Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሚዲያ ሀገራዊ ሚና ምን መሆን አለበት?

0 607

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሚዲያ ሀገራዊ ሚና ምን መሆን አለበት?

ቶሎሳ ኡርጌሳ 01-01-17

የአንድ ሀገር ሚዲያ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባሮች ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። በተለይም እንደ እኛ ዓይነት በማደግ ላይ ለሚገኝ ሀገር ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚገባቸውን ሀገራዊ ትልሞችን በማሳወቅና በማስተማር ረገድ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም። ታዲያ በዚህ ፅሑፍ ሚዲያ የሀገራችንን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትልሞችን ዕውን ለማድረግ የሚኖረውን ሚና በመጠኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በህገ-መንግስቱ ላይ በግልፅ የተደነገጉት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች እውን እንዲሆኑ ከመታገሉም በላይ፣ እንዳይሸራረፉም በፅናት ታግሎላቸዋል፤ እየታገለላቸውም ነው። በተለይም ሚዲያ በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎች ላይ የራሱን እሴት የሚጨምር መሳሪያ አድርጎ ይመለከተዋል። ሆኖም ሚዲያ ህግና ስርዓትን አክብሮ ካልተንቀሳቀሰ፤ ያለው ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁለንተናዊ የዕድገትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዓላማዎች ላይ ጉዳት ሊያደረስ እንደሚችል የሚገነዘብ ይመስለኛል። ሆኖም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት የሚዲያን ጉዳት ለማስቀረት ሲል ጥቅሙን የመገደብ አካሄድ ሊከተል የሚችል አይመስለኝም። ሚዲያ እንደ ሌሎቹ የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች ሁሉ፤ ነፃና ጤነኛ ሆኖ በሀገሪቱ ፈርጀ ብዙ የልማት ተግባራት ውስጥ የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚችል የሚገነዘብ ይመስለኛል። ይህም መንግስት ሚዲያው ነፃና ጤነኛ በሆነ አኳኋን እንዲያድግና እንዲመነደግ የሚያደርጉ ስራዎችን የሚፈፀመው ለማንም ብሎ ሳይሆን ዘርፉ በሀገር ግንባታ ላይ ያለውን ጠቀሜታ ስለሚረዳ ነው። ከሁሉም በላይ ዘርፉ በሀገራችን ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብና ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካለው ፅኑ ፍላጎት ተነስቶ የሚተገብረው መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ምንም እንኳን ሀገራችን ውስጥ ያለው ሚዲያ ተግባሩን አቅም በፈቀደ መጠን እየተወጣ ቢሆንም፤ በመንግስት በአሁኑ ወቅት ዘርፉ የሚጠበቅበት ሀገራዊ ሚና በተገቢው መንገድ እየተወጣ ነው ብዬ አላምንም። ይህን አባባሌን በቅርቡ ፓርላማ ቀርበው የመስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወር አፈፃፀም አስመልክተው ገለፃ ያደረጉት የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ይጋሩታል። እርሳቸው ለፓርላማው እንደገለፁት፤ በሚዲያውና በህዝብ ግንኙነት ዘርፎች ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍና ማኅበረሰቡን በመረጃ ተደራሽ ለማድረግ ዘርፉን ለማሻሻል የሚያስችል ሪፎርም ይደረጋል። ይህ የሚኒስትሩ አባባል ሚዲያው ተግባሩን ሲወጣ የመጣ ቢሆንም፤ ዘመኑ በሚጠይቀው ክህሎትና ብቃት መታጀብ እንዳለበት የሚያመላክት ነው። ይህም መንግስት ሚዲያውን በመደገፍ በሀገራችን ዕድገት ላይ የሚጫወተውን ሚና እንዲያሳድግ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳያል። ሚዲያው ለህዝብ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ተግባሩን መወጣት ይኖርበታል። ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታም በትክክለኛው የልማታዊ ጋዜጠኝነት ዘውግ መመራት አለበት። የልማት ኮሙኒኬሽን ንድፈ-ሓሳብ በግልፅ እንደሚያስረዳው፤ የልማት ጋዜጠኝነት መንግስትና ህዝብ በጋራ ተቀናጅተው ከሰሩ ሶስተኛው ዓለም በልማት ጎዳና የማይጓዝበት ምንም ምክንያት የለም። ይህም መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ የልማት ስራ ሲያከናውኑ ሂደቱ በልማት ጋዜጠኝነት ዘገባ መደገፍ እንደሚኖርበት ያስረዳናል። በልማት ጋዜጠኝነት ውስጥ የህዝብን ጥቅም ባማከለ መልኩ መነቀፍ ያለበት ጉዳይ ዝም ተብሎ የሚታይ አይደለም፤ ይዘገባል። 2 ይሁንና ዊልበርና ሽራም የተሰኙ የመስኩ ምሁራን እንደሚሉት የዘርፍ ዘገባ ከአጠቃላይ ጥላቻና ከአጠቃላይ ውዳሴ የራቀ መሆን ይኖርበታል። የልማት ጋዜጠኝነት እንደ ሀገራችን ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገሮች ህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሁነቶችን የማስታወቅ፣ የማስተማርና የማነሳሳት ተግባራትን ያነገበ ነው። እነዚህ ህዝቦች ካሉበት የድህነት አዙሪት ቀለበት ነፃ እንዲሆኑና በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋል። ህዝብን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ፣ ፈጣን ሀገራዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ትክክለኛ የልማት ሃሳቦችን ህዝቡ እንዲገነዘባቸው፣ እንዲያምንባቸውና በአተገባበራቸውም በንቃት እንዲሳተፍ የሚያደርግ እንዲሁም አዎንታዊ የልማትና የዴሞክራሲ የለውጥ እሴትንም የሚገነባ የጋዜጠኝነት ዘርፍ ነው። ታዲያ ይህ ዘርፍ ራሱን ከጭፍን ጥላቻና ከጭፍን ሙገሳ የተላቀቀ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በየጊዜው በሚካሄዱ የልማት ተግባራት ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ነቅሶ በማውጣት የተጣለበትን ሀገራዊ ሃላፊነት መወጣት አለበት። ለአብነት ያህል አንድ የልማት ፕሮጀክት በዕቅድ ደረጃ እንደሚከናወን የገለፀ ሚዲያ፣ ምርቃቱ ላይ ብቻ ለመገኘት ቀጠሮ መያዝ አይኖርበትም። ፕሮጀክቱ በየጊዜው ያስመዘገበውን ዕመርታ፣ በሂደቱ ውስጥ ያጋጠሙት ተግዳሮቶችና ብልሹ አሰራሮች እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ስንክሳሮቹ እየተነቀሱ በባለሙያዎች እንዲተቹ ማድረግ አለበት። እነዚህን ጉዳዩች ሳያከናውን በምርቃቱ ላይ ተገኝቶ “እገሌ የተሰኘው ፕሮጀክት በምንትስ ወጪ ተመረቀ” የሚል ዘገባን ካቀረበ ራሱን ከልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ ጋር እያላተመ መሆኑን ማወቅ ያለበት ይመስለኛል። ሚዲያ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት የውይይት መድረክም መሆን ይኖርበታል። ይህም በወሳኝ ጉዳዩች ላይ ለሚከናወኑ የብሔራዊ መግባባት ስራዎች የበኩሉን ሚና ይጫወታል። አንድ ሚዲያ በተለያዩ ዘርፎች አንድ ዓይነት ድምፆች ብቻ የሚስተናገዱበት ከሆነ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ ተወጥቷል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም ዜጋ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖረው ስለማይችል ነው። አንድ ዓይነት ማህበረሰብ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ሚዲያው የሚታወቅ አጀንዳን በአንድ ጎኑ ብቻ ለታዳሚው የሚያቀርብ ከሆነ ከገደል ማሚቶነት የተለየ ሚና የሚኖረው አይመስለኝም። በመሆኑም የትኛውም ሚዲያ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አመለካከት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ሆኖም ሚዲያ የነፃነቱን ያህል በሀገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚሰራና ተጠያቂነትም ያለው መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ሚዲያ ከስሜታዊነት፣ ከአሉባልተኝነትና ከጭፍን ጥላቻ ርቆ ብሎም እንደማንኛውም ሀገር ሚዲያ የሀገሩን ህጋዊ አሰራሮችን አክብሮ ተግባሩን ማከናወን ይኖርበታል። አዎ! እርግጥም ጋዜጠኝነት ህዝብን የሚያስተምርና የሚያሳውቅ ሙያ እንደመሆኑ መጠን፤ “እዚህ ጋ ጥሩ ተሰርቷል፣ እዚህ ጋ ደግሞ መስተካከል ያለበት ጉዳይ አለ” እያለ ተግባሩን ሳይወጣ ቀርቶ፤ በአንፃሩ በፍፁም ጥላቻ ላይ ተመርኩዞ ሁልጊዜ ፅንፈኛ አስተሳሰቦችን ብቻ የሚያራምድ ከሆነ ህዝብን ከማደናገር ውጪ ሙያዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል ሊባል የሚችል አይመስለኝም። ሚዲያ የህዝብን አስተያየት የሚያስተናግድ፣ የውይይት መድረክ ሆኖ የሚያገለግልና ህግና ስርዓትን አክብሮ የሚሰራ ተቋም እንጂ፤ የጥላቻ ስሜት መጋለቢያ ፈረስ ከሆነ ጤናማ ሆኖ ተግባሩን እየተወጣ ነው ሊባል አይችልም። የዘገባው ዕይታ የተንሸዋረረ ሊሆን ስለሚችልም ሚዛናዊነትን በመሳት አሉባልታዊ ድርሳኖችን እያነበነበ አሊያም እያተመ ለማሰራጨት ይገደዳል። ከፍ ሲልም የአንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን አጀንዳ የራሱ አድርጎ በማቅረብ የጎላ ስህተት ሊፈፅም ይችላል። በመሆኑም ሚዲያው የተቋቋመበትን ሀገር ህግና ስርዓት አክብሮ መስራት ይኖርበታል። እርግጥ ሚዲያ እንደ ማንኛውም የሙያ ዘርፍ የሥራ ነፃነት ስላለው ብቻ የሀገሪቱን ህግና አሰራርን እንዲሁም የራሱን የስነ-ምግባር ደንብ እየደፈጠጠ እንዳሻው ሲሆን ዝም ተብሎ የሚታይ አይመስለኝም። እናም ማንኛውም 3 ሚዲያ የሙያውን ነፃነትን ጭንብል ተሸፋፍነው ወንጀል ለመስራት ሲሞክሩ እንዲሁም ህግና ስርዓትን ደፍቀው በማን አለብኝነት የያዙትን ቀለምና ወረቀት እስኪጨርሱ ድረስ እየለቀለቁ ተጠያቂነት በሌለው አኳኋን በአሉባልታ ላይ የተመሰረቱና የተዛቡ ዘገባዎችን ለህዝብ ሲያቀርቡ ብሎም የፀረ ሰላም ኃይሎችንና የአሸባሪዎችን አጀንዳ ሲያራግቡ የሚዲያውን ጤናማነት በሚቆጣጠሩት የሀገሪቱ ህጎች መጠየቃቸው የሚቀር አይመስለኝም። ‘ለምን?’ ቢባል፣ በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የህግ የበላይነት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ባለመሆኑ፣ በሚዲያ ውስጥም የሚሰራ ሆነም ሌላ ወገን ህጋዊ አሰራሮችን ተላልፎ ሲገኝ በህግ አግባብ መጠየቁ የማይቀር ስለሆነ ነው። በጥቅሉ ሚዲያ በሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ ሙያዊ ሚናውን እንዲወጣ ተግባሩን ሚዛናዊና የህዝብን ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ መወጣት ይኖርበታል። ለዚህም ዘርፉ በመስኩ በሰለጠኑ፣ አቅምና ፍላጎት ባላቸው ባለሙያዎች መደርጀት አለበት። ለዚህ ደግሞ መንግስት በአቅም ግንባታና ሚዲያውን ወቅቱ ከሚጠይቀው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን ማስተካከል ይኖርበታል እላለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy