Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዓይኖቻችንን ስላልከደንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም!

0 458

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…ይቺም ኑሮ ሆና ይሄን አይነት ውርጭ ይምጣብን! ቅዝቃዜ እንደሆነ በጎመን አይደለል ነገር፡፡ ለነገሩ…ስንቱን ነገርስ ‘በጎመን ደልለን’ እንችላለን! ውርጭ አየር፣ ውርጭ ጠባይ፣ ውርጭ ኑሮ!
ይቺን ስሙኝማ…አስተማሪው ገብቶ ትምህርት ሊጀምር ሲዘጋጅ አንዱ ተማሪ ሲጸልይ ያየዋል፡፡
“ለምንድነው ክፍል ውስጥ የምትጸልየው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ልጁ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “እናቴ ምንጊዜም ከመተኛትህ በፊት ጸልይ ብላኛለች…” አለውና አረፈ፡፡ አሪፍ አይደል!
እናላችሁ…የሆነ ስብሰባ ይጀመራል ከተባለበት አንድ ሰዓት ተኩል አልፏል። ‘እሳቸው’ ገና ስላልመጡ እየተጠበቀ ነዋ! ‘እሳቸው’ ያልከፈቱት ስብሰባ፣ ስብስባ አይባልማ! የተሰብሳቢው ገሚሱ እንቅልፍ፣ እንቅልፍ ይለው ጀምሯል፡፡
እናማ… ዓይኖቻችንን ስላልከደንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም፡፡
እናላችሁ… እሳቸው ‘በተመቻቸው’ ሰዓት ይደርሳሉ፡፡ እናማ ኮራ ይሉና…
“የዛሬውን ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው…” ሲሉ የቤቱ ሦስት አራተኛ ዓይኑን ከፍቶ ተኝቷል፡፡
ይሄ ጥያቄና መልስ ከእለታት አንድ ቀን የሚባል ይመስለኛል….
“ለህዝብ ንግግር አድርገህ ታውቃለህ?”
“አዎ…”
“ምን እያልክ?”
“መቶ ብር የነበረው በታላቅ ቅናሽ ስድሳ አምስት ብር እያልኩ…”
የሚያስተኙ ስብሰባዎች፣ ቃለ መጠይቆች፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎች …ለእንቅልፍ ኪኒን ከምናወጣው ገንዘብ አድነውናል ቂ…ቂ…ቂ… (ምስጋና በሚገባው ቦታ ምስጋና መስጠት አስፈላጊ ነዋ!)
ሀሳብ አለን… አዳራሹ ሀምሳ በመቶው ዓይኑን ከፍቶ የማይተኛባቸው ስብሰባዎች ሊሸለሙ ይገባል፡፡
እናማ… ዓይኖቻችንን ስላልከደንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም፡፡
አንዱ ከሰመመን መስጫ መድሀኒት እኩል ‘ኃይል’ ያለው ንግግር አድርጎ ከመድረክ ሲወርድ ከፍተኛ ጭብጨባ አጀበው፡፡ ኮራ ብሎ ጎኑ ላለው ሰው…
“በንግግሬ ተደስተው እንዴት እንዳጨበጨቡ ሰማህ!” ይለዋል፡፡ ያኛው ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“የተደሰቱት በንግግርህ ሳይሆን ተመልሰህ መድረኩ ላይ እንደማትወጣ ስላወቁ ነው።” እናማ… ሁልጊዜ ስናጨበጭብ ንግግር ማድነቃችን ሳይሆን…ተናጋሪው፤ “እንኳን ጥርግ ብሎ ከመድረክ ወረደልን…” በሚል እንደሆነ ይታወቅልንማ!
እናማ… ዓይኖቻችንን ስላልከደንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም፡፡
ፖለቲካዊ ትንታኔ መስጠት በጀመሩ በአምስተኛው ደቂቃ ላይ ከአድማጩ ወይም ከተመልካቹ ሀያ በመቶ ‘ዓይኑን ከፍቶ የማይተኛባቸው’ ተንታኞች ልዩ ሽልማት ይገባቸዋል፡፡ ምን ግራ ይገባሃል አትሉኝም፣ የሆነ ነገር ‘በተከሰተ’ ቁጥር ከየቀበሮ ጉድጓዳቸው ብቅ የሚሉ ‘ተንታኞች!’ እኛ እኮ እሱ ሰውዬ በቃ አማዞን ጫካ ገብቶ ቀልጧል ብለን ረስተናቸዋል።
ስሙኝማ…አንዱ ምን አለ መሰላችሁ… “ፖለቲከኞችና የልጆች ዳይፐሮች ተመሳሳይ ናቸው። ሁሉም ተመሳሳይ ለሆነ ምክንያት በየጊዜው መለወጥ አለባቸው፡፡” ይሄ ሰው ካለበት የዓለም ጥግ ተፈልጎ የበዓል እንግዳ ይሁንልንማ!
እናማ… ዓይኖቻችንን ስላልከደንንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የቴሌቪዥኑና የራድዮን ጣቢያው እየበዛ ባለበት ይሄ የማስታወቂያ ነገራችን ለምን እንደማይሻሻል አይገርማችሁም፡፡ ልክ ነዋ ..አልፎ አልፎ በጣት ከሚቆጠሩት ማስታወቂያዎች በቀር አብዛኞቹ ‘ያው’ ናቸዋ! (‘ፈረንጅ’… “ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ” የሚለው አይነት ነገር፡፡)
እናላችሁ… የሚያስተኙ ማስታወቂያዎች መአት ናቸው፡፡ ከእኒያ ሁሉ ነጻ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች  እኮ ስንትና ስንት ሀሳቦች ማግኘት ይቻላል፡፡ እንዴት ነው ትንሽ ‘ከዘመን ጋር የዘመነ’ የሚባል አይነት ፈጠራ የጠፋው!… ሁሉም ነገር የዝክረ ትርኢት ‘ጭውውት’ አይነት መሆን አለበት እንዴ! ዓይናችንን ከፍተን የሚያስተኙን ማስታወቂያዎች መአት ናቸዋ! በነገራችን ላይ…ክርኤቲቭ ዲፓርትመንት ምናምን የሚባል ነገር ያላቸው የማስታወቂያ ድርጅቶች አሉ?!
እናማ… አሁን፣ አሁን በጀመሩ ቁጥር “ኤጭ!” የሚያስብሉን ማስታወቂያዎች እየበዙ ነው።
እናማ… ዓይኖቻችንን ስላልከደንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም፡፡
ልጆቹ አንዲት ቡቺ ያገኛሉ፡፡ ታዲያላችሁ… ቤተሰባቸው ዘንድ ይመለሱና…
“ከፍተኛውን ውሸት መናገር የሚችል ይቺን ውሻ ይሸለማል፣” ይላሉ፡፡
ይሄኔ አባትዬው ይቆጣል፡፡ “እናንተ ልጆች፤ በጣም አዝኜባቸዋለሁ፣” ይላቸዋል፡፡
ልጆቹም… “አባዬ፣ ምን አጠፋን!” ይሉታል። አባትየውም…
“ውሸት መናገር መጥፎ እንደሆነ አታውቁም!  እኔ ለምሳሌ  በህይወቴ ሙሉ አንዲትም ቀን ውሸት ተናግሬ አላውቅም…” ይላል፡፡
ይሄኔ አንደኛው ልጅ፣ ቡቺዋን እያቀበለው፣ ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“አባዬ ቡቺዋን ተቀበለኝ፣ አሸናፊው አንተ ነህ…”
ሰውየው ትያትር ቤት ገብቶ፣ በሆነ ባልሆነው ያጨበጭባል፡፡ አብሮት የገባው ጓደኛውም…
“ምን አየህና ነው በየደቂቃው የምታጨበጭበው! ይህን ያህል ትያትሩ ደስ ብሎህ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ እሱዬው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“እባክህ እንቅልፍ እንዳይወስደኝ ራሴን ለማነቃቃት ብዬ ነው…”
እናማ… ዓይኖቻችንን ስላልከደንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም፡፡
የውሸት ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ለጓደኛዋ…
“የሚገርምሽ ነገር መሥሪያ ቤታችን ሰው ውሸት ሲናገር የሚለይ መሣሪያ ተገጠመ…” ትላታለች፡፡ ጓደኛዋም ምን ብላ መለሰች…
“የእናንተ መሥሪያ ቤት ነው የተገጠመው፤ የእኔ ግን ቤቴ አለ…”
“ምን! ውሸት የሚለይ መሣሪያ፣ቤቴ አስገጥሜያለሁ ነው የምትዪው!” ብትላት… ምን ብላ ብትመስል ጥሩ ነው…
“አስገጥሜ ሳይሆን ያገባሁት ራሱ ውሸት የሚለይ መሣሪያ ነው…” ብላት አረፈች፡፡
እናላችሁ… ዓይኖቻችንን ከፍተንም የሚያስተኙን ነገሮች እየበዙብን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የአንዳንዶቻችን ድፍረት እኮ ግርም የሚል ነው፡፡ ምንም የማናውቀው ነገር የለማ! ካቻምናም፣ አምናም፣ ዘንድሮም…
‘የአገር ፖለቲካ’ ጉዳይ ሲሆን ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ ሬድዮ ላይ ቀድመን ገጭ ብለን ‘ትንታኔ’ የምንሰጠው እኛ!
‘የስፖርት’ ጉዳይ ሲሆን ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ ሬድዮ ላይ ቀድመን ገጭ ብለን ‘ትንታኔ’ የምንሰጠው እኛ!
‘የትረምፕ’ ጉዳይ ሲሆን ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ ሬድዮ ላይ ቀድመን ገጭ ብለን ‘ትንታኔ’ የምንሰጠው እኛ!
‘ኃይማኖታዊ’ ጉዳይ ሲሆን ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ ሬድዮ ላይ ቀድመን ገጭ ብለን ‘ትንታኔ’ የምንሰጠው እኛ!
አገር ደግሞ በእኛ ጉዳይ ስልችት ብሎት፣ ዓይኖቹን ሳይከድን እንቅልፍ እንደወሰደው የሚነግረን ጠፍቶ…መከራችንን እናያለን፡፡ የምር ግን… አለ አይደል… ‘እንቅልፍ ለወሰደው ሰው ማውራት’ አሪፍ አይደለም፡፡ “እንኳን ከመድረክ ወረድክ…” ብሎ የሚያጨበጭብ የለማ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ… ዓይኖቻችንን ስላልከደንን ‘እንቅልፍ አልወሰደንም’ ማለት አይደለም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

admass

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy