Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከድህነት ለመውጣት አገሪቱ የያዘችው ፍላጎት ማሳያ ነው፡- ጽህፈት ቤቱ

0 572

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከድህነት ለመውጣት አገሪቱ የያዘችው ፍላጎት ማሳያ ነው፡- ጽህፈት ቤቱ

ታህሳስ 21፣ 2009

የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከድህነት ለመውጣት አገሪቱ የያዘችው ፍላጎት ማሳያ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ጽህፈት ቤቱ ይሕን የገለጸው የመንግስትን አቋም በሚገልጸው ሳምንታዊ መግለጫው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦችና መንግስት ፀረ ድህነት ትግል ከጀመሩ ሁለት አስርት ዓመታት ሆኗቸዋል ያለው መግለጫው የውርደታቸው ምንጭና የህልውናቸው ጠላት ከሆነው ድህነት ለመላቀቅም የህዳሴ ጉዞ ጀምረዋል ብሏል። የፀረ ድህነት ትግሉን ባጠረ ጊዜ በድል ለማጠናቀቅም የተለጠጡ የልማት ዕቅዶችን መተግበር ላይ ይገኛሉ ብሏል። ሰሞኑን የተመረቀው ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የዚህ ጥረት አንድ ማሳያ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

እያንዳንዳቸው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው ያለው ጽህፈት ቤቱ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለውሃ እና ለመንገድ ግንባታዎች በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እየተመደበም እየተስፋፋም ይገኛል ብሏል። ለቴሌኮም መሠረተ ልማት ከሚመደበው ከፍተኛ በተጨማሪ የስኳር የማዳበሪያ የሲሚንቶና የመሰል ግዙፍ አምራች ፋብሪካዎች ግንባታ በመከናወን ላይ ነው ብሏል። የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት የተጀመረው ጥረት ዓለምን ሳይቀር ያስገረመ ሆኗል።ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብቻውን ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ነው። ጊቤ ሶስትም ከ1.5 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ ጠይቋል ብሏል መግለጫው።

ከዚህም በላይ ጊቤ 3 በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ፣ በሀብት ማፈላለግ ሂደቱና በግዝፈቱ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ለማሳረፍ ይሰሩ በነበሩ የውጭ አካላት ጥረት በእጅጉ የተወሳሰበ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ጊቤ 3 ሀገራችን የጀመረችው የሶስት ዘመን የሜጋ ፕሮጀክቶች ውዝፍ የማወራረድ ጥረት፡ ተራ ህልም አለመሆኑን ያረጋገጥንበት እና ይህን መሰል ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የገነባነውን ጠንካራ የፋይናንስ፣ የማኔጅመንትና የቴክኖሎጂ አቅም ጥንካሬ የታየበት በመሆኑ ብሔራዊ ኩራት ሆኗል ሲል ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

ህዝቦና መንግስት ይህን ሁሉ ዋጋ የሚከፍሉት ዜጎች ለኑሮና ለስራ የሚመርጧት፣ በየትኛውም መመዘኛ የበለጸገችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነው ያለው መግለጫው በመሆኑም ካለፉት ትውልዶች የተሻገረ የልማት ስራ፣ ዛሬ የተነቃቃው ልማት የፈጠረው ተጨማሪ ፍላጎት እና ነገ ላይ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን መሰረተ ልማት ከወዲሁ የመስራት ኃላፊነት የዚህ ትውልድ ተልዕኮ ሆኗል ብሏል። የትላንትን፣ የዛሬንና የነገን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ዛሬ ላይ ሆኖ መመለስ በማስፈለጉም ዘመኑ ‹የሜጋ ፕሮጀክቶች› ዘመን ሆኗል። በመሆኑም በሁሉም ደረጃና በሁሉም ዘርፍ አቅም የሚፈትኑና ለመዋቅራዊ ሽግግር መሠረታዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ታቅደው በመሰራት ላይ ይገኛሉ ብሏል ጽህፈት ቤቱ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች ከወዳጅ ሀገራትና ተቋማት ጋር በመተባበር በዋናነት ግን የራሳቸውን አቅም በማስተባበርና በማጠናከር ከትላንት ዛሬ እየበረቱ እዚህ ደርሰዋል። የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆኑ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም ለማጠናቀቅ በመረባረብ ላይ ናቸው። አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የስኳር ፍላጎትን መሸፈን የሚችሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች መትከልና ማስተዳደርም እየቻሉ ነው። ከግልገል ግቤ 3 እንደታየውም አንዱ ሲያልቅ ሌላ ግዙፍ ፕሮጀክት በመጀመር ተጠምደዋል ብሏል።
ይህ ትጋታቸው፣ ሠላማቸውና እየፈጠሩ ያሉት ግዙፍ ኢኮኖሚ የዓለምን ትኩረት መሳብ ጀምሯል። በዚህም ምክንያት ሊጎበኟቸውና ሀብታቸውን አፍስሰው አብረዋቸው ሊሰሩ የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ሲል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መግልጫ አስታውቋል።

የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የህዳሴ ጉዞ የመምራትና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ያለው መግለጫው ለህዳሴ ጉዞው ስኬት መሠረት የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ያለማንም ተጽዕኖ ለማጠናቀቅም ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር መስራቱን ይቀጥላል ብሏል።

በዚህ አጋጣሚም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደሁልጊዜው ሁሉ ከመንግስት ጋር እንዲሰሩ፣ ሂደቱን የሚያደናቅፉ አካላትና አሠራሮችንም በትጋት መታገላቸውን እንዲቀጥሉ ጽህፈት ቤቱ ጥሪውን አስተላልፏል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy