የጊቤ ሶስት የሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ አሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ግንባታው በ1999 ዓመተ ምህረት የተጀመረው ግድቡ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዮሮ ወጪ ተደርጎበታል።
ከዚህ ወጪ ውስጥም 40 በመቶ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፥ ቀሪው 60 በመቶ የግንባታ ወጪ ደግሞ ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር ተሸፍኗል።
አሁን ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው እና በኢትዮጵያ በግድብ ግንባታ የበርካታ አስርት ዓመታት ልምድ ያለው የጣሊያኑ ኩባንያ ሳሊኒ ግንባታውን አካሂዷል።
ግድቡ 246 ሜትር ከፍታእና 630 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፥ 15 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው።
ኢንጂነር አዜብ ግድቡ እያንዳንዳቸው 187 ሜጋ ዋት ሀይል የሚያመነጩ 10 ተርባይኖች ያሉት ሲሆን፥ በአጠቃላይ ግድቡ 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ያመነጫል።
ግድቡ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ከመጠናቀቁ ቀደም ብሎ ወደ ሀይል ማምረት የገባ ሲሆን፥ ይህም ባለፈው ዓመት በኤል ኒኖ ምክንያት የአንዳንድ ግድቦች የውሃ መጠን በመቀነሱ ምክንያት የሀይል አቅርቦትን በፈረቃ ከማቅረብ ታድጓል።
አሁን ላይ በግድቡ በተጠራቀመው ውሃ ልክ 900 ሜጋ ዋት ሀይል በማመንጨት ላይ እንደሚገኝ ነው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ የተናገሩት።
ሁሉም ተርባይኖች ሀይል ለማመንጨት ዝግጁ ቢሆንም፥ ግድቡ ማጠራቀም የቻለው ውሃ አነስተኛ በመሆኑ በሂደት ሁሉም ተርባይኖች ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ሳይት አስተባባሪ ኢንጅነር መብራቱ ተሾመ እንደሚሉት፥ በግንባታው በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋራጮች እና ዲዛይነሮች የተሳተፉ በመሆኑ በሂደቱ ኢትዮጵያዊያን ሌሎች ተመሳሳይ ግድቦችን ለመገንባት የሚያስችላቸውን እውቀት እና ልምድ አግኝተዋል።
በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ባለሙያዎችም በአንድ ወቅት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት አስተያየት፥ የእውቀት ሽግግርን በመፍጠር ረገድ የፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።
ከቀሰሙት እውቀት እና ካገኙት ልምድ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉንም ነው የገለጹት።
ኢንጅነር መብራቱ ተሾመ፥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያኑ ከሀገራችው አልፍው ውጪ ሀገር ድረስ ተቀጥረው የሚሰሩበት እውቀትና ልምድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ጊቤ ሶስት በግልገል ጊቤ ወንዝ ላይ የተገነባ ሶስተኛው ግድብ ነው። ጊቤ አንድ 184 ሜጋ ዋት ሀይል የሚያመርት ሲሆን፥ ጊቤ ሁለት ደግሞ 420 ሜጋ ዋት ሀይል በማምረት ላይ ይገኛል።
ጊቤ ሶስት የሀይል ማመንጫ የአገሪቱን የሀይል አቅርቦት 4 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ያደርሰዋል።