በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል ለዓመታት በዘለቀው የድንበር ማካለል ችግር ሲጉላሉ የቆዩና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት የወሰዱ 38 ኢንቨስተሮች በኦሮሚያ ክልል እንዲተዳደሩ ተወሰነ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚዋሰንባቸው በተለይ በሰበታና በገላን ከተሞች አቅራቢያ፣ ለኢንቨስተሮችና ለመንግሥት ተቋማት ለልማት የሚሆን መሬት በተለያዩ ጊዜዎች ሰጥቷል፡፡
ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለልማት ያስተላለፋቸው በርካታ ቦታዎች፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ክልል ነው በሚል ተቃውሞ ተነስቷል፡፡ በሁለቱ አስተዳደራዊ አካላት መካከል የተፈጠረው የቦታ ይገባኛል ውዝግብ፣ በወቅቱና በአግባቡ ባለመፈታቱ በርካታ ባለሀብቶች ሲጉላሉ መቆየታቸው ይነገራል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት አዲስ አበባ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ደብዳቤዎችን የተለዋወጡ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ፣ የ38 ባለሀብቶች ፋይል ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲላክ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የሲቪል ሰርቪስና የመልካም አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ እሸቱ ደሴ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ሐምሌ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ አቅራቢያ ለተለያዩ ባለሀብቶች የኢንዱስትሪ መሬት መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡ አስተዳደሩ የሰጣቸው ቦታዎች ከሰበታ አስተዳደር መሬት ጋር የተደራረቡ በመሆናቸው፣ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ የመለየትና የማካለል ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባለሀብቶች መጉላላት ስለሌለባቸው፣ ሙሉ ፋይላቸው ለኦሮሚያ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ እንዲላክ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
‹‹የክልሉ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት የተፈቀደላቸው ባለሀብቶች በዚህ በተፈጠረው ችግር ምክንያት መጉላላታቸው ተገቢ ባለመሆኑ ሙሉ በሙሉ ፋይላቸውን ተረክቦ ለማስተናገድ ተወስኗል፤›› ሲሉ አቶ እሸቱ ለከንቲባ ድሪባ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የኦሮሚያ ክልል ጥያቄን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሏል፡፡ አቶ አሰግድ ከኦሮሚያ ክልል የተጻፈውን ደብዳቤ ዋቢ በማድረግ ለከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ፣ ድንበር የማካለሉ ጉዳይ ወደፊት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እስኪፈታ ድረስ ባለሀብቶቹ ወደ ልማት መግባት እንዲችሉ የባለሀብቶቹን ፋይል ለኦሮሚያ ክልል እንዲላክ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለው ወሰን ማካለል ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ቦታዎቹ ለልማት በሚፈለጉበት ወቅት ይገባኛል ጥያቄ እየተነሳ፣ በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ መስተጓጎል ይፈጠራል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ይህንን ችግር ለመፍታት በርካታ ንግግሮች ቢካሄዱም፣ አሁንም የወሰን ጉዳይ ጎልቶ የሚነሳና ወደ ሥራ ለመግባት ቦታ የወሰዱ ባለሀብቶችም እያጉላላ ነው፡፡
ባለሀብቶቹ ለጊዜው በኦሮሚያ ክልል እንዲተዳደሩ የተወሰነ ቢሆንም፣ ለወደፊቱ ችግሩን በኮሚቴ ለመፍታት መታቀዱ ታውቋል፡፡
reporter