የትግራይ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ሹመቶችን አጸደቀ
ህዳር 26፣2009
የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን አጸደቀ፡፡
ምክር ቤቱ በዚሁ አስቸኳይ ጉባኤው የቢሮ ሃላፊዎችን ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የክልሉ ዋና ኦዲተር አዲስ ሹመቶችን አጽድቋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ለሹመት ያቀረቧቸው የስራ ሃላፊዎች ድርጅቱ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ያካሄደውን ሰፊ ግምገማ መነሻ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት
1/ዶክተር ኢንጂነር ገብረ መስቀል ካህሳይ የትምህርት ቢሮ ሃላፊ፣
2/ ዶክተር ተስፋ ሚካኤል ገብረ ዮሐንስ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ፣
3/ዶክተር ሙሉጌታ ሃጎስ የቴክኒክ ትምህርትና ሙያ ስልጠና ቢሮ ሃላፊ ፣
4/ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ፣
5/ዶክተር አትንኩት መዝገቡ በግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ተጨማሪ የቢሮ ሃላፊ እና
6/ ዶክተር አብረሃ ኪሮስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ወደ ቢሮ እንዲያድግ በማድረግ ሃላፊ ሆነዋል፡፡
በተጨማሪም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሀጎስ የተሾሙ ሲሆን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ደግሞ አቶ አማኑኤል አሰፋ እንዲሁም ለክልሉ ዋና ኦዲተር ዶክተር ረዳኢ በርሄ ሆነው ተሹመዋል፡፡
ከዚህም ሌላ የውሃ ሀብት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ ለክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ፣ አቶ ጎይቶም ይብራህ ለወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ፣ ዶክተር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር ለትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡
ተሿሚዎቹ በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ መፈጸማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።