Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ የመጨረሻ ዙር ውይይት እየተካሄደ ነው

0 1,435

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ላይ ከወረዳ አመራሮች ጋር የመጨረሻ ዙር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኮሚሽነር አቶ ማቴዎስ አስፋው እንደገለጹት፣ አሥረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን በቀናት ውስጥ ፀድቆ በይፋ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙት 116 ወረዳዎች እያንዳንዳቸው 25 አመራሮች አሏቸው፡፡ በአጠቃላይ 2,900 ከሚሆኑት እነዚህ የወረዳ አመራሮች ጋር በአራት ዙር ከሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም ከክፍላተ ከተሞች ጋር በማስተር ፕላኑ ላይ ውይይት መደረጉ ይታወሳል፡፡ በአንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ 28 ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከ28 ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት በባለሙያ የሚመራ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ 27 አመራሮች አሉት፡፡ በድምሩ 270 ለሚሆኑ አመራሮችና በማዕከል ከሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በማስተር ፕላኑ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የወረዳ፣ የክፍላተ ከተሞችና የማዕከል ምክር ቤቶችና የተለያዩ ፎረሞች በማስተር ፕላኑ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ መድረኮች ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች እየተገባደዱ በመምጣታቸው በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ማስተር ፕላኑ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል፡፡

‹‹አሥረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ማቴዎስ ገልጸው፣ ‹‹ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ሰዎች ማስተር ፕላን የመሐንዲሶች ጉዳይ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ነገር ግን የማስተር ፕላን ዝግጅት የብዙ ባለሙያዎችንና ፖለቲከኞችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፤›› ሲሉ በተለይ የወረዳ አመራሮች ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በውይይቱ ወቅት አሳስበዋል፡፡

በማስተር ፕላን ዝግጅቱ ወቅት በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቦርዱ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል፡፡

አሥረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር ሲካሄድ ቆይቶ፣ በተነሱ አለመግባባቶች ማስተር ፕላኑ በአዲስ አበባ ክልል ውስጥ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

አዲሱ ማስተር ፕላን በነባሩ የአዲስ አበባ መዋቅር ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ለማድረግ አስገድዷል፡፡ አቶ ማቴዎስ እንደገለጹት አሥሩ ነባር ክፍላተ ከተሞች ወደ 13 ከፍ እንዲሉ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ነባሮቹ 116 ወረዳዎች ወደ 120 ወረዳዎች ከፍ ይላሉ፡፡

ይህ ማሻሻያ የሚደረገው በተለይ ቦሌና አቃቂ ክፍላተ ከተሞች ከሌሎቹ ክፍላተ ከተሞች ጋር ሲነፃፀሩ የቆዳ ስፋታቸው በእጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ፣ ለአስተዳደራዊ ሥራዎች ባለመመቸታቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

አዲስ አበባ ዘጠነኛው ማስተር ፕላን ጊዜ ወደ ጐን ስትለጠጥ ቆይታለች፡፡ በአዲሱ ማስተር ፕላን ግን ወደ ጐን መለጠጧን አቁማ ወደ ላይ ከፍ ማለት እንደምትጀምር አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት አዲስ አበባ ካላት 54 ሺሕ ሔክታር መሬት 30 በመቶውን ለአረንጓዴ ልማት፣ 30 በመቶውን ለመንገድ አውታር ግንባታ፣ ቀሪውን 40 በመቶ ለተለያዩ ሕንፃዎች ግንባታ እንደምታውለው ተገልጿል፡፡

ይህ መሠረተ ልማት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት አራት ሚሊዮን በተጨማሪ፣ 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚያስተናግድ ታሳቢ ተደርጐ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ይህንንም ለማሳካት ከተወሰኑ ልዩ ባህሪ ካላቸው ግንባታዎች በስተቀር የሚገነቡ ሕንፃዎች አፓርትመንቶችን አካተው እንደሚገነቡ፣ ጥግግቱም እንዲጨምር ተደርጐ ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ የነበረው የመኖሪያ ቤቶች የወለል ስፋት 30 ካሬ ሜትር ወደ 90 ካሬ ሜትር እንደሚያድግ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ አዲሱ ማስተር ፕላን አዲስ አበባ ከተማ በቂ የመኖሪያ ሥፍራ፣ የመሥሪያ ቦታና የመዝናኛ ቦታ እንዲኖራት የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ የአፍሪካ መዲና መሆኗንም የሚያረጋግጡ ግንባታዎችን ታካሂዳለች ተብሏል፡፡

በውይይቱ ወቅት የወረዳ አመራሮች ላቀረቧቸው ጥያቄዎች አቶ ማቴዎስና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የከንቲባው አማካሪ አቶ ተወልደ ገብረተንሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy