የሻምበል አትሌት ምሩጽ ይፍጠር አስክሬን ዛሬ አዲስ አበባ ገባ
የአትሌቱ አስክሬን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የአትሌቱ ቤተሰቦች እና ታዋቂ አትሌቶች ተገኝተው የክብር አቀባበል አድርገዋል።
በመቀጠልም የአትሌቱ አስከሬን አሸኛኘት ወደሚደረግበት ቦሌ መድሀኒዓለም በሚገኘው የአትሌቱ መኖርያ ቤት አምርቷል።
የቀብር ስነ ስርዓቱም ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የሚፈጸም ይሆናል።
አትሌት ምሩፅ በ1972 ዓ.ም በሞስኮ በተካሄደው ኦሎምፒክ በ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር ተወዳድሮ ድርብ ወርቅ ለሀገሩ ማምጣት የቻለ ታሪካዊ አትሌት ነው።
ምሩፅ በ1964 ዓመተ ምህረትም በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ለሀገሩ የነሐስ ሜዳሊያ ማስገኘት ችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅና ነሀስ ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ አበርክቷል።
በውድድር ፍጻሜ ላይ በተደጋጋሚ ሳይታሰብ ተፎካካሪዎችን አስከትሎ በሚገባበት አጨራረሱ “ማርሽ ቀያሪው” የሚል መጠሪያ ያገኘው ምሩፅ፥ ባለፉት ጥቂት ወራት በህመም ሲሰቃይ ቆይቷል።
ለህክምና ወጪውም ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከሙያ አጋሮቹ እና ከወዳጆቹ ድጋፍ ተደርጎለታል።
ይሁንና ያጋጠመው የጤና ችግር ፀንቶበት በካናዳ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ታህሳስ 14 2009 ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።