Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምክር ቤቱ ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ የሚውል 9 ቢሊየን ብር የተካተተበት ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

0 1,357

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምክር ቤቱ ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ የሚውል 9 ቢሊየን ብር የተካተተበት ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

ምክር ቤቱ ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ የሚውል 9 ቢሊየን ብር የተካተተበት ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌደራል መንግስት የ18 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ተጨማሪ በጀቱን ሲያፀድቅ 9 ቢሊየን ብሩ ለመንግስት ሰራተኞች ለሚደረግ የደመወዝ ማሻሻያ እንደሚውል ተመልክቷል።

5 ቢሊየን ብር ደግሞ ለወጣቶች የስራ አድል ፈጠራ ተንቀሳቃሽ ፈንድ የሚውል ነው።

እንዲሁም በገጠር እየተካሄደ ያለው የልማታዊ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ማስፋፊያ በ2009 በጀት ዓመት የተያዘው በጀት በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንዳስፈለገም ተገልጿል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተስተዋለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል እና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም መንግስት ቀሪ ግዴታውን በመወጣት የደረሰውን ተፅእኖ ለመቋቋም 1 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈግል ተብራርቷል።

በበጀት ዓመቱ በመጠባበቂያነት የተያዘው በጀት አብዛኛው የደረሰውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም የዋለ በመሆኑ፤ በቀጣይ ወራትም መንግስት ግዴታውን ለመወጣት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመጠባበቂያ በጀት፤ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር ለስራ ማስኬጃነት እንደተያዘም ተመልክቷል።

የካፒታል ወጪ በሚል የተያዙትን ደግሞ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለስልጣንን የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለማስጀመር እንዲሁም በዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ገቢ፣ ወጪ እና ተላላፊ እቃዎች የተሳለጡ እንዲሆኑ ለማስቻል በ20 ሚሊየን ብር አገልግሎቱን ለማስጀመር እንደሚጠይቅ ተገልጿል።

የከተማ የምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምን ለማስጀመር በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፥ 236 ነጥብ 2 ሚሊየን ብሩ የመንግስትን ድርሻ እንደሚጠይቅም ተነግሯል።

በጤናው ዘርፍ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልብ ህክምና ማእከል በመንግስት ለማቋቋም የኔዘርላንድስ መንግስት ከሚያደርገው 35 ሚሊየን ዩሮ የኢትዮጵያ መንግስትን 90 ሚሊየን ብር ድርሻ ይጠይቃል ተብሏል።

ወጪው ለልብ ህክምና መሳሪያ ግዥ ለማከናወን፣ የልብ ህክምና ቦታ ለማዘጋጀት እና ባለሙያ ለመቅጠር እንደሚውልም ተገልጿል።

በአጠቃላይም ተጨማሪ 18 ነጥብ 26 ቢሊየን ብሩ በቀጣይ ወራት ለሚከናወነው መደበኛ የስራ ማስኬጃ እና የካፒታል ወጪ የሚውል ይሆናልም ተብሏል።

ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም፥ “ለመንግስት ሰራተኛው የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰትና ጭማሪው ትርጉም አልባ እንዳይሆን ምን ታስቧል? ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መንግስት ከመደበው 10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ አንጻር የተጠየቀው 5 ቢሊየን ብር ዝቅተኛ አይሆንም?” የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አለማየሁ ጉጆ በሰጡት ምላሽ፥ የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ የዋጋ ጭማሪ እንደማያስከትል ተረጋግጧል ብለዋል።

ለዚህም ገበያው ውስጥ ካለው ገንዘብ በተጨማሪ ሌላ ገንዘብ ወደ ገበያ የማይገባ በመሆኑ ምንም አይነት ለውጥ እንደማያስከትልም ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ የተረጋጋ በመሆኑ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል የኢኮኖሚ መሰረት የለውም፤ ሆኖም ግን ማሻሻያውን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷልም ብለዋል።

ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ ተግባራዊ ለምን አይደረግም በሚል ከምክር ቤተ አባላት ለቀረበው ጥያቄም አቶ አለማየሁ፥ በተወሰኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስርአቱ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፤ ሙሉ በሙሉ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አብራርተዋል።

ሆኖም አሁን የሚደረገው ጭማሪ ከዚህ ቀደም ደመወዛቸው በልዩ ስኬል ለተያዘላቸው እና በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ክፍያ ያላቸውን የመንግስት ተቋማት ሰራተኞችን እንደማያካትት አስታውቀዋል።

“ተቋማቱ የትኞቹ እንደሆኑ እና ጭማሪው እስከምን ድረስ እንደማይመለከታቸው ለመለየት እየተደረገ ያለ ጥናት አለ፤ ጥናቱ እንደተጠናቀቀም ዝርዝር መረጃው ይፋ ይደረጋል” ነው ያሉት።

ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ በተመለከተም የተመደበው 5 ቢሊየን ብር እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውል ነው ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ የተመደበው ገንዘብ በቂ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ፥ ተጨማሪ 5 ቢሊየን ብሩ በ2010 በጀት ዓመት ፀድቆ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መዋል ይጀምራል ብለዋል።

ምክር ቤቱ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ለ2009 በጀት ዓመት 274 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበውን የፌደራል መንግሥት በጀት ማፅደቁ ይታወሳል።

በበላይ ተስፋዬ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy