Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“አይደገምም!”…ሲባል?

0 452

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“አይደገምም!”…ሲባል?

ዘአማን በላይ 01-01-17

በቅርቡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ኮማንድ ፖስቱ ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ዜጎችን ከእስር ለቅቋል። እነዚህ ትምህርት ወስደው ከእስር የተለቀቁ ዜጎች በሁከቱ ወቅት ያከናወኑትን ኢ-ህጋዊ ተግባር “አይደገምም!” በማለት የበደሉትን ህዝብ እንደሚክሱ በሚዲያ ሲገልፁ ተመልክተናል፤ አድምጠናል። ሆኖም አንዳንድ ወገኖች ይህን የታራሚዎቹን አባባል ከእነርሱ ፍላጎት ውጪ ሲተረጉሙትና ለሚፈልጉት ተራ የፖለቲካ ትርፍ አጣምመው ሲተረጉሙት እየስተዋለ ነው። በዚህ ፅሑፍ ላይም ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለማረቅ እሞክራለሁ። ይሁንና “ነገርን ከመሰረቱ” እንዲሉ አበው፣ የአባባሉን ትክክለኛ እሳቤ ከመግለፄ በፊት የሁነቱን ዝርዝር ማውሳቱ ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው በሀገራችን ውስጥ በኦሮሚያና በሰሜን ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ሳቢያ በሚያሳዝን መልኩ ህይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ ንብረትም ወድሟል። ይህ በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስት ጥልቅ ሃዘኑን ገልጿል። የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ለማድረግና የነበረን ሰላም ባለቤት ወደ ሆነው ህዝብ እንዲመለስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አውጥቷል። አዋጁን የሚያስፈፅምና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮማንድ ፖስትንም አቋቁሟል። ኮማንድ ፖስቱም በውስጥ በውጭ ፀረ-ሰላም ሃይሎች እንዲሁም በጽንፈኛ ዲያስፖራዎች አማካኝነት በተፈጠረው ሁከት ላይ ተሳታፊ የነበሩ ዜጎችን በቁጥጥር ስር አውሏል። ከእነዚህ ውስጥም በሁከቱ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ አነስተኛ የሆነውና በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ዜጎች (አብዛኛዎቹ ወጣቶች መሆናቸው የተገለፀው) ከህገ መንግስቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ትምህርቶችን ወስደው ወደ መጡበት ቦታ እንዲመለሱ ተደርጓል። ቀሪዎቹ ደግሞ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንዳለ እንዲሁም በፈፀሙት ወንጀል ልክ ጥፋታቸው በህግ እንደሚታይ ተገልጿል። ታዲያ በተለያዩ ማቆያ ቦታዎች ትምህርት የወሰዱት ተመራቂዎችም ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላለቀሉ ቀደም ሲል በመታለልም ይሁን ባለማወቅ የበደሉትን ህዝብ እንደሚክሱ ተናግረዋል። እርግጥ እዚህ ላይ አንድ እውነታን ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል። ይኸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተዘጋጀው በዋነኛነት ዜጎችን ለመቅጣት ሳይሆን፣ ለማስተማር መሆኑን ነው። አዎ! የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ ማስተማር እንጂ መቅጣት አይደለም። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት አጥፍተው የነበሩትን ወጣቶች የለቀቀው የህግ የበላይነትን ዕውን ላለማድረግ አይመስለኝም— ሰዎችን ከማሰር ይልቅ አስተምሮ መልቀቁ ጠቀሜታ ስላለው እንጂ። በዚህ ላይ ደግሞ አጥፊዎቹ ወጣቶች በፈፀሙት ተገቢ ያልሆነ ተግባር ተፀፅተዋል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ ሀገር የወጣቶች ነው። ወጣቶች የዚህች ሀገር የነገ ተስፋዎች ናቸው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እነዚህን ወጣቶች አስተምሮ መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁና ወደ ትክክለኛው ጎዳና እንዲገቡ ማድረግ ትልቅ ስኬት ነው። ይህም እነዚህ ወጣቶች በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ከማስቻሉም በላይ፤ ወጣቶቹ መንግስት ባመቻቸው የብድር አገልግሎት ተጠቅመው ወደ ስራ እንዲገቡና የህብረተሰቡን የልማት ጉዞ እንዲደግፉ ያደርጋል። እናም የወጣቶቹ መፈታት ምክንያት ከዚህ ሀገራዊ ጥቅም አኳያ መታየት ይኖርበታል ባይ ነኝ። 2 ለነገሩ የሀገራችን የፍትህ ስርዓትም ይህን መሰሉን አካሄድ የሚደግፍ ነው። የፍትህ ስርዓቱ የተመሰረተው አጥፊዎችን በመቅጣት አስተሳሰብ ላይ አይደለም—በማስተማርና አጥፊዎች ከስህተታቸው እንዲማሩ ቅድሚያ መስጠትን እንጂ። ይህም አዋጁ በአንዳንድ ወገኖች በተሳሳተ መንገድ እንደሚገለፀው የዜጎችን መብቶች የሚገፍ ሳይሆን፤ ዜጎች መብቶቻቸውንና ግዴታቸውን እንደምን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መጠቀም እንደሚችሉ የሚያስተምር ነው። እናም በኮማንድ ፖስቱ እየተተገበረ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዜጎችን መብቶች ለመጠበቅና ተቃውሞ ካላቸውም ህገ መንግስታዊ በሆነ ሰላማዊ ሁኔታ ማቅረብ እንደሚችሉ ለማሳወቅ ያስቻለ ነው ማለት ይቻላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ህገ መንግስቱ ማንኛውም ዜጋ የመቃወም ህገ መንግስታዊ መብት አለው። ይህን መብቱን የሚገድብ አንዳችም ዓይነት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ሊኖር አይችልም። ቢኖርም ተቀባይነት የለውም—ህገ መንግስቱን ይፃረራልና። ያም ሆኖ ግን ማንኛውም ተቃውሞ አግባብ ባለው ሰላማዊ ሁኔታ መከናወን ይኖርበታል። በማንኛውም ሀገር ውስጥ እንደሚደረገው እዚህ ሀገር ውስጥም ተቃውሞን በኃይልና ሁከት በተሞላበት መንገድ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። እንዲህ ዓይነቱ የመቃወም ፍላጎት የህዝብን ሰላማዊ ህይወት፣ የመልማት ፍላጎትና በዴሞክራሲ የማበብ ህልምን የሚያውክ በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ይህን ሁኔታ ማስተማርና ማሳወቅ ደግሞ የመንግስት ኃላፊነት ነው። እናም የወጣቶቹ መፈታትና ትምህርት ወስደው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ የማድረግ መንግስታዊ ክንዋኔ ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል። እስቲ አሁን ደግሞ በመግቢያዬ ላይ ወደ ጠቀስኩትና ታራሚዎቹ “አይደገምም!” በማለት ቃል ወደ ገቡት ትክክለኛ እሳቤ ላምራ። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አንዳንድ ወገኖች ይህን አባባል ከራሳቸው ፍላጎት በመነጨ ሁኔታ ‘መንግስት ታራሚዎቹን አይደገምም በማስባል ተቃውሞ ማድረግ አይቻልም እያለ ነው’ በማለት ያልተገባ ትርጓሜ እየሰጡት ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ መቃወም እዚህ ሀገር ውስጥ የተከለከለ በማስመሰል ሁኔታውን በማራገብ ሊያጎኑት ሞክረዋል። ይህ ግን ፈፅሞ ትክክል አይደለም። ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ዓይነት መንገድ ለፈለገው ዓላማ ተደራጅቶ የመቃወምም ሆነ የመደገፍ መብት እንዳለው ደንግጓል። እርግጥ ተቃውሞና ድጋፍ የአንድ ዓላማ ሁለት ዘውጎች ናቸው። እነዚህ ሁለት ዘውጎች ግን ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ ማዕቀፍ ውስጥ መመራት ይኖርባቸዋል። ማንኛውም ዜጋ አንድን ክስተት ሲቃወምም ይሁን ሲደግፍ ምርኩዙ ሊሆን የሚገባው ህጋዊ ማዕቀፍ ነው። ህገ ወጥ በመሆን መቃወምም ሆነ መደገፍ አይቻልም። ህጋዊነትንም ይሁን ህገ ወጥነትን በህገ ወጥ ሁኔታ ለማስፈፀም መሻት ራስን መቃወም ነው። ለአንዱ ትክክል የሆነ ሁነት፣ ለሌላው ወገን የተሳሳተ ሊሆን ይችላል። አንድ ወገን የፈለገውን ጉዳይ ለማስፈፀም ሲል እርሱ ራሱ ‘ትክክል አይደለም’ እያለ የሚሟገትለትን ዕውነታ እየተጣረሰ መሆን የለበትም። አንድን ትክክል የሆነ ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ ለማስፈፀም መሞከር ባለጉዳዩ ‘ትክክል ነው’ ያለውን ሃቅ ጭምር መቃወም መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል— ነገርዬው ህጋዊነትን በህገ ወጥ መንገድ መሻት ነውና። ይህን አባባሌን በአንድ ሀገር ውስጥ ተፈፅሟል በተባለ ተረክ ባስደግፈው የተነሳሁበትን ጭብጥ የሚያጎለብትልኝ ይመስለኛል።… “በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ይጠራራሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ‘በሀገራችን ህግ ውስጥ ሞት ቅጣት መኖር የለበትም’ የሚል ነው። እናም እነዚህ በቁጥራቸው በርከት ያሉ የዚያች ሀገር ዜጎች፣ የሞት ቅጣትን የሚያወግዙ መፈክሮችን አንግበው የሀገራቸውን አደባባይ አጥለቀለቁ። ‘በእግዚአብሔር 3 አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ፣ ህይወቱ ማብቃት ያለበት በፈጣሪው እጅ እንጂ፤ በህግ በተደነገገ ቅጣት መሆን የለበትም’ ሲሉም ለመንግስታቸው አቤቱታቸውን አሰሙ።… “…ሆኖም መፈክራቸውን እያስተጋቡ ሳለ፤ ከእነርሱ ትይዩ በሆነ ቦታ ላይ አንድ የተለየ መፈክር የያዘን ግለሰብ ይመለከታሉ። ግለሰቡ በግራ እጁ ላይ የያዘው መፈክርም ‘በሀገራችን ህግ ውስጥ የሞት ቅጣት መኖር አለበት’ የሚል ነው። ታዲያ የሞት ቅጣትን የሚቃወሙት ሰዎች ግር ብለው ወደ ግለሰቡ በመጠጋት በጥያቄ ያጣድፉት ጀመር። ብቸኛው የሞት ቅጣትን የሚደግፈው ሰው፤ ‘የቅጣቱ መኖር ለሌሎች ወንጀለኞች መቀጣጫ ይሆናል’ የሚል አቋሙን በመግለፅ ለሚጠይቁት ጥያቄ ምላሽ ይሰጥ ገባ። ሰዎቹም ግለሰቡ የእነርሱን አቋም እንዲይዝ ቢሞክሩም፤ ሰውዬው ሊስማማ አልቻለም። በዚህ የተናደዱት ‘የሞት ቅጣት አያስፈልገንም’ ባዩች፤ በያዙት መፈክርና በድንጋይ ግለሰቡን ይቀጠቅጡታል። ግለሰቡም በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት ይሞታል። በዚህ ድርጊታቸውም ሰዎቹ መኖር የለበትም ያሉትን የሞት ቅጣት ራሳቸው ገቢራዊ በማድረግ ያቀረቡትን ጥያቄ በአደባባይ ሻሩት።´…” እንግዲህ ከዚህ ምሳሌያዊ ተረክ የምንረዳው ነገር ቢኖር የራስን ዓላማ ለማሳካት ሲባል፤ ህገ ወጥ ተግባርን መከወን ውጤቱ ኢ-ህጋዊነት መሆኑን ነው። ህጋዊነትን በህገ ወጥነት ለማሳካት መሞከር ራስን መልሶ መፃረር ጭምር መሆኑንም እንዲሁ። እናም እንዲህ ዓይነቱን ህገ ወጥ ተግባር “አይደገምም!” ማለት ተገቢና ትክክል ይመስለኛል። ዕውነታውን ትምህርት ወስደው ወደ መጡበት አካባቢ ከተመለሱት ወጣቶች አኳያ ስንመለከተውም፤ ወጣቶቹ “አይደገምም!” ያሉት ቀደም ሲል በሁከቱ ወቅት የፈፀሙትን ህገ ወጥ ተግባርን እንጂ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት እዚህ ሀገር ውስጥ መቃወም አይቻልም ለማለት አይደለም። ወጣቶቹ “አይደገምም!” ያሉት በፀረ- ኢትዮጵያ ሃይሎች ገፋፊነት የተፈፀመው መብትን በህገ ወጥ መንገድ ለማስፈፀም መሞከራቸውን ነው። ወጣቶቹ “አይደገምም!” ያሉት ባለማወቅ የጠፋውን ዜጎች ህይወት፣ የጎደለውን አካልና የወደመውን ንብረት ነው። “አይደገምም!” የተባለው ስሜታዊ በመሆን ህግና ስርዓትን መፃረርን ነው። የማይደገመው ከህግ አግባብ ውጪ የሌሎችን መብት መግታት ነው። “አይደገምም!” የተባለው ለሌሎች እኩይ ፍላጎት መሳሪያ መሆን ነው። የማይደገመው የህዝብን ፍላጎት ወደ ጎን በማለት የራስን ለማሳካት ኢ-ህገ መንግስታዊ መንገድን መከተል ነው። “አይደገምም!” የተባለው ማንኛውንም ጉዳይ በኃይልና በጉልበት ማስፈፀም ነው። በመሆኑም እነዚህ “አይደገምም!” የተባሉት ጉዳዩች ከመቃወም ህገ መንግስታዊ መብቶች ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት ነገር አለመኖሩን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy