ዶክተር ወርቅነህ ከዩኤስኤይድ ሀላፊ ጋይል ስሚዝ ጋር ተወያዩ
በውይይታቸው ዩኤስኤይድ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እንዲሆኑ እና አቅማቸውን በመገንባት ረገድ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች በንቃት እንዲሳተፉ ርብርብ እያደረገ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
መንግስት የዜጎችን ፍላጎት በማሟላት የሀገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነ መሆኑንና ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን እያስፋፋ እንደሚገኝም ለአስተዳዳሪዋ ነግረዋቸዋል።
ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርት፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ በስራ ፈጠራ እንዲሁም በማህበረሰብ ልማት መስኮች ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ዶክተር ወርቅነህ በኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም ለሀላፊዋ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ጋይል ስሚዝ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን ማህበረ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ እድገት ፍትሃዊ እና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ ያከናወናቸውን ተግባራት አድንቀዋል።
ኤጀንሲው ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍም ገልፀዋል።
ምንጭ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር