Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልካም ተሞክሮ በሶማሌ ክልል

0 438

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መልካም ተሞክሮ በሶማሌ ክልል

ይነበብ ይግለጡ 01-23-17

ጋዜጠኝነት ከወታደራዊ ሙያ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ልዩነቱ ወታደሩ ጠመንጃ ጋዜጠኛው ደግሞ ብእርና መቅረጸ-ድምጽ ይዘው መንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ ወታደር ወዴት እንደሚታዘዝ፣ መቼ እንደሚሄድ፣ ቅርብ ይሁን ሩቅ ተዘጋጅቶ ከመጠበቅ ውጭ ቀድሞ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ጋዜጠኛውም የትም ሆነ የት ዜና ባለበት ሁሉ ስሊሚሰማራ ምን እንደተፈጠረ፤ የት እንደሚሄድ የሚያውቀው ለስራው ሲላክ ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ማንሳት የተፈለገው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በአሸባሪዎችና በእስላማዊ አክራሪዎች የተነሳ ለረዥም ግዜ ሰላም የሌለበት የጦርነት ቀጠና ሁኖ ቆይቶአል፡፡ ጋዜጠኞች ለስራ ብዙ ግዜ ወደዚሁ ቀጠና ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ሲሄዱ በወታደራዊ ኮንቮይ ታጅበው ጉዞው ከጠዋቱ አንድ ሰአት ተጀምሮ ከቀኑ አስር ሰአት ላይ ያበቃል፡፡ በምሽት መንቀሳቀስ በፍጹም አይቻልም ነበር፡፡ በዚሁ ክልል አንድ ግዜ አንድ ሹም ጋዜጠኞችን ለስራ ሲሸኙ ሳያውቁት በሉ እንግዲህ በሰላም ያገናኘን አሉ፡፡ ከሰላም ያገናኘን ጀርባ የነበረው ፍርሀት የአካባቢውን የጎላ የሰላም ማጣትና መደፍረስ ችግር ጠቋሚ ነበር፡፡ ጥርጣሬና ስጋት ሰቅዞ እንደያዛቸው ከፊታቸው ይነበባል፡፡ ወቅቱ ከአሸባሪዎች ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ የነበረበት ነው፡፡ አሸባሪዎች በየመንገዱ ደፈጣ ያደርጋሉ፡፡ ፈንጂ ይቀብራሉ፡፡ ጥይት ለአካባቢው የሙዚቃ ድምጽ ያህል የተለመደበት ነበር፡፡ ዛሬ የተረጋጋ ሰላም ያለበት ለልማትና ለእድገት የሚሰራበት ክልል ለመሆን በቅቶአል፡፡ ድንቅ ስራም እየተሰራ ነው፡፡ ያ ሁሉ የፈተናና የመከራ ግዜ የታለፈው በሰራዊታችን ታላቅ የጀግንነት ተጋድሎና መስዋእትነት ነው፡፡ ዛሬ በሶማሊያ ክልል ቀንም ለሊትም በሰላም መንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ የጸጥታ ስጋት የለም፡፡ የበረሀ ገነቶች አነሰም በዛም በየቦታው እየተገነቡ ነው፡፡ መንገዶች በስፋት ተሰርተዋል፡፡ በአርብቶአደርነት ከቦታ ቦታ ይንከራተት የነበረውን ማህበረሰብ በአንድ ቦታ ሰፍሮ የጋራ ማህበራዊ ህይወት እንዲኖረው የትምህርት የጤና አገልግሎት ንጹህ የመጠጥ ውሀ ወዘተ እንዲያገኝ ለማድረግ ያለማሰለስ ስራው ቀጥሎአል፡፡ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ደረጃ በደረጃ የነዚህ ትሩፋቶች ተጠቃሚ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ ክልሉ በተደጋጋሚ በድርቅ ተጠቂ የመሆኑ እውነት እንዳለ ቢሆንም የፌደራል መንግስትና የክልሉ መንግስት በጋራ ሕዝቡን ከድርቅ ለመታደግ ሰፊ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የጉድጓድ ውሀ ቁፋሮው በጣም በጥልቀት 500 እና 600 ሜትር ተቆፍሮ የሚገኝበትም የማይገኝበትም ሁኔታ አለ፡፡ ጋሻሞን በመሳሰሉት ድርቁ በአየለባቸው አካባቢዎች ለግዜው በጥልቅ ቁፋሮ ውሀ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ተስፋ የሚያስቆርጥ ግን አይደለም፡፡ የፌደራሉና የክልሉ መንግስት ቦቴዎችን በመጠቀም ርቀት ካለው ቦታ ውሀ እየጫኑ በየእለቱ ለሕዝቡ በማድረስ ሕይወቱን ለመታደግ እየተጉ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የተቆፈሩት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ሰውና እንስሳትን ከድርቁ አደጋ ማትረፍ ችለዋል፡፡ጀረር ዞን የጉና ገዶ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አይሻ ሐሰን ለዋልታ እንደገለጹት ቀደም ሲል ውሃ ለማግኘት በየቀኑ ርቀት ወዳለው ቦታ በእግር ይጓዙ ነበር፡፡የውሃ ጉድጓድ መቆፈሩ ውሀውን በቅርበትና በሚፈልጉት መጠን እንዲያገኙ ረድቷቸዋል፡፡ሌሎች ነዋሪዎችም ይሄንኑ ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ የውሀ ጉድጓዶቹ መቆፈር ለውሀ ፍለጋ ይደረግ የነበረውን መንከራተት አስቀርቶአል፡፡ ውሀው ሁለት ወረዳዎችንና አራት ቀበሌዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ሀላፊዎች ይናገራሉ፡፡ አንዱ በሰከንድ 22 ሊትር ውሃ ለማምረት የሚችል ሁለት ጉድጓዶች ተቆፍረው 146 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው መስመር መዘርጋቱን ሀላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡በየ5ኪሎሜትር ርቀት ሕብረተሰቡ በጋራ ውሀ የሚቀዳበት የቦኖ ቧንቧና ለእንስሳት ውሃ መጠጫ ገንዳ መዘጋጀቱም ታውቆአል፡፡አብዛኛው የግንባታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪው በአጭር ጊዜ ስራው አልቆ ሁሉም ቀበሌዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡220 ሚሊየን ብር ለግንባታው ወጪ ተደርጎአል፡፡ በጥልቅ የውሀ ጉድጓዶቹ መቆፈር ነዋሪው ሕዝብና እንስሳት ውሀ ለማግኘት በመቻላቸው የድርቁን አደጋ መቀነስ ተችሎአል፡፡ በአቧሬ ወረዳ የተቆፈረው የውሀ ጉድጓድ 75 ሺህ ነዋሪዎችን በአርሲ ወረዳ 150ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ከወረዳዎቹ ውሀ ልማት ጽሕፈት ቤት የተገኙ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ በመጪው ሚያዚያ ወር የሚጠበቀው ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ካልዘነበ አሁን በመደረግ ላይ ያለው መንግስታዊ ድጋፍ እንዳለ ሁኖ ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ የሚመጣውን የከፋ ድርቅ ለመከላከል እስከ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለተረጂዎች የሚውል ምግብ ፣ውሃ ፣መድሀኒት የእንስሳት መኖን ለመግዛትና ለማከፋፈል የሚያስፈልግ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚደንት አቶ አብዲ ሙሐመድ ሰሞኑን በክልሉ ያለውን የድርቅ ሁኔታ አስመልክተው ሲናገሩ ገልጸዋል፡፡ በድርቁ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ጉዳት እንዳይደርስ አማራጮችን በመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መሆኑን ከአርብቶ አደሩ እንስሳትን በመግዛት ውሀ ወዳለበት ሥፍራ በመውሰድ ድርቁ ካለፈ በኋላ ለአርብቶ አደሩ በመመለስ ኑሮውን እንደነበረው እንዲቀጥል የማድረግ አቅጣጫ ተግባራዊ እንደሚደረግ ፕሬዚደንቱ አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት 150 አዳዲስ የውሀ ቦቴዎችን ለመግዛትና በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚደረገውን የመጠጥ ውሀ ሥርጭት ለማጠናከር አቅዶ 30 የሚሆኑት ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሥራ ጀምረዋል፡፡ ቀሪዎቹ በ15 ቀናት ውስጥ የሚገቡ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች የተቆፈሩት ጥልቅ ጉድጓዶች ለ24 ሰዓት ያለምንም ማቋረጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ለስራውም በቂ ባለሙያዎች መመደባቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ይሀው ጥረትና ተግባራዊ እርምጃ በሶማሌ ክልል በድርቅ በተጎዱት አካባቢዎች ከፍተኛ ለውጥ በማስመዝገብ የሰውንና የእንሰሳትን ሕይወት በአስደናቂ ርብርብ እየታደገ ይገኛል፡፡ በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ በመከላከል የሰውና እንስሳት ሕይወትን ለመታደግ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አጠናክሮ እንደሚገፋበት የክልሉ መንግስት የገለጸ ሲሆን ባለፉት 15 ቀናት ብቻ ከ11ሺ ኩንታል በላይ ሩዝና 50 ሺ እሥር ሣር ለድርቅ ተጎጂዎች ማከፋፈሉን 40 አባላት ያሉት የሕክምና ቡድን በድርቅ በተጠቁ የክልሉ አካባቢዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑም ታውቆአል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በአምስት አመታት ውስጥ ከ170 ሺ በላይ አባወራዎች በመንደር ለመሰባሰብ መቻላቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አብዲ መሀመድ ኡመር ለዋልታ ገልጸዋል፡፡የመንደር ማሰባሰቡ ሂደት በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስችሎአል፡፡ ሰፋሪዎቹ ተፋሰስ ባለበት አካባቢ መሰባሰባቸው በማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ረገድ ተጠቃሚ አድርጎአቸዋል፡፡ ለእርሻና ለእንስሳት መኖ ማምረቻ የሚሆን መሬትና ከ12ሺ በላይ የውሀ መሳቢያ ፓምፖች ተከፋፍለው ወስደዋል፡፡ የውሀ ፓምፖቹ በሰከንድ 70 ሊትር ለመሳብ ይችላሉ፡፡ በክልሉ በቅርቡ በተደጋጋሚ በተከሰቱ የድርቅ ክስተቶች በመንደር የተሰባሰቡ ነዋሪዎች አልተጠቁም፡፡ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከሚኖሩ አርብቶ አደሮች ጋር ሲነጻጸሩ በድርቅ አካባቢ ከሚኖር 100 ግመሎች ካሉት ነዋሪ ይልቅ በሰፈራ በተሰባሰቡ አካባቢዎች የሚኖር 10 ግመሎች ያሉት አባወራ እንደሚሻል ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ከአንድ ግመል እስከ 1.5 ሊትር ወተት በቀን ሲያገኙ በመንደር የተሰባሰቡት ደግሞ እስከ አራት ሊትር ያገኛሉ፡፡የመንደር ማሰባሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ አስገኝቶአል፡፡በመንደር የማሰባሰቡ ፕሮግራም ነዋሪዎች በአንድ ቦታ ተረጋግተው በመኖር የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችን እንዲያገኙ የሚያስችልና ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲለወጡ ማገዙን የክልሉ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy