የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ተከፈተ
ምክር ቤቱ የአሜሪካና የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላል ተብሎለታል።
በኢትዮጵያና በአፍሪካ አገራት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተሰማሩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ትብብር የተቋቋመው ምክር ቤቱ የኩባንያዎቹ ባለቤቶች በንግድ ዘርፍ ያላቸውን ልምድ በመጠቀም የሎጅስቲክ ወጪ ለመቀነስና ለሥራ የሚያስፈልገውን የሠው ኃይል ለመመጠን የሚያስችል ምክክር እንዲያደርጉ ያግዛል ተብሏል።
የፋይናንስ ፍሰቱን በመረዳትና ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሆን ለችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሠራም ነው የተጠቆመው።
የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ኃይሉ እንዳሉት፥ ምክር ቤቱ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል።
በኢትዮጵያ ግልጽነትና ቀጣይነት ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ ባህል እንዲሆን እንደሚሠራና የኢንቨስትመንት ሥራዎች በምን መልኩ እንደሚተገበሩ ምክር ቤቱ ለአዳዲስ ኩባንያዎች ያስተዋውቃል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ልምዳቸውን አዲስ ለሚመጡ ኩባንያዎች የሚያስተላልፉበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።