋል።

“በጂቡቲ መንግስት እና ህዝብ ስም ለኢትዮጵያ ህዝብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም፣ አንድነት፣ ህዳሴ ብልጽግና እና እድገት ምኞቴን አስተላልፋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት እስማኤል “..ብዙሃነት የኢትዮጵያ ልዩ ሀብት ነው” ብለዋል።

 

በፋሲካው ታደሰ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy