የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ለመገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ድጋፍ አደርጋለሁ አለ
አዲስ አበባ ህዳር 22/2009 የመገናኛ ብዙኃን የሕዝብ አገልጋይ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ለሚያከናውኑት ስራ ሙያዊ ድጋፍ እንደሚደረግ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ።
በአገሪቷ የሚከናወኑ ተግባራትን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ዓለም ለማስተዋወቅ የአገር ወስጥ መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ እንዲሆኑ ለማድረግም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በመገናኛ ብዙኃንና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ሊሰራባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ሕብረተሰቡ በሚያነሳው ጥያቄዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በሕብረተሰቡ የሚቀርቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የሕዝብ አገልጋዮች በሚሰጡት አገልግሎት ተጠያቂ መሆናቸውን የሚያሳዩ ስራዎችንም በስፋት ይሰራል ብለዋል።
የሕዝብ አገልጋዮች ሥራቸውን በአግባቡ በመሥራት መሪነታቸውን በውጤት በማሳየት በአንጻሩ ደግሞ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡትን በማጋለጥ እንዲሰሩ ለመገናኛ ብዙሃኑ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ይደረጋልም ነው ያሉት።
ድጋፉ በአገር ውስጥ ለሚሰሩ የግልና የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን እንደሚደረግና መገናኛ ብዙሃኑ በጋራ አንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ በአገር እድገት ላይ ጉልህ ሚና እንዲኖረው አቅሙ ሊጎለብት ይገባል።
የሕዝቡ የልማት ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር፣ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ እንዲሁም ተጠያቂ እንዲኖር በማድረግ የመገናኛ ብዙሃኑ የመረጃ ፍሰት እንዲጠናከር ለማድርግ ሰፊ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል ዶክተር ነገሪ።
“የምርመራ ጋዜጠኝነት የልማታዊ ጋዜጠኝነት አንድ አካል ነው አንጂ የሌላ የጋዜጠኝነት አስተምህሮ አካል አይደለም” ያሉት ሚኒስትሩ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች በዚህ ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ይደረጋልም ብለዋል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በተለይ የአገርን ገጽታ በመገንባት የሚኖራቸው ሚና ከፍ እንዲል ይደረጋልም ነው ያሉት።